Monday, 06 October 2014 08:28

አለማቀፉ “ራማዳ አዲስ” ሆቴል ከዓመት በኋላ ስራ ይጀምራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

        በሰባት የዓለም ሀገራት 7,540 ያህል ሆቴሎችን የሚያስተዳድረው ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ፤ “ራማዳ አዲስ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ሆቴል ከአንድ ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ይገነባል የተባለው ይኸው ሆቴል፤ 128 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎችና 8 የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው የአለማቀፍ ሆቴሎች ስብሰባ ላይ የተሳተፈው ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ሆቴሉ በ2008 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብሏል፡፡
የ“ራማዳ አዲስ” ሆቴል ባለቤት አቶ አዱኛ በቀለ፤ ኩባንያቸው ኤዲኤም ቢዝነስ ፒኤልሲ በአለማቀፍ ደረጃ የገነነ ስምና ዝና ካለው ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ ጋር በጋራ በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሆቴሉ ሲጠናቀቅ የሃገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ወደ ፊትበማራመድ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር ለ250 ያህል ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ “ራማዳ” በሚለው ስም በአለማቀፍ ደረጃ 830 ያህል መካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ አመት የብራንዱ 60ኛ አመት ይከበራል ተብሏል፡፡
 የዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ሲሆን በ71 የዓለም ሃገራት 650,200 ክፍሎች ያላቸው 7540 ሆቴሎችን ያስተዳድራል፡፡
የሆቴል ግሩፑ በአፍሪካ ውስጥ በጋና፣ በሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ቱኒዚያ ዋይንድሃም በሚለው ስም ሆቴሎች ያሉት ሲሆን በኬንያ፣ ታንዛኒያና ናይጄሪያ ደግሞ ራማዳ በሚል 6 ሆቴሎችን ከፍቷል፡፡
 በኢትዮጵያ የሚከፈተው “ራማዳ አዲስ” ሆቴል 7ኛው ይሆናል ተብሏል፡፡ ሰሞኑን በሸራተን አዲስ በተከናወነ ስነስርአት ላይ ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕ “ራማዳ አዲስ”ን ለማስተዳደር ከኤዲኤም ቢዝነስ ጋር የማኔጅመንት ኮንትራት ውል ተፈራርሟል፡፡

Read 2199 times