Saturday, 27 September 2014 09:41

በአለማችን ከ800 ሚ. በላይ ህዝብ የምግብ እጥረት ተጠቂ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያ ችግሩ ከተስፋፋባቸው አገራት አንዷ ናት ተብሏል

          የአለማችን ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልገው የምግብ እህል ከሁለት እጥፍ በላይ ማምረት ቢቻልም፣ አሁንም ድረስ በተለያዩ የአለም አገራት የሚገኙ ከ800 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቂ ምግብ እንደማያገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡ባለፉት አስርት አመታት በአለማችን የርሃብ ችግር በተወሰነ መልኩ ቢቀንስም ባለፉት ሁለት አመታት 11 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ የምግብ እጥረት ተጠቂ እንደነበረ የጠቆመው ዘገባው፣ የምግብ እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚታይባቸው አገራት መካከልም፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ እንደሚገኙበት ገልጿ ል፡፡ በቂ ምግብ የማያገኙ በርካታ ዜጎች ካሏቸው አገራት አንዷ በሆነችው ኢራቅ፤ ከአራት ኢራቃውያን አንዱ የምግብ እጥረት ችግር ሰለባ መሆኑንም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳምንቱ መጀመሪያ ያወጣውን መረጃ በመጥቀስ ዘገባው ጠቁሟል ፡፡

የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዳለው፣ ምንም እንኳን በአለማችን በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልገው የምግብ እህል ከሁለት እጥፍ በላይ ማምረት ቢቻልም፣ ምርቱን ለተመጋቢዎች በማድረስ ረገድ ክፍተቶች በመኖራቸው የምግብ እጥረት ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ ምርታማነት ቢያድግም የተመረተውን የምግብ እህል ለሸማቾችና የችግር ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ማድረስ ካልተቻለ፣ የምግብ እጥረቱ እንደማይቀረፍ የገለጸው ድርጅቱ፣ ለዚህም ሴፍቲ ኔትና ሌሎች የማህበራዊ ዋስትና አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

ከሚሊኒየሙ የልማት ግቦች አንዱ በታዳጊ አገራት የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ዜጎች ቁጥር እስከ 2015 ድረስ በግማሽ መቀነስ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተመድ ሪፖርትም ግቡን ለማሳካት እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ማስታወቁን ጠቁሟል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራትና በመካከለኛው ምስራቅ የሚከሰቱ Yተፈጥሮ አደጋዎችና ግጭቶች፣ የአካባቢው አገራት ግቡን ለማሳካት የሚደርጉትን እንቅስቃሴ እያደናቀፉት እንደሚገኙ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

Read 2558 times