Print this page
Monday, 20 October 2014 07:50

ኋላቀር ባህልና ቴክኖሎጂ ሲቀላቀል = የኢቦላ ወረርሽኝ

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(14 votes)

በአፍሪካና በአረብ አገራት ውስጥ፤ የአምባገነኖች አፈና፣ የአክራሪዎች ሽብር፣ የዘረኞች ግጭት፣ የበሽታዎች ወረርሽኝ የበረከተው አለምክንያት አይደለም - ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚመጥን ስልጡን ባህል ስለሌለን ነው።

         በአለም ዙሪያ የሚንቀለቀለው የአፈናና የሽብር፣ የግጭትና የበሽታ እሳት፣ ከድንበራችን ዘልቆ እስኪውጠን ድረስ፤ ድብብቆሽ እየተጫወትን ብንጠብቅ አያዋጣንም። “እቅጩን” ብንነጋገር ነው የሚሻለው። ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ፣ የአፍሪካና የአረብ ሰዎች በአብዛኛውና በአመዛኙ፣ ከጥንቱ ጭፍን አስተሳሰብና ከነባሩ ኋላቀር ባህል ለመላቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ገና ለስልጡን አኗኗር ብቁ አይደሉም። ለምሳሌ የስልጣኔ ውጤት የሆነውን የከተሜነት ኑሮ ተመልከቱ። አብዛኞቹ የአረብ ወይም የአፍሪካ ሰዎች፤ በገጠራማ መንደር እንጂ በሰፊ ከተማ ውስጥ የመኖር የሰብእና ብቃት የላቸውም - እንደ ኢቦላና ኤችአይቪ የበሽታ ወረርሽኝ በአፍሪካዊያን ላይ የሚበረታው ለምን ሆነና! የከተሜነትን ጥቅም ለመቋደስ የሚፍጨረጨሩት፤ ለከተሜነት የሚመጥን ስልጡን አስተሳሰብና ባህል በቅጡ ሳይጨብጡ ነው። “የዘልማድ” አስተሳሰብና “የይሉኝታ” ባህል፤ ለገጠር ኑሮ ቢመጥኑም እንኳ፤ “በሳይንስ” እና “በመርህ” ካልተተኩ በቀር፤ የሙጢኝ ብለን  ወደ ከተማ ስናስገባቸው ዋጋ ያጣሉ - የከተሜነት ትርፉ፤ “በዘፈቀደ” መደናበርና “በብዥታ” መንዘላዘል ይሆንና፤ የበሽታ ወረርሽኝ ይፈራረቅብናል።  
ሌሎች የስልጣኔ ውጤቶችንም መጥቀስ ይቻላል - የመገናኛና የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን። ብዙዎቹ የአፍሪካና የአረብ ሰዎች ዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበው የማውራት እንጂ ሞባይል ስልክንና ኢንተርኔትን የመጠቀም ስልጡን ሰብእና የላቸውም። ለእውነት ብዙም ክብር ስለሌላቸው፤ ቴክኖሎጂውን የአፈናና የአሉቧልታ መሳሪያ ያደርጉታል። በመከላከያ ቴክኖሎጂም በኩል፤ ዱላና ጩቤ ከመታጠቅ አልፈው በክላሺንኮቭና በታንክ ለመደራጀት የሚበቃ ስልጡን ማንነት አላዳበሩም። በሌላ አነጋገር፣ ሞባይልና ኢንተርኔት፣ ወይም  ክላሽና ታንኮች ላይ አይደለም ችግሩ። እነዚህ ሁሉ አሜሪካ ውስጥ እንደልብ ይገኛሉ። ግን፤ ሲጨፋጨፉ አናይም። ለቴክኖሎጂው የሚመጥን ስልጡን አስተሳሰብና ባህል ገና አልራቃቸውማ። በአፍሪካና በአረብ አገራት ግን፤ አብዛኛው ሰው፤ ከጥንቱ ጭፍንነትና ኋላቀርነት ጋር ሙጭጭ ስላለ፤ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የመጠቀም ሰብእና አልፈጠረም። ሞባይልና ኢንተርኔትን በመጠቀም፣ ጭፍን እምነትን ሲሰብክ፣ የጥላቻ አሉባልታን ሲያራግብና የአፈና ፕሮፓጋንዳን ሲያሰራጭ፤ ከዚያም ለስልጣን እየተሻኮተ፣ በዘርና በሃይማኖት እየተቧደነ ሲጨፋጨፍና ሲጫረስ የምናየው ለምን ሆነና!
