Saturday, 27 September 2014 09:38

‘ዘ ታይምስ’ በዘመነ ኮምፒውተር ወደ ታይፕ ራይተር ተመልሷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

            አለም በቴክኖሎጂ እየረቀቀች ነው፣ የህትመት ኢንዱስትሪውም እጅግ እየዘመነ ነው በሚባልበት በ‘ዘመነ - ኮምፒውተር’፣ ታዋቂው ጋዜጣ ‘ዘ ታይምስ’ 30 አመታትን ወደ ኋላ ተመልሶ ፊቱን ወደ ታይፕ ራይተር ማዞሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡ ዘ ታይምስ ጋዜጠኞቹን ለማነቃቃትና በሙሉ ሃይላቸው ሰርተው ዜናዎቻቸውን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲያስረክቡ ለማስቻል ሲል ነው፣ የጋዜጦች ዝግጅት ክፍሎች በዘመናዊ ኮምፒውተሮች ታግዘው በሚሰሩበት በዚህ ዘመን፣ ዘመኑ ያለፈበት የጽህፈት መሳሪያ ወደሚባለው ታይፕ ራይተር ፊቱን ያዞረው፡፡ዘ ኢንዲፔንደንት እንዳስነበበው፣ የጋዜጣው የስራ ሃላፊዎች በዜና ዝግጅት ክፍሉ ውስጥ ግዙፍ የድምጽ ማጉያ ተክለዋል፡፡

ይህ የድምጽ ማጉያ የታይፕ ራይተር ድምጽ የሚያወጣ ሲሆን፣ ድምጹ እየፈጠነ የሚሄድና ጋዜጠኞችን የሚያነቃቃ ነው ተብሏል፡፡ ድንገት በዝግጅት ክፍሉ ውስጥ ተገትሮ ባገኙት የድምጽ ማጉያ ግራ የተጋቡ ጋዜጠኞች እንደነበሩና ከመካከላቸው አንዱም፣ በሚያደምጠው የታይፕ ራይተር ድምጽ በመረበሽ ድምጽ ማጉያውን ለመዝጋት መሞከሩን ዘገባው ገልፃል፡፡ የጋዜጣው የቀድሞ ባልደረባ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ለንደን በሚገኘው ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ጆርጅ ብሮክ፣ ዝግጅት ክፍሉ ታይፕ ራይተሮችን መጠቀም ያቆመው እ.ኤ.አ በ1980 ዎቹ እንደነበር አስታውሰው፣ የአሁኑ የታይፕ ራይተር ድምጽ እርግጥም እንደታሰበው ጋዜጠኞችን ለስራ የሚያተጋ መሆንና አለመሆኑን ለመገመት እንደሚያዳግታቸው ገልጸዋል፡፡ የጋዜጣው የዲጂታል ክፍል ምክትል ሃላፊ ሉሲያ አዳምስ በበኩላቸው፣ ነገርዬው አስቂኝ ነው፤ ታይፕ ራይተር ጊዜው ያለፈበት ቢመስልም፣ ቴክኖሎጂ ነውና ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል፡፡

Read 1847 times