Saturday, 11 October 2014 13:35

የአሜሪካዊያን አማካይ የህይወት ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       በአሜሪካ አማካይ የህይወት ዘመን እ.ኤ.አ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መጨመር በማሳየት ወደ 78.8 ዓመት እንደደረሰ ኸልዝ ዴይ የአገሪቱ የፌደራል ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሰሞኑን ዘገበ፡፡ የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ በአገሪቱ አማካይ የህይወት ዘመን ሊጨምር የቻለው ዜጎች ወደ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመመለሳቸው ነው፡፡ “አሜሪካውያን ረዥም ዕድሜ እየኖሩ ሲሆን፣ ዘላቂ በሽታዎችን አስቀድሞ ስለመከላከል የተሻለ ግንዛቤ ጨብጠዋል” ብለዋል፤ የጥናት ሪፖርቱ ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ጂያኩዋን ዙ፡፡ “በህይወት የመቆያ አማካይ ዕድሜ የጨመረው ሰዎች ጤናማ ምግብ ስለሚመገቡና የአካል እንቅስቃሴ ስለሚሰሩ ነው” ብለዋል ዶክተሩ፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ሴቶች ከወንዶች የበለጠ በህይወት የመቆየት አማካይ ዕድሜ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የተወለዱ የሴቶች በህይወት የመቆያ አማካይ እድሜ 81 ዓመት ሲሆን የወንዶች 76 እንደሆነ የሪፖርቱ አዘጋጅ ዶ/ር ዙ ተናግረዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የነበሩ ሴቶች ተጨማሪ 20 ዓመት ገደማ ይኖራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ወንዶች ደግሞ 18 ዓመት ይኖራሉ ተብሏል፡፡ በሪፖርቱ መሰረት፤ ከ2011 እስከ 2012 ባለው ጊዜ በአሜሪካ የሞት መጠን ከ1 በመቶ በላይ መቀነስ አሳይቷል፡፡ ለሞት የሚዳርጉ ዋና መንስኤዎች በሚል የሚታወቁት ነገሮች አሁንም አልተለወጡም ተብሏል፡፡ በ2012 ዓ.ም 75 በመቶ ገደማ የሚሆነው ሞት የተከሰተው በልብ ህመም፣ በካንሰር፤ ዘላቂ በሆነ የታችኛው የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች፣ በስትሮክ፣ በድንገተኛ ጉዳቶች፣ በመርሳት በሽታ፣ በስኳር፣ በኢንፍሉዌንዛና በሳንባ ምች፣ እንዲሁም በኩላሊት በሽታ እና ራስን በማጥፋት እንደነበር ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ከአስሩ ቀዳሚ የሞት መንስኤዎች በስምንቱ ላይ የሞት መጠን ከፍተኛ መቀነስ እንዳሳየ የሲዲሲ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ምክንያቱ ባይታወቅም ራስን ማጥፋት በ2012 ዓ.ም ከቀደመው ዓመት በ2.4 በመቶ እንደጨመረ ዶ/ር ዙ ተናግረዋል፡፡

በኒውዮርክ ሲቲ ሌኖክስ ሂል ሆስፒታል ውስጥ የልብ ህመምን በመከላከል ላይ የሚሰሩት ዶ/ር ሱዛኔ ስቴይንባም፤ “ዋናዎቹ የሞት መንስኤዎች የአኗኗር ዘይቤን ተከትለው የሚመጡ ናቸው፡፡ በመከላከልና በህክምና ረገድ የተሻለ ሥራ እያከናወንን ነው” ብለዋል፡፡ የተሻለ ምግብ መመገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተርና ሲጋራ ማጨስ ማቆም ጤንነትን ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃዎች እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡በህይወት የመቆያ አማካይ እድሜ እንዲሻሻል ወይም እንዲጨምር የሚያደርገው ግን የተሻለ የህክምና ክብካቤ መኖር ነው ይላሉ - ዶ/ር ሱዛኔ፡፡ “በአብዛኞቹ የተለመዱት የሞት መንስኤዎች በአኗኗር ምርጫችን የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው” የሚሉት የህክምና ባለሞያዋ፤ አመጋገባችንንም ሆነ የአካል እንቅስቃሴያችንን ከተቆጣጠርን ብዙዎቹን ዋነኛ የሞት መንስኤዎች መከላከል እንችላለን” በማለት ያስረዳሉ፡፡ “‹ህክምና - ተኮር› ከመሆን ይልቅ ‹መከላከል - ተኮር› ብንሆን የህይወት ዘመንን በእጅጉ ማርዘም ይቻላል” ብለዋል፤ ዶ/ር ሱዛኔ ስቴይንባም፡፡

Read 2545 times