Saturday, 04 October 2014 14:07

የማሽተት ችሎታ በህይወት የመቆየት ዕድልን ያመለክታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በእድሜያቸው የገፉ ሰዎችን የማሽተት ችሎታ በመለካት፣ በቀጣይ በህይወት የሚቆዩበትን ጊዜ ለመተንበይ እንደሚቻል በአሜሪካ የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰራ ጥናት ማረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተመራማሪዎች ከ57 እስከ 85 አመት እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 3ሺህ ሰዎች ላይ ያደረጉትን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ጥሩ የማሽተት ችሎታ ያላቸው ሰዎች፣ የማሽተት ችሎታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ቀጣዮቹን 5 አመታት በህይወት የመቆየት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
ጥናቱ በተከናወነባቸው ሰዎች ላይ የተመዘገበው ውጤት እንደሚያሳየው፣ ዝቅተኛ የማሽተት ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ሲሞቱ፤ ጥሩ የማሽተት ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የሞቱት 10 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡
ተመራማሪዎቹ ለግለሰቦቹ የአሳ፣ የብርቱካን፣ የጽጌረዳ አበባ፣ የቆዳና የናና መዓዛዎችን በእስክርቢቶ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲያሸቱና የምን መዓዛ እንደሆነ እንዲለዩ በመጠየቅ የማሽተት ችሎታቸውን መዝግበዋል፡፡ ከአምስት አመታት በኋላም፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው ሰዎች፣ ምን ያህሉ በህይወት እንዳሉና ምን ያህሉ እንደሞቱ አረጋግጠዋል፡፡ በመቀጠልም የሞት መጠኑን ከማሽተት ችሎታ ጋር በማጣመር፣ በሁለቱ ነገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥናት ሞክረዋል፡፡
የማሽተት ችሎታ እየቀነሰ መምጣት በቀጥታ ለሞት እንደማይዳርግ የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ ይሄም ሆኖ ግን ክስተቱ እንደማስጠንቀቂያ ሊወሰድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
“የማሽተት አቅም መቀነስ በቀጥታ ለሞት አይዳርግም፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በግለሰቡ ጤንነት ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚያመላክት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ በምርምሩ ያገኘናቸው ውጤቶች በጤና ምርመራ ላይ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ለአደጋ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ በሽተኞችን ለይቶ ለማወቅ የሚያግዝ ፈጣንና ወጪ የማይጠይቅ የምርመራ ዘዴ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል” ብለዋል የተመራማሪ ቡድኑ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃያንት ፒንቶ፡፡
በህይወት የመቆየት ዕድልን የሚወስኑ እርጅና፣ የምግብ አወሳሰድ፣ የሲጋራ ሱሰኝነት፣ ድህነትና አጠቃላይ የጤና ሁኔታን የመሳሰሉ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ የማሽተት ችሎታቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ለሞት የመዳረግ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን የማሽተት ችሎታ መቀነስ፣ በምን መንገድ በህይወት ላለመቆየት እድል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በግልጽ ባይታወቅም፣ ተመራማሪዎቹ በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የራሳቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
አነስተኛ የማሽተት ችሎታ መኖር፣ በግለሰቦች ሰውነት ውስጥ የሚገኙ ያረጁ ህዋሶች የሚታደሱበት መጠን አነስተኛ መሆኑን ሊያመላክት ይችላል ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡ ጤናማ የማሽተት ችሎታ እንዲኖር ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል፣ በአፍንጫ ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት በየጊዜው መታደሳቸው ይጠቀሳል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሰዎች ዝቅተኛ የማሽተት ችሎታ ስላላቸው መጨነቅ እንደሌለባቸው የመከሩት ፕሮፌሰር ፒንቶ፤ ጉዳዩ ከጉንፋን፣ ከአለርጂክና ሳይነስን ከመሳሰሉ የጤና ችግሮች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ የማሽተት ችግሩ እየተባባሰ ከመጣ ግን፣ ሃኪማቸውን ማማከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑትና በጥናቱ ውስጥ ያልተሳተፉት ፕሮፌሰር ቲም ጃኮብ በበኩላቸው፤ በጥሩ ሁኔታ የተከናወነው ይህ ጥናት፣ የማሽተት ስሜትና ጤንነት በእጅጉ እንደሚቆራኙ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በሰውነት አጠቃላይ ሁኔታና በስነ-ልቦና መካከል ትስስር እንዳለ የጠቆሙት ጃኮብ፤ ለአብነትም ማሽተት አለመቻል ድብርት እንደሚፈጥር፣ ድብርትም በመስማት ችሎታ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

Read 4349 times