Monday, 06 October 2014 08:15

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

          ከአዋሳ እርሻ ኮሌጅ በዲፕሎማ ከተመረቅሁ በሁዋላ እዛው ከተማ 75 ዓመተምህረት ላይ በማውቀው ሰው እርዳታ ግብርና ሚኒስቴር ተቀጠርኩ፡፡ ‘አዲስ አበባ እንመድብሽ’ ቢሉኝም አልሄድም ነበር፡፡ አዲስአባን ጠላሁዋት፡፡ በቦዲ ሚሞሪ (የገላ ትውስታ ወይም የገላ ትዝታ) ይመስለኛል፡፡ ቦዲ ሚሞሪ (Body Memory) በአንጎል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላ የአካል ክፍል ውስጥም (በጡንቻ፣ በልፋጭ፣ በሞራ፣ በጉበት፣ በሳንባ ወዘተ) ትውስታ ሲከማች ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳዩ ከሽሮሜዳው አላዛር ጋር ተደርቦ አዲስአባን ስጠላ ትንሽ ልክ አይደለም፡፡ ባቡር ጣቢያ ምን አደረገኝ? በቅሎ ቤትና መካኒሳ ምን አደረጉኝ? እናቴ ለምን አዲስአባ እንደማልመጣ ስትጠይቀኝ  “እማመጃ ሙች መንግስት በእጣ ልመድብ እያለ አዋሳ ደረሰኝ፤ ገንዘብ ከፍዬ እንኳን የሚለውጠኝ አላገኘሁም፡፡ ምስክር ካስቸገረችሽ በደንብ ስቋቋም እወስዳታለሁ” አልኳት እማማ ‹ኸረ ለልጅቷ አይደለም፤ በሰራተኛ ከምታድግ ከእኔ ጋ ትሆናለች፡፡

ይሄን ደርግ የተባለ በጥባጭ ማን ላከብን እመቤቴ› ምናምን ምናምን፡፡ በልቤ የፈለግሽውን በይ እላለሁ፡፡ የአገራችን ምስክር መሃላ ነው፡፡ እንዋሽና እንምላለን፡፡ የማንምልበት የለም፡፡ ልብ ያልኩት እንዲህ ስገባበት ነው፡፡ በእግዚአብሔር እንምላለን፤ በሃይለስላሴ እንምላለን (ከንጉሠ ነገሥቱ የሚቀረው ጢማቸው ነው፣ እና ቀን ጠብቀንም ከተመቸን በጢማቸውም እንምላለን)፣ በመላእክት፣ በአባት፣ በእናት፣ በምንወደው ሰው፣ በደርጉ፣ በልባችን፣ በሳንባችን፣ በባላችንና በሚስታችን እንምላለን፡፡ በዚህ በዚህ ተለማምጄ ምናልባት በፋሲል እምላለሁ፤ በፋሲል ፔርሙስም እምላለሁ፡፡ ወደ አዋሳ ለመሄድ አንዳንድ እቃዎቼን በሻንጣ ስከት ያገኘሁዋቸውን የማርኪሲስት መፅሀፍት ለማድቤት እሳት ወረወርኩ፡፡ እስር ቤት ሙላት የሰጠኝን ያማረች ቅል እንዳትሰበርብኝ በጥንቃቄ በወረቀትና በላስቲክ ጠቅልዬ በልብሶቼ መሃል ወሸቅሁዋት፡፡ ድሮ አበባና ተክሎችን ከሰበሰብኩባቸው ሶስት አልበሞቼ አንዱን ብቻ አገኘሁ፡፡

