Monday, 13 October 2014 08:10

“የላቀች ሴት” የክብር ሽልማት እጩዎች ታወቁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

         ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄደው “የላቀች ሴት” የክብር ሽልማት ሥነስርዓት በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ እንደሚያካሂድ አሶሴሽን ኦቭ ውሜን ኢን ቢዝነስ (ኤውብ) ገለፀ፡፡ ሰሞኑን ማህበሩ በሳሮማሪያ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ለዚህ የክብር ሽልማት የሚታጩ ሴቶችን ህዝቡ ከክልልም ሆነ ከአዲስ አበባ እንዲጠቁም  ከተደረገ  በኋላ፣ ሰባት ሴቶች ተመርጠው መታጨታቸውን ጠቁሟል፡፡
ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ የኬኢሞጂ ኢትዮጵያ መስራችና ዳይሬክተር፣ ወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባው የባህር ዳር አካዳሚ ትምህርት ቤት መስራችና ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ፕሮቨስት፣ ወ/ሮ ራሄል መኩሪያ በቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትምህርት በቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍል ዋና ሃላፊ እና የቀድሞ ወጣት ክርስቲያን ሴቶች ማህበር (ወሴክማ) የቦርድ ፕሬዚዳንት፣ አምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል የቀድሞ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር፣ አምባሳደር እና የሴቶች ልማት ፈንድ መስራችና ዳይሬክተር፣ ወ/ሮ ትርሃስ መዝገበ የሙዠዤዋግ ሎካ የሴቶች ልማት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር እና ወ/ሮ ዘሚ የኑስ የኒያ ፋውንዴሽን መስራችና ዳይሬክተር በእጩነት መቅረባቸውን ማህበሩ ይፋ አድርጓል፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ በሚደረገው የእራት ግብዣ ላይ አሸናፊዋ ሴት፣ የ2007 የኤውብ የላቀች ሴት ስያሜና የ100 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጣት የማህበሩ የወቅቱ ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሰብለ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ አሸናፊዋ የተሸለመችውን ብር በበጐ አድራጐት ለተሰማራና ላመነችበት ድርጅት በስጦታ የምታበረክት ሲሆን  አመቱን ሙሉ በአምባሳደርነት ካገለገለች በኋላ፣ ማዕረጓን ለ2008 ተሸላሚ ታበረክታለች ተብሏል፡፡ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በማካሄደው በዚህ የላቀች ሴት ሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የ2006 ዓ.ም የላቀች ሴት ተሸላሚ የነበሩት የኔክስት ዲዛይንና ሞዴሊንግ ት/ቤት መስራችና ባለቤት ወ/ሮ ሳራ መሃመድ ተገኝተው፣ በአምባሳደርነታቸው ያከናወኗቸውን ስራዎች ተናግረዋል፡፡ የተሸላሚዋ ሴት የምርጫ መስፈርት በትምህርትም ሆነ በስራ ለግሏ ማደግና መላቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እንዲያድጉ፣ እንዲሻሻሉና እንዲልቁ ያደረገችው አስተዋፅኦ በዋናነት ይታያል ተብሏል፡፡  

Read 2516 times