Saturday, 11 October 2014 15:46

የአፍታ ቆይታ ከ”ለዛ” የሬዲዮ አዘጋጅ ጋር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

                 የሙዚቃና የፊልም ባለሙያዎችን አወዳድሮ የሚሸልመው የ”ለዛ” ፕሮግራም መቼና እንዴት ተጀመረ?
ፕሮግራሙ ከተጀመረ አራት አመት ሆኖታል፡፡ የ“ለዛ” ፕሮግራም በተለይ የሀሙስ የምሳ ሰዓት ዝግጅት በኢትዮጵያ ስራዎች ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ደረጃቸውን የጠበቁ የኢትዮጵያ ሙዚዎችን እየመረጥን እናስተላልፋለን፡፡ የዛሬ አራት አመት ሁሉ ነገር ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ የወጡት አልበሞች ትንሽ ነበሩ፡፡ እኛም ፕሮግራማችን ላይ የምንሰማው አዲስ ስራ አጣን፡፡ አርቲስቶቹ ከስራቸው የሚያገኙት ገቢ ባያስደስታቸውም፣ የኮፒራይት ጉዳይ ፈር ባይዝም፣ የሰሩትን ስራ አድማጩ “ጥሩ ነው” ብሎ ሲመርጠው ይበረታቱ ይሆናል በሚል ነው ሽልማቱ የተጀመረው፡፡ ሰርፀ ፍሬስብሐትና ያሬድ ሹመቴ፤ በብሄራዊ ቴያትር ከሚያዘጋጁት ፕሮግራም ጋር ለምን አይደረግም ብለው ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት የመጀመርያው የሽልማት ፕሮግራም እዚያው ተደረገ፡፡ ሁለተኛውን በእምቢልታ ሲኒማ፣ ሶስተኛውን በጃዝ አምባና አራተኛውን የዛሬ ሳምንት በጣሊያን የባህል ተቋም አድርገናል፡፡
ፕሮግራሙ አላማውን አሳክቷል ትላለህ?
አዎ! የሰው ተሳትፎ በጣም ጨምሯል፤ ከመጀመሪያው በስተቀር የሌሎቹ ምርጫው የተከናወነው በኢንተርኔት ነው፡፡ በየእለቱ መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ዘንድሮ በያሁ ዶት ኮምና በሸገር ዌብሳይት ላይ ነው ድምፅ የተሰጠው፡፡ በሸገር ዌብሳይት ላይ ብቻ የተሰጠው ድምፅ ከ60ሺ በላይ ነው፡፡ ማን ከየት ሀገር ማንን እንደመረጠ ማየት ይቻላል፡፡
ተወዳዳሪዎችም ምን ያህል ድምፅ እንዳገኙ ያዩታል፡፡ በዚህ በአራተኛው ዙር ከበፊቶቹ ዙሮች በተለየ ከህዝብ ድምፅ በተጨማሪ የባለሙያዎች ግምገማም እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ስራዎች ህዝብ ስለወደዳቸው ብቻ ሳይሆን ኪነ-ጥበባዊ ፋይዳቸውም እንዲታይ በማለት ለህዝብ ድምፅ 60 በመቶ፣ ለባለሙያ ድምፅ 40 በመቶ ተደርጓል፡፡
የፐርሰንት ስሌቱ እንዴት ተሰራ?
ፕሮግራሙ ሲጀመር የአድማጮች ምርጫ ስለተባለ፣ አብላጫውን ለህዝብ ለመስጠት ሲባል 60 በመቶ ለህዝብ ድምፅ ሲሆን 40 በመቶው ለባለሙያ ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ትልቁ ክርክር ምን መሰለሽ? ህዝቡን መምራት ያለበትና ኪነ-ጥበባዊ ስራዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የመገምገም የመሪነቱን ሚና መጫወት ያለበት ባለሙያው ነው የሚል ነው፡፡
መስፈርቱ ምን ነበር?