የቀረ አገር የለም ማለት ይቻላል። እንደ ዚምባብዌ፣ ኤርትራና ሳውዲ አረቢያ የመሳሰሉ አገራት በለየለት የአምባገነንነት ፕሮፓጋንዳና አገዛዝ ይሰቃያሉ። ...ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሴንትራል አፍሪካ፣ ማሊ፣ ኮንጎ፣  ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ የመን... የመሳሰሉ አገራት፣ ከአምባገነንነት በተጨማሪ በዘረኝነትና በሃይማኖት አክራሪነት በተለኮሰ ግጭትና ጦርነት ይተራመሳሉ። (እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሌሎች አገራትም፤ ከዚሁ አዝማሚያ የፀዱ አይደሉም - የኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ማዕድ ውስጥ፣ አምባገነንነት፣ ዘረኝነትና አክራሪነት በየአይነቱ እየተበራከተ መምጣቱን አልታዘባችሁም?) በኢቦላ ወረርሽኝ የእልቂት ደመና ያንዣበበባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራትን ደግሞ ተመልከቷቸው።
እነ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ፣ ከአሰቃቂ የእርስበርስ ጦርነትና ከአስከፊ የኤችአይቪ ኤድስ በሽታ ገና ትንሽ ፋታ ከማግኘታቸው፣ አሁን በኢቦላ ወረርሽኝ መተራመስ ይዘዋል። አስገራሚው ነገር ምን መሰላችሁ? አለም ሁሉ ስለኢቦላ በጭንቀት እያወራ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፤ በሴራሊዮንና በላይቤሪያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች “ኢቦላ የምር ነው” (Ebola is Real) በሚል የትምህርት ዘመቻ ተጠምደዋል። ለምን በሉ። “የኢቦላ ወረርሽኝ አልተከሰተም፤ ኢቦላ የሚባል በሽታ የለም” የሚሉ የአሉባልታ ወሬዎችና ጭፍን እምነቶች በስፋት ስለተሰራጩ፤ ብዙ ሰው ሳይንሳዊ መረጃዎችንና የጥንቃቄ ምክሮችን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። እናም፤ የጤና ባለሙያዎች፣ “ኢቦላ የእውነት በሽታ ነው!” እያሉ ለማሳመንና ለጤና የሚበጁ የጥንቃቄ ምክሮችን ለማሳወቅ መከራቸውን ያያሉ። ይህም ብቻ አይደለም።
“ኢቦላ የውሸት ነው” ብለው የሚሰብኩና የሚያምኑ ሰዎች፤ በዚያው መጠን...፤ ወላጆቻቸውን በኢቦላ ያጡ ሕፃናት ላይ የሚያደርሱት ስቃይ ልክ የለውም። የሕፃናቱ ወላጆች ከሞቱ በኋላ፣ መኖሪያ ቤታቸው የመድሃኒት ርጭት ቢደረግበትም፤ ልጆቹ በምርመራና በሳምንታት ክትትል ከኢቦላ ቫይረስ ነፃ እንደሆኑ ቢረጋገጥም፤ በሰፈራቸው ውስጥ እንደ እርግማን ነው የሚታዩት። ወደ ቤታቸው አካባቢ ከሩቁ ዝር የሚል የሰፈር ሰውና ዘመድ የለም።፤ ከቤታቸው ውጭ ውልፊት እንዲሉም አይፈቀድላቸውም። ለምን? ኢቦላን በመፍራት ነው። በአንድ በኩል፣ “ኢቦላ የሚባል በሽታ የለም” የሚል ጭፍን አሉባልታና እምነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ወላጆቹ በኢቦላ ሞተዋል” በሚል ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ ልጆችን ማግለል... እነዚህ ሁለት ነገሮች ተቃራኒ ይመስላሉ። ግን ምንጫቸው ተመሳሳይ ነው - ከስልጣኔ የራቀ ጭፍን አስተሳሰብና ኋላቀር ባህል! የጭፍንነትና የኋላቀርነት አንዱ ምልክት’ኮ፤ ተቃራኒ ነገሮችን አዳብሎና አቅፎ የመያዝ ባህሪ ነው።       
በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞንሮቪያ፣ በአንድ ክሊኒክ ዙሪያ የተከሰተውንም ረብሻ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ድሆች በሚበዙበት ሰፈር ውስጥ፣ የኢቦላ ምርመራና ህክምና የሚካሄድበት ክሊኒክ መከፈቱ ነው የረብሻው ሰበብ። በየእለቱ፤ አምቡላንሶች ወደ ክሊኒኩ ሲመላለሱ፣ ከራስ እስከ እግር “መከላከያ ልብስ” ያጠለቁ የጤና ሙያተኞችም ህመምተኞችን ይዘው ሲመጡና ሲገቡ ይታያል። የጤና ባለሙያዎቹ ጠንቃቃ ይመስላሉ። እንዲያም ሆኖ፣ በአፍሪካ መንግስት የተከፈተ ክሊኒክ፣ ለዚያውም ከጦርነት ባላገገመችው ላይቤሪያ ውስጥ፣ የተሟላ ጥንቃቄ ያደረጋል ብሎ ማመን የዋህነት ነው። የተሟላ ጥንቃቄ የሚደረግ ቢሆን ኖሮ፤ እስካሁን በመቶ የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች በኢቦላ ባልሞቱ ነበር። እናም፤ ከአቅራቢያቸው በተከፈተ ክሊኒክ ሳቢያ፣ በአንዳንድ የሰፈሩ ሰዎች ዘንድ ፍርሃትና ጥርጣሬ ማንዣበቡ አይገርምም - “በሰፈራችን የኢቦላ ክሊኒክ ከፍተው ለበሽታ ሊያጋልጡን ነው” ብለው ቢሰጉ እንዴት ይፈረድባቸዋል? ከማንም ሚዛናዊ ሰው የሚጠበቅ ስጋት ነው።
መጥፎነቱ፣ የሰፈሩ ሰዎች ስጋታቸውን በአግባቡ የሚገልፁበት፣ መንግስትም የመፍትሄ ምላሽ የሚሰጥበት ስልጡን አስተሳሰብና ባህል በአገሬው የለም። አንዳንዶቹ ሰዎች፣ የተለያዩ አሉባልታዎችን እየጨማመሩ ስጋታቸውን በፌስቡክና በሞባይል ሜሴጅ ካራገቡት በኋላ ነው፤ በስሜት የጋሉ በርካታ የሰፈሩ ሰዎች በክሊኒኩ ዙሪያ ለተቃውሞ የተሰባሰቡት። ለተቃውሞ ከሚጮሁት ሰዎችም ሆነ ክሊኒኩን ለመጠበቅ ከተመደቡት ሰራተኞች መካከል፣ ሰከን ብሎ ለማሰብ የሚችልና ሌሎቹንም የሚያሰክን ሰው አልነበረም። “ሆይ ሆይታ” ነገሰ። የተቃውሞና የጥበቃ ጩኸት፤ “በለው ... ግፋው” ወደሚል ግርግር ለመሸጋገር ጊዜ አልፈጀበትም። ለተቃውሞ ተሰባስበው ረብሻ የፈጠሩት የሰፈሩ ሰዎች፣ የክሊኒኩን ጥበቃ ጥሰው ገቡ። አካባቢው ተተረማመሰ። ከፊሎቹ “ኢቦላ የውሸት ነው” እያሉ በክሊኒኩ ውስጥ የነበሩ ህመምተኞችን እየጎተቱ ያወጣሉ። ገሚሶቹ ህመምተኞች የተኙበትን አንሶላና ብርድልብስ፣ ፍራሽ ሳይቀር ይዘርፋሉ። አንዳንዶቹ የላብራቶሪ እቃዎችን እየበረበሩ ተሸክመው ይወስዳሉ...። አሁን ይሄ ምን ይባላል?
“ሰፈራችን ውስጥ የኢቦላ ክሊኒክና ህመምተኛ እንዲኖር አንፈልግም” በሚል ስጋት የተሰበሰቡ ሰዎች፤ ያለ ምንም “ስጋት” ህመምተኞችን መጎተትና በቫይረስ የተበከሉ አንሶላዎችን መዝረፍ፤ ከእብደት አይተናነስም። ምን ያህሉ በቫይረሱ እንደሚጠቁ አስቡት። ለዚያውም፤ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው የሚኖርባት ከተማ! ለዚያውም በተፋፈፈገው የድሆች ሰፈር! የዚህ ጭፍንነት መዘዝ ቀላል አይደለም። በኢቦላ ወረርሽኝ ቀዳሚ ያልነበረችው ላይቤሪያ፤ ዛሬ ዋናዋ ተጠቂ ሆናለች። አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ በላይቤሪያ 2ሺ ገደማ ሰዎች በኢቦላ ሞተዋል። ጭፍን አስተሳሰብና ኋላቀር ባህል የቱን ያህል ተቃራኒ ነገሮችን አቅፈው እንደሚይዙ አያችሁ! በኢቦላ ሰግተናል ብሎ መቃወምና ያለስጋት ከኢቦላ ጋር መጫወት!
