Saturday, 04 October 2014 14:09

ህፃናት በጥርስ መበስበስ ችግር እየተጠቁ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ወላጆች የጥርሳቸውን ጤንነት ሊከታተሉላቸው ይገባል

የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና ተመራማሪዎች፤ 54ሺ ገደማ የሚሆኑ ህፃናትን ጥርሶች ከመረመሩ በኋላ 12 በመቶ በሚሆኑት ህፃናት ላይ የጥርስ መበስበስ ምልክቶችን እንዳገኙ ይፋ አደረጉ፡፡ ህፃናቱ በአማካይ ሶስት ጥርሶቻቸው አንድም በስብሰዋል አሊያም ወልቀዋል ወይም ደግሞ ተሞልተዋል ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡ ከቦታ ቦታ የጥናት ውጤቱ ከፍተኛ ልዩነት ያሳየ ሲሆን በሌችስተር አካባቢ 34 በመቶ ያህሉ ህፃናት የጥርስ መበስበስ ሲስተዋልባቸው በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ 2 በመቶ ያህሉ ብቻ የችግሩ ተጠቂዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
አንዳንድ ህፃናት ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚከሰት የተለየ ዓይነት የጥርስ መበስበስ እንደተገኘባቸው ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ይሄ ችግር የሚያጠቃው የላይኛውን የፊት ጥርሶች ሲሆን በፍጥነትም ወደ ሌሎች ጥርሶች የሚሰራጭ እንደሆነ ታውቋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የጥርስ መበስበስ ችግር በጡጦ ወይም በኩባያ ጣፋጭ አሊያም ስኳር የበዛባቸው ፈሳሾችን በመውሰድ የሚከሰት ነው ተብሏል፡፡
የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና ተመራማሪዎች፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ጣፋጭ ምግቦችንና መጠጦችን አልፎ አልፎና በጣም በትንሹ መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የእናት ጡት ያቆሙ ህፃናት በሚወስዷቸው ምግቦችና መጠጦች ላይም ስኳር እንዳይጨምሩ ለወላጆች ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ወላጆችና ሞግዚቶች፤ ህፃናቱ የመጀመሪያ ጥርሳቸውን እንዳበቀሉ መቦረሽ መጀመር አለባቸው የሚሉት የህክምና ባለሙያዎች፤ ልጆቹ ሰባት ወይም ስምንት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስም የጥርስ ንፅህና አጠባበቃቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

Read 2597 times