 መስፈርቱ ግልፅ ነው፡፡ የሙዚቃ ስራዎችን ለመገምገም የሚችሉ ከበቂ በላይ ሙያተኞች አሉን፡፡ የፊልም ጥበብ ስራ ላይ ግን ገና ይቀረናል፡፡ ስራዎችን የሚገመግሙ በቂ ሙያተኞች የሉም፡፡ እንግዲህ በአገር ዳኛ ነው የሚዳኘው፡፡
በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ምንድን ናቸው?
ፕሮግራሙን ተረድቶት ላለፉት ዓመታት በብቸኝነት የረዳን “አኳ አዲስ” ነው፡፡ በጣም የሚገርመኝ የቢራ ፋብሪካዎች አልበም ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ ስፖንሰር ያደረጓቸው አልበሞች በዚህ ውድድር ሲሳተፉ እያዩ፣ ይህን የውድድር መንፈስ ለማገዝ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ሌላው ችግር ፕሮግራሙ የሚዘጋጅበት ቦታ ማግኘት ነው፡፡ ብቸኛው ጥሩ አዳራሽ ብሔራዊ ትያትር ነው፤ ነገር ግን ነፃ የሚሆነው ሰኞ ብቻ ነው፡፡
የጣልያን የባህል ተቋም አዳራሽ ሰፊ ነው፤ ግራንድ ፒያኖና ብዙ ሰው የሚያስተናግድ ግቢ አለው፡፡ ይህንን የሚያሟላ ቦታ ለማግኘት ብዙ ምርጫ የለንም፡፡ መድረኩን እንደ አዲስ ነው የሰራነው፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ገቢ አለው?
የለውም፤ እንዲያውም ከኪስ ያስወጣል፡፡ ፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች ላይ የሚታዩ ስፖንሰሮች ገንዘብ ሳይሆን የሚሰጡት ወጪዎችን ነው የሚችሉት፡፡ አንዱ የአዳራሽ ኪራይ ሲችል ሌላው የጥሪ ካርድ፣ ሌላው ውሃ፣ ሌላኛው ምግብ ያቀርባል፡፡ በዚያ መልክ ነው የዝግጅቱ ወጪ የሚሸፈነው፡፡
በአሸናፊዎቹ ምርጫ ላይ ቅሬታ ቀርቦ ያውቃል?
በፍፁም! ተወዳዳሪ ሁሉ በእርግጥ ማሸነፍ ይፈልጋል፤ ነገር ግን የድምፅ አሰጣጡ ሂደት መቶ በመቶ ግልፅ ነው፡፡ የተገኘው ድምፅ በግልፅ ይቀመጣል፡፡ እንዲያውም “አንተ አሪፍ ነው ያልከው ስራ አሸንፏል ወይ” ብትይኝ መልሴ አይደለም ነው፤ እኔ ጥሩ ያልኳቸው ያልተሸለሙ አሉ፤ ጥሩ አይደሉም ያልኳቸው የተሸለሙ አሉ፡፡
የውድድር ዘርፎቹ እንዴት ናቸው?
በአመት ውስጥ ምን ያህል የባህል ዘፈን ይወጣል? ምን ያህል ስራዎች በሙዚቃ ስልት ለመመደብ የተመቹ ናቸው ስትይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ አልበም ውስጥ የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶች አሉ፤ ስለዚህ ለምደባ አስቸጋሪ የሚሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ዜማና ግጥም የሚል ምድብ ለመጨመር እየታሰበ ነው፤ ዘንድሮ “ምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ”፣ “አዲስ ድምፃዊ” እና “የህይወት ዘመን ተሸላሚ” የሚሉ ምድቦች ተካትተዋል፡፡
 በፊልም “ምርጥ ሳውንድ ትራክ” የሚል ምድብ ለመጨመር ታስቦ ምን ያህል ናቸው ኦርጂናል ሳውንድ ትራክ የሚጠቀሙት የሚለው ተገምግሞ ውድቅ ሆኗል፡፡  

Read 2740 times