በእርግጥ፤ እንዲህ አይነት ተቃርኖ አዲስ ነገር አይደለም። ከነጥፋቱ፤ ድሮ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነገር ነው። አሁን በዘመናችን የተፈጠረ አዲስ ነገር ቢኖር ምን መሰላችሁ? ነባሩን ተቃርኖ የሚያራግብና የጥፋት ውጤቱን የሚያባብስ ሌላ አዲስ ተቃርኖ ተፈጥሯል። ምን አይነት ተቃርኖ? “ጭፍን አስተሳሰብን ከስልጣኔ ውጤቶች ጋር፤ ኋላቀር ባህልን ከቴክኖሎጂ ጋር ያደባለቀ ተቃርኖ”!
ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ የአፍሪካና የአረብ አገራትን መቃኘት ትችላላችሁ። በደቡብ ሱዳንና በሴንትራል አፍሪካ፤ ወይም በየመንና በሶሪያ... ምን አለፋችሁ? ኢትዮጵያን ጨምሮ፤ በአፍሪካና በአረብ አገራት ውስጥ፤ በጎሳና በብሄረሰብ፤ ወይም በሃይማኖትና በጭፍን እምነት ተቧድኖ መጨፋጨፍ ከድሮ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ኋላቀር ባህል ነው። አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ሶሪያና ደቡብ ሱዳን ውስጥ “የሱኒ ሙስሊም እና የሺዓ ሙስሊም”፤ “የኩርድ ተወላጅና የአረብ ተወላጅ”፤ “የኑዌር እና የዲንቃ ተወላጅ” እያሉ የድሮ ሰዎች ሲጨፋጨፉ ነበር - በድንጋይና በዱላ ወይም በጩቤና በጦር። ዛሬ ግን መሳሪያቸው ተለውጧል - ቦንብና ፈንጅ፤ ታንክና ባዙቃ... የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ። የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን መመልከት ይበቃል። ወገባቸው ላይ ከሚታጠቁት ጥንታዊ ጩቤ ጋር ትከሻቸው ላይ ክላሽንኮቭ ያንጠለጠሉ ታጣቂ ቡድኖች ከተማዋንና አገሪቷን በሙሉ ወረዋታል። የግድያውና የእልቂቱ መጠንም የዚያኑ ያህል ይጨምራል - ጭፍን አስተሳሰብና ኋላቀር ባህል ከቴክኖሎጂ ውጤት ጋር ሲቀላቀሉ!
በሃይማኖትና በጭፍን እምነት ወይም በዘርና በቋንቋ ሰዎችን ለማቧደን የሚሰብክና የሚቀሰቅስ፤ ያልታጠቁ ሰዎችን ጭምር በጭካኔ እያረደና እየገደለ የሚያሸብር ሰው ድሮ ጥንትም ነበር። ዛሬ በዘመናችን የተጨመረ ነገር ምንድነው? ስብከቱንና ግድያውን በሞባይል እየቀረፀ በኢንተርኔት ያሰራጫል። የኢቦላ ወረርሽኝም ተመሳሳይ ነው። የበሽታ ወረርሽኝ፤ ለአፍሪካ አዲስ ነገር አይደለም - ከኋላቀርነት ጋር ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው። ዛሬ በዘመናችን የተፈጠረ አዲስ ነገር ቢኖር፤ የወረርሽኙ የስርጭት ስፋትና ፍጥነት ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ነው። የበሽታ ወረርሽኝ፤ ዛሬ እንደጥንቱ፤ በአንድ መንደር፣ በአንድ ወረዳ ወይም በአንድ አገር ውስጥ ተገድቦ አይቀርም። ለምን? ከጭፍን አስተሳሰብና ከኋላቀር ባህል ሳንላቀቅ፤ የሳይንስና የስልጣኔ ውጤት የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንጠቀማለና።