ታስሬ ከተወሰድኩ በኋላ በበነጋታው ፈታሾች እኔን የሚወነጅሉበት ጸረ-አብዮት ወረቀት ሊያገኙ ሲበረብሩ እንደነበር ተነግሮኛል፡፡ የቀሩትን በርባሪዎቹ እንደወሰዱአቸው አውቃለሁ፡፡ ቢያበሳጭም ምን ይደረጋል? “ምን አውቃለሁ የሆነ ወረቀት ሰብስበው ሄዱ” አለች እማማ፤ ቀኑ ሲያልፍ፡፡
አላለፈም፡፡ በልጅነቴ የለፋሁበት ሲጠፋ ሃዘን አይገባኝም አሉ? ሃዘን ካለ የአልበሞቼ ትዝታ አለ ማለት ነው፡፡ ሁሉም አልበሞቼ ገና እኔ ውስጥ አሉ፡፡ ትንሽ ተቀምጬ ከትውስታዬ ሊጠፋ የጀመሩ አትክልቶችን እየገለጥኩ አየሁ፡፡ የመፅሀፉ ጠረን መስከረም ወር ውስጥ እንደሚያጋጥም የእንጦጦ ሸለቆ ነው፡፡ መጨረሻው ገፅ ላይ አንድ ጠጅ ሳር አገኘሁ፡፡ ገና በጣቴ ስነካካው ፈራረሰ፡፡ መደርደሪያዬ ላይ ደሞ ምናልባት ከሰባት አመታት በፊት አላዛር ለልደት ቀኔ የሰጠኝን አንድ ዳልሜሽያን የውሻ አሻንጉሊት አገኘሁ፡፡ ወደ ግድግዳ ገፋ ተደርጋለች፡፡ አቧራ ለብሳለች፡፡ በአዲስነቷ በጥቁር ነጠብጣቦች የተሸፈነች በረዶ ነጭ ነበረች፡፡ አይኖቿ ጥቁር ሆነው በዙሪያቸውን አረንጓዴ ናቸው፡፡ አፍንጫዋ ጥቁር ነው፡፡ ጅራተ ጎራዳ ናት፡፡ አልጋዬ ላይ በጀርባዬ ስሆን ሳታቋርጥ ታየኝ ነበር፡፡ አስተያየቷ ያባባል፡፡ ቆሻሻዋን አራግፌ ሻንጣዬ ውስጥ ከተተትኳት፡፡
አቶ አባይ አዋሳ አደርሳታለሁ ስላሉ ሳሎን ተቀምጬ እሳቸውን ስጠብቅ ቆይቼ፣ ሰልችቶኝ መኝታ ቤት ስገባ፣ እማማ ሻንጣዬን ስትበረብር አገኘሁዋት፡፡ በቀኝ እጅዋ ዳልሜሽያን አሻንጉሊቷን ይዛለች፤ ቀና ብላ በማዘን አየችኝና ምንም ሳትናገር እነበረችበት አመቻችታ አስቀመጠቻች፡፡ አፍሬ ወደ ሳሎን ተመለስኩ፡፡ አለሁበት መጥታ ምንም ነገር እንዳልሆነ፡፡
“አባይ የት ጠፋ? እያረጀ ሲሄድ ቀጠሮ መርሳት ጀመረ?” አለች፡፡ አልመለስኩላትም፡፡
አጠገቧ እግሮቿ ስር በጉዞዬ አውቶቡስ ውስጥ የምበላቸው ብርቱካኖች ሙዞች ተደጋግፈው ተቀምጠዋል፡፡ ብርቱካኑ ቅጠልያ ቀለሙ አልተወውም፡፡ ሎሚ አስተኔ ቆምጣጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፍራፍሬ ኮርፖሬሽን ቤመንገዱ ድንኩዋን ተክሎ ኪሎው በሁለት ብር ካምሳ ከሚሸጠው ከእማማ ገዝታ ነው፡፡ ከነዚህ ጎን ደሞ ገና አረንጓዴነቱ ያለቀቀው ጥሬ ሙዝ አለ፡፡ እማማ ከመስሪያቤቷ ስትወጣ፣ የስራ ጓደኛዋ ልጅሽን ደህና ግቢ በይልኝ ብላ የላከችልኝ ነው፡፡ ከሴትዬዋ አልቀራረብም፡፡ ሙዞቹ ጥሬ ከመሆናቸው የተነሳ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጠንከራ ሰረሰሮች አሉዋቸው፡፡ ስድስቱም አንድ አንጓ ላይ እንደ ደራጎን ጥርስ ተደርድረዋል፡፡
እማማ የላስቲክ ቀረጢቱን በእግሯ እየነካካች ታስባለች፤ ስለ እኔ ጉዞና ሰፈር ስለመቀየር ይሁን ስለ አባይ እንጃ፡፡ እኔ መሄዴ ነው፡፡ እማማ ብቻዋን መኖር የምትችል አይመስለኝም፡፡ ከአባይ ጋር ለምን እንደማይጋቡ አይገባኝም፡፡ አሻንጉሊቴን ባታይብኝ ኖሮ ትዳር ስለመመስረት እጠይቃት ነበር፡፡ ግን፤“አንቺስ አሻንጉሊት ከመሰብሰብ አላዛርን ጠበቅ አታደርጊም ነበር” ብትለኝስ ብዬ ተውኩት፡፡ በየቀኑ በደም ስሬ፣ በልቦናዬ ደካማ የሚያደርገኝን ነገር የምሰበስብ ይመስለኛል፡፡----
(ከደራሲ አዳም ረታ
መረቅ የተሰኘ አዲስ ረዥም ልብወለድ
መጽሃፍ ውስጥ የተቀነጨበ፤2007 ዓ.ም)

Read 6202 times