Saturday, 11 October 2014 13:20

በዲላ ዩኒቨርሲቲ ያዘኑት የተማሪ ቤተሰቦች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(13 votes)

             ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተመደበ ተማሪ ይዘው ወደ ከተማዋ የሄዱ ቤተሰቦች (አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እህት፣ አሳዳጊ) በዩኒቨርሲቲው ባዩትና በገጠማቸው ነገር በጣም ማዘናቸውንና ማፈራቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤተሰቦቹን ያገኘኋቸው ተማሪዎቹን አድርሰው ከዲላ ወደ አዲስ አበባ በአውቶብስ ሲመለሱ ነበር፡፡ ከንጋቱ 11፡20 ገደማ መናኸሪያ ስደርስ፣ አውቶብሱ ሞልቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በመጨረሻው ወንበር ሁለት ክፍት ቦታ አየሁ፡፡ የተሻለ መቀመጫ ባገኝ ብዬ ወደፊት ሳማትር፣ መሃል አካባቢ አንድ ክፍት ቦታ አየሁ፡፡ ወደዚያው ሳመራ፣ ፊት አካባቢ ነጠላ ተከናንባና መስኮቱን ተደግፋ ከተኛችው ሴት ጎን ያለው ወንበር ባዶ ስለነበር ተቀመጥኩ፡፡ በዙሪያዬ የተቀመጡት መንገደኞች፣ ልጆቻቸውን ዲላ ዩኒቨርሲሲቲ አድርሰው እየተመለሱ ነበር፡፡ ግቢው በጣም ሞቃት ስለሆነ ተማሪዎች “ሰመራ” በማለት በሰየሙት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ ስላዩትና ስላጋጠማቸው ነገር በምሬት ያወሩ ነበር፡፡

ሰዎቹ ስለዩኒቨርሲቲው የሚናገሩት ፈፅሞ ለማመን የሚያዳግት ነው፡፡ ነባር ቀርቶ አዲሶቹም ቢሆኑ፣ ሰዎቹ እንደሚሉት ይሆናል ብዬ ስለማልገምት፣ በትኩረት አዳምጣቸው ጀመር፡፡ ይህንን ችግር፣ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል ብዬ ስላሰብኩ የተማሪዎቼ ቤተሰቦች በዝርዝር እንዲነግሩኝ ጠየቅኋቸው፡፡ ከአዲስ አበባ የሄዱት አንድ ወላጅ፣ “ያየናቸውን ችግሮች መንግስትና ሕዝብ እንዲያውቋቸውና መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ስለሆነ እንነግርሃለን፡፡ ለነገሩ እኔም መፃፌ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር መናገር እንፈልጋለን፡፡ እኛ የነገርንህን ትተህ፣ መንግስትን ለማስደሰት የሌለውን አለ ብለህ ቀባብተህ የምታወጣ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ችግሩ ሳይቀረፍ እንዳለ ይቀጥላል፡፡ እኛ የምንነግርህ፣ ማንንም ለማሳጣትና ለመወንጀል አይደለም፡፡ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከተው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተዳደር ጉባኤ፣ ይህን ስር የሰደደ ችግር አውቀውና ተገንዝበው መፍትሄ እንዲፈልጉለት ነው፡፡