በአንድ በኩል፤ መረጃዎችን ለማረጋገጥ ከመሞከር ይልቅ አሉባልታዎችን ማስተናገድ፤ ሰክኖ ከማሰብና በራስ ከመመራት ይልቅ በጭፍን ስሜት መታወርና በመንጋ መንጋጋት ይቀናናል። ለተጨባጭ መረጃና ለሳይንሳዊ አስተሳሰብ ዋጋ ከመስጠት ይልቅ፤ ነገሮችን በዘርና በጭፍን እምነት፣ በሃይማኖትና በጥንቆላ መመራትን እንወዳለን። በሌላ በኩል ደግሞ ከሳይንስና ከስልጣኔ የሚገኙ ውጤቶችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንፈልጋለን።
ለምሳሌ ከተሜነት አንዱ የስልጣኔ ውጤት ነው። ሞንሮቪያ፣ ፍሪታውንና ኮናክሪን የመሳሰሉ ዋና ከተማዎች ውስጥ በርካታ ሚሊዮኖች እንደሚኖሩ አስቡት። እንደ ድሮ በየገጠሩ ተበታትነው አይኖሩም። እንዲህ ከተሜነት በተስፋፋበት በዛሬው ዘመን፤ በጥንቱ ጭፍን አስተሳሰብና ኋላቀር ባህል ሳቢያ፤ አምባገነን መንግስት የአፈናና የግድያ ዘመቻ ሲያካሂድ፣ ወይም በዘር እና በሃይማኖት የተቧደኑ አክራሪዎች ሽብርና ግጭት ሲፈጥሩ፤ ወይም ደግሞ እንደ ኢቦላ የመሳሰሉ የበሽታ ወረርሽኞች ሲከሰቱ፤ የስንት ሚሊዮን ሰዎች ሕይወትና ኑሮ እንደሚናጋ አስቡት? የጭፍንነትና የኋላቀርነት መዘዝ፤ እንደ ድሮ የመቶ ወይም የአንድ ሺ ሰዎችን ህይወት በማናጋት አይመለስም። ዘመናዊ ትራንስፖርትም እንዲሁ ከሳይንስና ከስልጣኔ የሚገኝ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። መንገዶች እየበዙ መኪኖች እየተበራከቱ ሲመጡ፤ የሰዎች እንቅስቃሴም እንዲሁ ይጨምራል - የንግድ ወይም የጦርነት፤ የግንባታ ወይም የጭፍጨፋ፤ የምግብ አቅርቦት ወይም የበሽታ ወረርሽኝ ይጨምራል። ከኢንተርኔትና ከሞባይል ስልክ ጋርም፤ የመረጃ ወይም የአሉባልታ፣ የሃሳብ ወይም የጭፍን ስሜት ስርጭት ይጨምራል። የበርካታ ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ስብስብ ውስጥ፤ የሳይንስ ሳይሆን የሃይማኖት፤ የስኬታማ ሰዎች ታሪክና ተሞክሮ ሳይሆን በዘር የመቧደንና በጭፍን ፍረጃ የመሰዳደብ ጩኸት የበረከተው በዚሁ ምክንያት ነው። ለጊዜው የከፋ ጥፋት ስላላስከተለ፣ ቸል ልንለው እንችል ይሆናል። ግን፤ ከጥንቱ ጭፍን አስተሳሰብና ኋላቀር ባህል ሳንላቀቅ፤ የሳይንስና የስልጣኔ ውጤት የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ስንጠቀም፤ ከፍተኛ ጥፋትና መዘዝ መከተሉ እንደማይቀር አትጠራጠሩ።
ዙሪያችሁን ተመልከቱ። አንዳንዶቹ አገራት፤ በአምባገነኖች አፈናና ግድያ ይሰቃያሉ። ሌሎቹ በበሽታ ወረርሽኝ ያልቃሉ። ገሚሶቹ፤ በዘር ወይም በብሄረሰብ ተወላጅነት በተቧደኑ ታጣቂዎች ይታመሳሉ። ገሚሶቹ በሃይማኖትና በጭፍን እምነት በተቧደኑ አክራሪዎችና ታጣቂዎች ይተራመሳሉ። ይህን ሁሉ ጥፋት እያየን፤ እኛ ዘንድ እስኪደርስና እስኪያጥለቀልቀን ድረስ በዝምታ እንጠብቅ? ይባስ ብለን እያራገብን እንቆይ? አቋራጭ መፍትሄ የለውም። በአሉባልታና በፕሮፓጋንዳ ከሚሽከረከር ጭፍን አስተሳሰብና ኋላቀር ባህል በመላቀቅ፤ መረጃ ላይ ወደተመሰረተ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና ስልጡን ባህል ለመሸጋገር እንጣር።


Read 5875 times