Saturday, 27 September 2014 09:46

ከሥራ ጋር የተያያዘ ጭንቀት ለአስም ሊያጋልጥ ይችላል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

            ሥራዬን ላጣ እችላለሁ የሚል ስጋትና ጭንቀት በአስም የመያዝ አደጋን ሊጨምር እንደሚችል በአውሮፓ የተደረገ አዲስ ጥናት አመለከተ፡፡ ጥናቱ በጀርመን የሚገኙ ከ7ሺ በላይ ተቀጣሪ ሠራተኞችን ያሳተፈ እንደነበር ታውቋል፡፡ እነዚህ ተሳታፊዎች አውሮፓ የኢኮኖሚ ድቀት ባጋጠማት ወቅት (እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም) ስለመተንፈሻ አካላት መዛባትና በሁለት ዓመት ውስጥ ከሥራችን እንፈናቀላለን ብለው ያስቡ እንደሆነ ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጥናቱ በተካሄደባቸው ጊዜያት ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ከ100 በላይ የሚሆኑት አዲስ የአስም በሽታ እንደተቀሰቀሰባቸው ኸልዝዴይ ኒውስ ጥናቱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ከሥራ ጋር የተገናኘ ጭንቀት በ25 በመቶ ባደገ ቁጥርም በአስም የመያዝ አደጋ በ24 በመቶ እንደጨመረ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ሥራ የማጣት ዕድላችን ከፍተኛ ነው ብለው ያስቡ የነበሩት ተሳታፊዎችም በአስም የመያዝ ዕድላቸው ወደ 60 በመቶ ማሻቀቡን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡በሁለት ዓመት ውስጥ ሥራችንን የማጣት ዕድላችን ዝቅተኛ ነው ወይም ስጋት የለብንም ካሉት ይልቅ ሥራ የማጣት ዕድላችን ከፍተኛ ነው ያሉት በዕድሜ ወጣት፣ በትምህርት ብዙ ያልገፉ፣ ያላገቡና ዝቅተኛ ወርሃዊ ደሞዝ ያላቸው እንደነበሩ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ የስራ ማጣት ያሰጋቸው ተሳታፊዎች፤ ቋሚ የሥራ ኮንትራት የማግኘት ዕድላቸው እጅግ ዝቅተኛና በድብርት ለመሰቃየት የበለጠ የተጋለጡ እንደነበርም ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ የጥናት ውጤቱ ባለፈው ሳምንት “ጆርናል ኦፍ ኢፒዲሞሎጂ ኤንድ ኮሙኒቲ ኸልዝ” ላይ እንደወጣ ተገልጿል፡፡

ጥናቱ፤ ከስራ ጋር የተያያዘ ጭንቀት ለአስም መንስኤ እንደሆነ አላረጋገጠም ይላሉ - ተመራማሪዎቹ፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል በስነልቦና ጭንቀት ላይ የተደረገ ጥናትም ለአስም አደጋ የሚያጋልጥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ደርሰንበታል ብለዋል፡፡ “የጥናት ውጤቱ፤ በኢኮኖሚ ድቀቱ ወቅት ጊዜ በእንግሊዝ የመተንፈሻ አካላት መዛባት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበትን ምክንያትም ሊመልስ ይችላል” በማለት ተመራማሪዎቹ በጆርናሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስፍረዋል፡፡ ይሄ በዚህ እንዳለ የአባቶች አጫሺነት ህፃናትን ለአስም በሽታ እንደሚያጋልጥ በጀርመን የተካሄደ ጥናት ጠቁሟል፡፡ በተለይ አባት የረዥም ጊዜ አጫሽ ከሆነ፣ ህፃኑ በአስም የመያዝ ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ብለዋል - አጥኚዎቹ፡፡ ቀደም ሲል የአባት ማጨስ በህፃኑ ላይ ስለሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ማንም ትኩረት ሰጥቶት እንደማያውቅ ያወሱት ተመራማሪዎቹ፤ አዲሱ ጥናት የእናትየዋን ያህል አባትም በልጅ ጤና ላይ ይሄን ያህል ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ መታወቁ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

Read 2705 times