ስለዚህ የምንነግርህን እንደወረደ በትክክል ታቀርባለህ?” በማለት ጠየቁኝ፡፡ ሌሎችም፣ “ትክክል ነው፣ ትክክል ነው፡፡ እኛ፣ ልጆቻችን ያሉበት ሁኔታ አሳስቦን ነው እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደለም” በማለት በሰውዬው ሐሳብ መስማማታቸውን ገለጹ፡፡ እኔም በጠየቁት መሰረት ለማቅረብ ስለተስማማሁ፡፡ እነሆ በቃል የነገሩኝን በጽሑፍ እንደወረደ አስፍሬዋለሁ፡፡ እህቱን ይዞ ዲላ የሄደው ወጣት፣ ችግሩ የጀመረው ገና ዩኒቨርሲቲው ጋ በፊት ወደ ዩኒቨርሲቲው መታጠፊያ ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከመታጠፊያው እስከ ግቢው ያለው መንገድ በግምት አንድ ኪ.ሜ ተኩል እንደሚሆን ጠቅሶ፣ ኮብል ድንጋይ እንኳን ስላልለበሰ በጭቃ ቦክቶ እንደነበር ገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲው፣ ተማሪዎችን ከመታጠፊያው ተቀብሎ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርስ ሰርቪስ ማዘጋጀቱ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጾ፣ ሌሎች ማጓጓዣዎች ወደ ግቢው እንዳይደርሱ መከልከሉ ግን አግባብ አይደለም ብሏል፡፡ “ባጃጅና ጋሪ ወደ ግቢው እንዳይሄድ ተከልክሏል፡፡ እኛ ያየነው አንድ ሰርቪስ ነው፡፡ ሰርቪሱ፣ እኛ ስንደርስ ቀደም ብለው የደረሱ ተማሪዎችንና ወላጆችን አፍኖ ሄደ፡፡ የወሰዳቸውን አራግፎ እስኪመለስ ይቆያል፡፡ መጠበቅ ያልፈለገ ሰው ሌላ አማራጭ እንዲጠቀም መፍቀድ ነበረባቸው፡፡ ከወደ ዩኒቨርሲቲው የመጣ ጋሪ አግባብተን እህቴ ጋሪው ላይ ስትወጣ፣ “እንግዳ ተቀባይ” የሚል ባጅ ያንጠለጠለ ወጣት፣ ‹በዚህ መሳፈር አትችይም፤ ነይ ውረጂ› እያለ እያመናጨቀ ሲጎትታት በጣም ስለተናደድኩ ኃይለ ቃል ተለዋወጥን” በማለት ገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ግቢ ደርሰው ሲወርዱ፣ ያየውንና ያጋጠመውን ነገር ማመን እንዳቃተው ወጣቱ ይገልጻል፡፡ ‹ዲላ ዩኒቨርሲቲ› የሚል ቀስት እንጂ አጥር እንኳ የለውም፡፡ በርካታ ህንፃዎች ከርቀት ቢታዩም የተቀቡት ነጭ ቀለም ደብዝዞ፣ መስኮቱ ላይ የተጠራቀመው አቧራ፣ ዝናብ ሲመታው መስመር እየሰራ በወረደው ቀይ ቀለም ጠፈጠፍ ተዥጎርጉረው ሲያይ፣… በጣም እንደቀፈፈው ይናገራል፡፡ እህቱ ወደ ተመደበችበት ህንፃ ጠጋ ሲሉ ያየው ደግሞ በጣም የባሰ ነው፡፡ በአጠቃላይ ህንፃው አቧራ ከመልበሱም በላይ ኮሪደሩም ሆነ ክፍሎቹ መጥረጊያ ነክቷቸው የሚያውቁ አይመስልም፡፡ ወደ ፎቅ መውጫው ደረጃ የተማሪዎች እግር ያመጣው ጭቃ ተጋግሮበት የቀለጠ ሻማ መስሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ተማሪዎች እንደገቡ ውሃ ስለሌላቸው ሰልፍ ወጥተው ነበር ያለው ተሳፋሪ፤ በዲላ ከተማ ለ6 ዓመት የኖረ ውስጥ አዋቂ ነው፡፡ “ውሃ የላቸውም፣ ሽንት ቤት የለም (ሽንት ቤቱ ሞልቶ አያስገባም ተብሎ እኛም በአካል ተገኝተን አይተናል) ልጆቹ የውሃና የሽንት ቤት ጥያቄ አቅርበው ሰልፍ ስለወጡ፣ ፖሊስ ተጠርቶ ተደብድበው እንዲበተኑ ተደረጉ፤ ለብዙ ጊዜ የታሰሩም ነበሩ፡፡ ሽንት ቤቱ እስካሁንም አልተሰራም፡፡ የውሃና የመብራት ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ መብራት በት/ቤቱ ውስጥ ሁለትና ሶስት ቀን የሚጠፋበት ጊዜ ሞልቷል፡፡ የውሃ ችግርማ አይነገርም፡፡ ተማሪዎቹ፣ እዚያው አካባቢ ካሉ ኪዮስኮችና ሱቆች አንድ ሃይላንድ የቀዘቀዘ የቧንቧ ውሃ በ3 ብር ገዝተው ነው የሚጠጡት፡፡ (መያዣውን በ1 ብር፣ ውሃውን በ2 ብር) ይኼ ለረዥም ጊዜ የቆየ ባህል ሆኗል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ት/ቤቱ መቼ እንደተሰራ አላውቅም፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን ታድሶ አያውቅም፡፡ አጥሩም ዘንድሮ ነው የተሰራው፡፡ አሁንም ስላላለቀና ከፊት ለፊት ክፍት ስለሆነ አጥር አለው ማለት አይቻልም፡፡ ባለፈው ጊዜ ተማሪዎቹ የሚቀርብልን ምግብ ትክክል አይደለም ብለው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ደረቅ እንጀራ ከከተማ እየቀረበ ነበር የሚመገቡት፡፡ አቅራቢዎች በክሬዲት ያቀርቡ ስለነበር በመሃል አስተዳደሩ ተቀየረ፤ ገንዘባቸውን ሳይቀበሉ፡፡ አሁን ሰዎቹ ክስ እንደመሰረቱና እስካሁንም ሂሳባቸው እንዳልተከፈላቸው አውቃለሁ በማለት ስለ ዲላው “ሰመራ” ዩኒቨርሲቲ የሚያውቁትን ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍል በዩኒቨርሲቲው ቀርቶ በእስር ቤትም ይኖራል ብዬ ስላልገመትኩ፣ ልጄ ወደተመደበችበት ክፍል ስገባ በጣም ነው የደነገጥኩት ያሉት፤ የዘመድና የራሳቸውን ሴት ልጆች ይዘው የሄዱት የአዲስ አበባ ነዋሪ አባት ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ልጄ ወደ ተመደበችበት ህንፃ ኃላፊ (ፕሮክተር) ቢሮ ሄደን የተመደበችበትን ክፍል ጠየቅን፡፡ ፕሮክተሯ ነረገችንና፤ ግን መግባት አትችሉም አለችን፡፡ “አሁን ለሌላ አገልግሎት ውሏል”፡፡ ስትለን “እናንተ ምን ሆናችሁ ነው ሳትዘጋጁ የጠራችሁን” አልኳት፡፡ “አይ፤ ለዛሬ ሌላ ክፍል ይደሩና ነገ ይመደባሉ” አለች፡፡ “የት ነው የምንመደበው?” “አይታወቅም” ዕቃችንን እሷው ክፍል አስቀምጠን፣ በማግስቱ የተሰጠንን ክፍል ገባ ብለን ስናይ፣ በጣም ደነገጥን፡፡

የጭቃው ክምር ዩኒቨርሲቲ አይደለም… ምን ብዬ እንደምናገር አላውቅም፡፡ ኮብልስቶን የለበሰው የግቢው ዋነኛ መንገድ ጭቃና ክፍል ውስጥ ያለው ተመሳሳይ ስለሆነ እንቢ አልን፡፡ ከሰዓት በኋላ ስንሄድ የተሰጠንን ክፍል ጠርገን ለመግባት፣ ውስጡ ያለው ቆሻሻ በፍፁም የሚያስገባ አልነበረም፡፡ መስኮቱ አይከፈት፣ የአልጋው ፍራሽ የበሰበሰ፣ የለበሰው ጨርቅ የተቀደደ፣ ሁሉም ነገር የሚሆን ስላልሆነ፣ ተስፋ ቆርጬ ልጄን ይዤ ልመለስ ነበር፡፡ ልጄ ናት ምናልባት ይሻሻል ይሆናል፤ እስቲ እንሞክረው ብላ ያበረታታችኝ፡፡ እሺ! ይሁን ብዬ ሽንት ቤቱን እንዲያሳዩን ጠየቅሁ፡፡ ሽንት ቤት የለም፣ ስለሞላ ተቆልፏል፡፡ ጠይቄ እንደተረዳሁት ከህንፃው ውጭ በቆርቆሮ የተሰራ ሽንት ቤት አለ፡፡ እሱም‘ኮ ሞልቶ ለእግር መርገጫ ቦታ የለም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ወንዶችሽ ይሁን ጫካ ውስጥም ሊፀዳዱ ይችላሉ፡፡ እንዴት ነው ቀሚስ የለበሰች ሴት ልጅ ከዶርሟ 700 ሜትር ያህል ርቃ ጫካ ውስጥ የምትፀዳዳው? ግራ የሚያገባ ነው፡፡ ውሃ የለም፡፡ ክፍሉን ለማጽዳት ከከተማ ውሃ በጀሪካን ባመጣ፣ በርካታ ሴቶች “በዚህ ጭቃ እንዴት አንሶላ ውስጥ እንገባለን? እባክዎትን ውሃውን ይስጡንና እግራችንን እንታጠብበት” ሲሉኝ፣ ሰጠኋቸውና ለእነሱም አልበቃም፡፡ ውሃና ሽንት ቤት፣ የቅንጦት ሳይሆኑ ለሕይወት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ በልቶ መፀዳዳት፣ የተፈጥሮ ግዴታ ነው፡፡

