Monday, 20 October 2014 07:48

መንግሥት የአሸባሪዎች የጥቃት ስጋት እንደሌለ አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“ኢቦላ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቷል የሚባለው ሃሰት ነው”

የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ክፍሉ ጠንካራና ህብረተሰቡን ያማከለ በመሆኑ ከአልሸባብም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ከሚደገፉ አሸባሪዎች ሊደርስ የሚችል ጥቃት እንደማይኖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋገጠ፡፡
ሰሞኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው አማካኝነት በቦሌ አካባቢ አልሸባብ ጥቃት ሊፈፅም እንደሚችል መረጃው ደርሶኛል በማለት ዜጐቹ በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በድረገፁ መልእክት ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በበኩላቸው፤ “የሀገሪቱ ፀጥታ የተጠናከረ ነው፤ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ስጋት አይግባው” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን ደህንነት የምንጠብቀው በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ የጥቃት ማስጠንቀቂያዎች አይደለም ያሉት አምባሳደሩ፤ የፀጥታ ሃይሉ የህብረተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት እለት ከእለት በጥንካሬ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለዲፕሎማቶችና ለአለማቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢቦላ ታማሚ እንደሌለ አረጋግጧል፡፡
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ-ገፆች ኢትዮጵያ ውስጥ በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል የኢቦላ ታካሚዎች አሉ በሚል የተሰራጩ መልእክቶች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡ ጥቆማዎች በስልክ መስመር 8335 ላይ እያስተናገደ መሆኑን የጠቆመው መስሪያ ቤቱ፤ የኢቦላ ታማሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገኝ እንደማይደበቅና ሀገሪቱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ ገልጿል፡፡
በሽታው ሀገር ውስጥ ቢገባ እንኳን በብቃት ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁሟል፡፡

Read 2234 times