Saturday, 11 October 2014 15:43

የኬንያው ፕሬዚዳንት በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት ቀረቡ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

           የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሰባት አመታት በፊት በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በአገሪቱ ከተቀሰቀሰውና ከ1ሺህ 200 በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት፣ 600 ሺህ ያህሉን ደግሞ ለመፈናቀል ከዳረገው የእርስ በርስ ግጭት ጋር በተያያዘ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት የተመሰረተባቸውን ክስ ባለፈው ረቡዕ በፍ/ቤቱ ቀርበው አደመጡ፡፡
በስልጣን ላይ እያሉ በአለማቀፉ ፍርድ ቤት የቀረበባቸውን ክስ ለማድመጥ በፈቃደኝነት የተገኙ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ዘ ሄግ በሚገኘው ፍ/ቤት በተዘጋጀው የቅድመ ፍርድ ሂደት ውይይት ላይ ተገኝተው የተመሰረቱባቸውን አምስት የወንጀል ክሶች ያደመጡ ሲሆን፣ ወንጀሎቹን አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“የተመሰረቱብኝ ክሶች ከፖለቲካዊ ጥቅም ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ክሶቹ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል” ብለዋል ምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን በቦታቸው ወክለው፣ ክሱን ለማድመጥ ወደ ፍርድ ቤቱ የሄዱት ኬንያታ በሰጡት ምላሽ፡፡
በ2007 የኬንያ የምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በአገሪቱ በተከሰተው ግጭት ውስጥ እጃቸው አለበት፣ ሰብዓዊ መብቶችን በሚጥሱ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል በሚል በቀረቡባቸው አምስት ክሶች፣ የሚሊሺያ ወታደሮችን በገንዘብ በመደገፍ ለጥቃት አነሳስተዋል፤ ጉዳያቸው በመደበኛ ፍርድ ሂደት ይታይ አይታይ የሚለው  ሐሙስ የሚወሰን ይሆናል፡፡በዕለቱ አቃቤ ህግ፤ የኬንያ መንግስት በፕሬዚዳንቱ ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁልፍ ማስረጃዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም በሚል ቢወነጅልም፣ ኬንያዊው ጠበቃ ጊቱ ሙጋይ ግን  ውንጀላውን አልተቀበሉትም፡፡ ፍርድ ቤቱ በቂ ማስረጃ ካላገኘ፣ ክሶቹ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ወንጀሎቹ  በፕሬዚዳንቱ መፈጸማቸውን የሚያረጋግጡ የስልክ ማስረጃዎችና ዘጠኝ ምስክሮች እንዳሉት አስታውቋል፡፡ፍርድ ቤቱ በኡሁሩ ኬንያታ ላይ የተመሰረተውን ክስ ውድቅ ማድረጉን አልያም የፍርድ ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት ሰሞኑን ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ በስልጣን ላይ እያሉ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ሌላው መሪ፣ የሱዳኑ ኦማር አልበሽር እንደሆኑ ያስታወሰው ዘገባው፤ በዳርፉር በተከሰቱ የጦርነት ወንጀሎች ተከስሰው  ፍርድ ቤቱ ያወጣባቸውን የእስር ትዕዛዝ አልቀበልም ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡በፍርድ ቤቱ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ባለፈው ሃሙስ ወደ አገራቸው የተመለሱት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ናይሮቢ በሚገኘው አየር ማረፊያ ሲደርሱ በባህላዊ ጭፈራና የወታደራዊ ማርሽ የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ከአየር ማረፊያ እስከተማዋ ማዕከላዊ አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውም ለፕሬዚዳንታቸው ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡
“አንድ ነን!... ኬንያ የተረጋጋች አገር ስለሆነች ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም!” ብለዋል ኬንያታ ለህዝቡ ባሰሙት አጭር ንግግር፡፡

Read 2581 times