ይቅርብኝ ብለህ በሌላ ነገር የምትተካው አይደለም፡፡ ያለ ውሃም መኖር አንችልም፡፡ የምንበላውና የምንጠጣው፣ የግል፣ የልብስ፣ የቤት፣ የአካባቢ ንፅህና … የምንጠብቀው በውሃ ነው፡፡ በአጠቃላይ ህይወታችን በውሃ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ካላሟላ፣ በእውነት ምን እየሰራ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ስለ ውሃ ችግር ስናገር የሰሙ ሰዎች ብዙ ስጋት አይግባህ፣ ከዩኒቨርሲቲው ፊት - ለፊት ያሉ ቤቶች የሴቶቹን ችግር ስለሚያውቁ ለመፀዳጃ የሚሆን ውሃ በ3 ብር እየሸጡላቸው ነው አሉኝ፡፡ ወላጅ ታዲያ በየቀኑ የመፀዳጃ ውሃ በ3 ብር እየገዛ እንዴት ይችላል? አገር የሚመሩና የሚያስተዳድሩ ባለሙያዎች ያፈራል፤ የህብረተሰብን ችግር ይፈታል፣ የማህበረሰቡን ዕድገት፣ ባህል፣ ኢኮኖሚ፣… ያሳድጋል፣ ይመራል፣… የተባለ ዩኒቨርሲቲ፤ ራሱን ማስተዳደር ካልቻለ መጨረሻው ምን ይሆናል? ተማሪዎች እየተማረሩ ሰልፍ ሲወጡ፣ መንግስት የፀረ-ሽብር ኃይሎች የፈጠሩት ሴራ ነው ማለቱን ትቶ፣ ችግሮቹ የሚቀረፉበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፡፡ የከተማው አስተዳደር ዩኒቨርሲቲውን የሚፈልገው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊና ዋነኛ በሆኑ ችግሮች ተተብትቦ እያየ፣ ለመቅረፍ አንዳች ጥረት አላደረገም ባይ ነኝ፡፡ ይህን የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ምንም ቤቶች በሌሉበትና ሰዎች በማይጠቀሙበት ከከተማው ጀርባ ባለ ስፍራ ብዙ ሚሊዮን ብሮችን አውጥቶ፣ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ከመስራቱም ሌላ ግራና ቀኝ የመንገድ መብራት ተክሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያለው ዲላ ከተማ መግቢያ ላይ ነው፡፡

በዚህ ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ የሚመደቡት ከመላው ሀገሪቱ ብሔር ብሄረሰቦች የሚመጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ ወላጆች መምህራን፣ ቱሪስቶች፣ እንግዶች፣… የሚሄዱበት ትንሽ ርቀት ያለውን መንገድ ትቶ አገልግሎት የማይሰጥ መንገድ መገንባቱ ምን ይባላል? ተማሪዎች የከተማዋንና የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንደሚያንቀሳቅሱ ስለሚታወቅ በሌሎች አካባቢዎች ሕዝቡ ዩኒቨርሲቲ ይከፈትልን እያለ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል፡፡ መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚታየው ዕድገት የተመጣጠነ እንዲሆን፤ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ስርፀት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ለማጎልበት፣ በዞኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢያቋቁምም የዲላ ከተማ አስተዳደር ግን ትኩረት አልሰጠውም፡፡ ይሄ የመንግስትን የትምህርት ፖሊሲም እንደመቃወም ይቆጠራል፡፡ ብለዋል፤ ከአዲስ አበባ የመጡት አባት፡፡ የተሰጠን ክፍል መብራት፣ ውሃ፣ ሽንት ቤት፣ ሻወር የለውም ያለችው ከእህቷ ጋር ከባህርዳር ከተማ የመጣች ወጣት ናት፡፡ ክፍሉ ውስጥ ገብተን ያረፍነው በሞባይል ባትሪ ነው፡፡ በሩ ቁልፍ የለውም፤ አልጋው የተሰባበረ፣ የስፖንጁ ልባስ የተቀዳደደ፣ መስኮትም የሌለው፣ በጭቃ የተሞላ፣ የተዘጋው ሽንት ቤት በጣም የሚሸት፣ የኮሪደሩ ጭቃ ሻንጣ የማያስብ፣ ሳጥናቸው የተሰባበረና ቁልፍ የሌለው ስለሆነ፣ ቁልፍ ገዝቼ በምስማር መትቼላቸው ነው የመጣሁት፡፡ ችግሩ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ቀርቶ የአንድ አርሶ አደር መፀዳጃ ቤት አይመስልም፡፡ እኛ የአርሶ አደር ልጆች ነን፡፡ ሽንት ቤት ተጠቅመን ስንወጣ ደጅ ላይ እጃችንን የምንታጠብበት ውሃና ሳሙና አለን፡፡ የገላ ንፅህና መጠበቂያ ሻወር ሳይቀር እየሰራን ነው፡፡ እዚህ ግን ፊትና እጅ ለመታጠብ ውሃ የለውም፡፡ ልብስ የት ነው የሚታጠበው ብለን ስንጠይቅ፣ በጀሪካን 10 ሊትር ውሃ ገዝተው ዶርማቸው አጠገብ በጎማ ላይ ያጥባሉ አሉን፡፡ ግቢው ውስጥ ማጠቢያ ገንዳ የለም፡፡ እህቴማ በዚህ አይነት እንዴት እማራለሁ? ካንቺ ጋር ልመለስ ብላኝ ነበር፡፡ እኔ ‹አይዞሽ! ይሻሻል ይሆናል፤ ትንሽ ቆይተሽ እይው› አልኳት፤ በማለት ገልጻለች፡፡ ልጄ ዩኒቨርሲቲ ገባች ሲባል በጣም ደስ አለኝ፤ ከአዲስ አበባ ውጭ መመደቧን ስሰማም፣ የምትሄድበትን አካባቢ ባህልና የሕዝቡን አኗኗር ታውቃለች፤ ዩኒቨርሲቲውም ዘመናዊ ይሆናል በማለት ደስ ብሎኝ ልጄን ይዤ ወደ ዲላ ሄድኩ፡፡

ዩኒቨርሲቲው አጥር እንደሌለው ሳይ፣ ግምቴ ሁሉ ከንቱ ሆነ ያሉት ሌላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወላጅ ናቸው፡፡ እኔ የገጠር ልጅ ነኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲውን ሳይ፣ ከብቶች ቀረጥ የሚቀረጡበት በረት መስሎ ስለታየኝ በጣም አዘንኩ፡፡ ወደ ውስጥ ገብቼ የተሰጣትን ክፍል ሳይ፣ ‹ልጄ እዚህ ውስጥ ነው የምትኖረው?› በማለት ዘገነነኝ፡፡ ለአራት ተማሪዎች የተሰጠው ክፍል መፈናፈኛ የሌለው ጠባብ፣ (የፕሮክተሮች ኃላፊ አዲስ ተማሪዎች እየመጡ ስለሆነ እንደምንም አድርጋችሁ በየክፍሉ አንድ አንድ አልጋ ጨምሩ ማለቱን እንደሰሙ አንድ ወላጅ ተናግረዋል) ትኋን የተባለው ተባይ በየአልጋውና ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ይታያል፡፡ የወለሉ አቧራ ደግሞ አይጣል ነው፡፡ ገና ስንረግጠው እየቦነነ ያስነጥሰን ጀመር፡፡ አቧራ ውስጥ የምታድግና ቁንጫ የመሰለች ሙጃሌ የምትባል ተባይ አለች፡፡ ይቺ ተባይ እግር ጣቶች ውስጥ ሰርስራ በመግባት፣ አድጋ እንቁላሏን እስክትጥል ድረስ በጣም ታሳክካለች፡፡ ልጆቹ ትምህርት ይማሩ ወይስ? እሷን ይከኩ? ግራ የገባ ነገር‘ኮ ነው፡፡ በጣም እያዘንኩ ነው ልጄን ጥያት የመጣሁት፡፡ የአቅም ጉዳይ ሆኖብኝ ነው እንጂ ከዚያ አውጥቼያት ሌላ ቦታ አስተምራት ነበር፡፡ ልጄ ዩኒቨርሲቲ ሳይሆን በረት ነው የገባችው፡፡ አንድ ልጇን