Monday, 20 October 2014 07:47

ፕ/ር መስፍን በአውስትራሊያ የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት ይቀበላሉ

Written by 
Rate this item
(24 votes)

        ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ተቀማጭነቱ በአውስትራሊያ የሆነው ‘ዲሞክራሲ ፎር ኢትዮጵያ ሰፖርት ግሩፕ’ የተሰኘ ቡድን ያዘጋጀውን የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት ለመቀበል ሰሞኑን ወደ አውስትራሊያ መሄዳቸውን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማስቻል ለረጅም አመታት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ያለው ቡድኑ፣ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት በማሰብ ሽልማቱን  እንዳበረከተላቸው አስታውቋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ሽልማቱን ከመቀበላቸው በተጨማሪ፣ ከነገ ጀምሮ በሚልቦርን፣ በሲድኒ፣ በብሪስባኔና በሌሎች የአውስትራሊያ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በሰብዓዊ መብቶች፣ በታሪክ፣ በጂኦግራፊና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ መጽሃፍትንና የጥናት ወረቀቶችን የጻፉትና ለረጅም አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተለያዩ የመንግስት ድርጅቶች ያገለገሉ ፕ/ር መስፍን፣ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መስራቾች አንዱ ሲሆኑ፣ ለተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካሪ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

Read 4487 times