Monday, 20 October 2014 07:36

የጦማሪያኑና የጋዜጠኞቹ የፍ/ቤት ውሎ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግ ምላሽ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጥ የታዘዘው የማረሚያ ቤት ተወካይ አልቀረበም

አገሪቱን በሽብር ወንጀል ለማሸበርና ህጉንና ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል በሽብርተኝነት የተከሰሱት ሰባት ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞችን በሚመለከት ጠበቆቻቸው በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ በአቃቤ ህግ ምላሽ የተሰጠበት ሲሆን ምላሹን መርምሮ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤት ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሴት ተከሳሾች ኤዶም ካሳዬና ማህሌት ፋንታሁን በማረሚያ ቤት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት ቅሬታ አቅርበው የማረሚያ ቤት ተወካይ የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆነ ባለፈው ረቡዕ ግን የማረሚያ ቤት ተወካይ ፍ/ቤት ተገኝቶ አላስረዳም፡፡ ተወካዩ ለምን ቀርበው ምላሽ እንዳልሰጡ ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለፍ/ቤት እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አቃቤ ህግ የተከሳሽ ጠበቆች ላቀረቡት የክስ መቃወሚያ ባለሶስት ገፅ ምላሽ ለፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻችን በፀረ-ሽብር አዋጅ አንቀፅ ሶስት ከተጠቀሱት የሽብር ድርጊቶች አንዱንም ስላስፈፀሙ ክሱ ይሰረዝልን ያሉትን በተመለከተ፤ አቃቤ ህግ ክሱን ሲመሰርት በተከሳሾች ላይ የቀረበውን ማስረጃ ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ማገናዘቡን ጠቅሶ፣ በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም አንቀፅ ሶስት ላይ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በአንቀፅ አራት ላይ ማቀድ፣ ማሴር፣ በህቡዕ መደራጀት ምን ማለት እንደሆነ ከመዘርዘሩም በላይ ህገ-መንግስታዊ ስርአትን በኃይልና በአመፅ ለማስወገድ ስልጠናዎችን በአገር ውስጥና በውጭ የወሰዱ መሆናቸው፣ ከስልጠናው በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ የአመፅ ተግባሩ መቼ መታቀድ እንዳለበት፣ በህገ-መንግስቱና በስርዓቱ ላይ ያነጣጠረ የአመፅ ጥሪ ለመፈፀም በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበሩና እነዚህ ድርጊቶች የሽብርተኝነት ተግባራት በመሆናቸው ክሱ የሚሰረዝበት የህግ መሰረት የለም በማለት ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡
ጠበቆች የተከሳሾችን የመሰብሰብ፣ መደራጀትና ሃሳብን የመግለፅ መብት በተመለከተ የሕገ-መንግስቱን አንቀፅ 26፣29 እና 31 በመጥቀስ “የተከሳሾችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያላገናዘበና የሚጥስ” በማለት ያቀረቡትን መቃወሚያ በተመለከተም አቃቤ ህግ የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 29/6 እና 7 በመጥቀስ የህፃናት፣ ወጣቶችንና አገር ደህንነትን በሚመለከት በልዩ ሁኔታ ሊገደብ እንደሚችል አመልክቶ፣ ተከሳሾች ይሄን ሽፋን በማድረግ ህገ መንግስቱን ለመናድ የአመፅ ጥሪ ለማድረግ ሲያቅዱና ሲያሴሩ የነበሩ በመሆናቸው ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም በማለት የጠበቆች መቃወሚያ ተቀባይነት እንደሌለው ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡
አቃቤ ህግ በጠበቆቹ ከቀረቡት የክስ መቃወሚያዎች ውስጥ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርአት ህግ አንቀፅ 111ን በመጥቀስ ቡድን፣ ድርጅት ስልጠና እና ህቡዕ በማለት የተጠቀሰው ግልፅ አለመሆኑንና ክሱን ለመከላከል አያስችልም ሲሉ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ በተመለከተም አቃቤ ህግ የተከሳሾችን የወንጀል ተሳትፎ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርአት ህግ አንቀፅ 111 እና 112 መሰረት ያቀረበ መሆኑን ጠቅሶ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡት መቃወሚያ ህጋዊ መሰረት የለውም ብሏል - ለፍ/ቤቱ ባቀረበው ምላሽ፡፡
ፍ/ቤቱ የክስ መቃወሚያውን ከአቃቤ ህግ ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠትና ማረሚያ ቤቱ የሴት እስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ለምን ተወካዩን ልኮ ምላሽ እንዳልሰጠ እንዲያስረዳ ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የተከሳሽ ጠበቆች አቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለ25 መቀጠሩን ተቀብለው፣ የሴት እስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥ ለጥቅምት 25 መቀጠሩ የራቀ በመሆኑ ቀጠሮው እንዲያጥር ጠይቀዋል፡፡
ፍ/ቤቱም፤ ሁለቱንም በ25 የቀጠርነው እንዳይመላለሱ ብለን ነው በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን ዘጠነኛ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ “እኛ ሽብርተኛ እየተባልን መገለልና አድልኦ እየደረሰብን ነው፤ የሚጠይቀን ቤተሰብና የምንጠየቅበት ሰዓትም ተገድቧል” ስትል በማስረዳት፣ ባለፈው ጊዜ ይህንኑ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ለማግኘት አንድ ወር ከ26 ቀን እንደወሰደና አሁንም ለጥቅምት 25 መቀጠሩ በጣም እንደራቀ በመጥቀስ ቀጠሮው እንዲያጥር ፍ/ቤቱን ጠይቃለች፡፡
ፍ/ቤቱም የጠበቆችንና የተከሳሿን ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት ማረሚያ ቤቱ ለጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ያዘዘ ሲሆን አቃቤ ህግ በክስ መቃወሚያው ላይ የሰጠውን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ደግሞ ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡    

Read 2222 times