ይዛ የሄደች እናት፣ የልጇን ክፍል አይታ በጣም አዘነችና፣ እኔ ት/ቤቱ ቢፈቅድልኝ የልጄን ክፍል፣ የተሰባበሩትን ቁሳቁሶች አስቀይሬ፣ ቀለም አስቀብቼ አስተካክል ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን የልጄን ዶርም ጉዳይ ሳላስተካክል እንዲሁ አቧራ ውስጥ ጥያት አልሄድም ስትል ሰምቻለሁ፤ በማለት ገልፀዋል፡፡ የሕንፃዎቹ ውስጣዊ ገፅታ ሲታይ የተደረደረው ብሎኬት ቫርኒሽ ከመቀባቱ በስተቀር አልተለሰነም፣ ቀለም አልተቀባም ብለዋል ሌላ ወላጅ፡፡ እንዴት ነው እዚያ ጉረኖ ውስጥ ሆነውና ተምረው ውጤታማ የሚሆኑት? ቀለም‘ኮ የሚቀባው ለውበትና ለቅንጦት ብቻ አይደለም፡፡ ቀለም፣ በርካታ የተለያዩ ሥነ-ልቦናዊ ጥቅሞች እንዳለው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና የቀለም ጥበብ ኢንጂነሮች ይናገራሉ፡፡ የሆስፒታልና የት/ቤት ክፍሎች በዘፈቀደ አይደለም ቀለም የሚቀቡት፡፡ ሆስፒታሎች የበሽተኛውን አዕምሮ የማይረብሹ፣ የማያስጨንቁና እንዲረጋጉ የሚያደርግ … ቀለም ነው የሚቀቡት፡፡ ት/ቤቶች የሚቀቡትም ቀለም የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያሻሽሉ፣ የተማሪውን የትምህርት አቀባበል የሚያጎለብቱ… መሆን አለባቸው፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ግን እንኳን ቀለም ልስን አያውቀውም፡፡ ገና እንደተሰራ ቢሆን ተማሪዎችን ለመቀበል ቸኩለው ይሆናል በሚል ምንም አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ አንድ ሁለት ዓመት መታገስም ይቻላል፡፡ በሰባትና በስምንት ዓመት ግን እንዴት አይስተካከልም? የሚለው መመለስ አለበት፡፡

መጀመሪያ ላይ መንግስት አቅም አንሶት ከሆነም ምንም አይደለም፤ መቀበል ይቻላል፡፡ ከዚሁ ሁሉ ዓመት በኋላ ግን ከባድ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች አይደሉም፡፡ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስርፀት ማዕከል ናቸው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለመማር ማስተማሩ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓይነት ይዞ በአገሪቷ ይህን ያህል ዩኒቨርሲቲዎች አሉ ማለት ከስታቲስቲክስነት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ የተጀመረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲሳካና ለወደፊቱም የአገሪቷ ቀጣይ ዕድገት ሲባል፣ መንግስት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ፣ በሪፖርት ሳይሆን በአካል ሄዶ አይቶ የተጓደሉ የተማሪውን ጥያቄዎች መመለስ፣ በከተማው አስተዳደርና በዩኒቨርሲቲው መካከል ያለውን ግንኙነት (ጥሩ እንዳልሆነ ይነገራልና) በጥልቀት መርምሮ መፍትሄ ማበጀት አለበት እላለሁ፡፡ የተማሪ ወላጆች ባነሱት ቅሬታ ላይ ዩኒቨረሲቲ ምላሽ እንዲሰጠን በሁለት የስልክ መስመሮች ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

Read 9632 times