Monday, 13 October 2014 07:58

“ተምሳሌት” የስኬታማ ሴቶች መፅሐፍ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ ስኬታማ ሴቶችን ታሪክ የሚዘክረውና ለዝግጅት 3 ዓመት ገደማ የፈጀው “ተምሳሌት፣ እፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” የተሰኘው መፅሃፍ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ተመረቀ፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት አሳታሚነት፣ በአሜሪካዊቷ ሜሪ ጄን ዋግል ተዘጋጅቶ፣ በጋዜጠኛ ኢዮብ ካሣ የተተረጐመው መፅሃፉ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ከጥንት ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ የተጫወቱትን ጉልህ ሚና የሚዘክር ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው አንፀባራቂ ውጤት ያስመዘገቡ የ64 ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ታሪክ አካትቷል፡፡
በጋዜጠኝነት፣ በህግ፣ በንግድ፣ በህክምና፣ በግብርና፣ በኪነጥበብ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በግንባታ ሙያ፣ በበጐ አድራጐት፣ በአመራር እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ለስኬት የበቁ እንስቶች የተካተቱበት መፅሃፉ፤ 298 ገፆች ያሉት ሲሆን በላቀ ጥራትና በማራኪ ዲዛይን ተዘጋጅቶ እንደታተመና 30 ሺህ ኮፒ ለት/ቤቶች፣ ለቤተመፃህፍትና የልጃገረዶችና ወጣት ሴቶችን አቅም በማጐልበት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች በነፃ እንደሚከፋፈል ለማወቅ ተችሏል፡፡
“ተምሳሌት” ባለፈው ማክሰኞ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ ለህትመቱና ስርጭቱ ድጋፍ የሰጡ የአሜሪካና የአውሮፓ አምባሳደሮች እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ነው የተመረቀው፡፡ በምርቃቱ ሥነ-ስርዓት ላይ የመፅሃፉ አዘጋጅ ሜሪ ጄን ዋግል ከመፅሃፉ ባለታሪኮችና የበጐ ፈቃድ ሰራተኞች፣ በቪዲዮ የተቀናበረ ምስጋናና ውዳሴ ቀርቦላታል፡፡
“ለኢትዮጵያውያን ሴቶች ለሰጠሽው ክብርና ዕውቅና እናመሰግንሻለን” ብለዋታል - አመስጋኞቹ፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን የባለታሪኮቹን ፎቶግራፎች ላለፉት 2 ዓመታት ገደማ ስታነሳ የቆየችው ዓለምአቀፍ የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዋ አይዳ ሙሉነህ ያዘጋጀችው የስኬታማ እንስቶቹ የፎቶግራፍ አውደርዕይ ለታዳሚዎች ቀርቦ ከፍተኛ አድናቆት እንደተቸረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3993 times