Monday, 20 October 2014 07:51

ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠ ምላሽ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

           አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም  እትሙ በነፃ አስተያየት አምድ ስር ’’በዲላ ዩኒቨርሲቲ ያዘኑት የተማሪ ወላጆች’’ በሚል ርዕስ ታትሞ የወጣውን ፅሁፍ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ፅሁፍ መገንዘብ እንደቻልነው ዝግጅት ክፍሉ ሊታረሙ ይገባል ብሎ በአስተያየት መልክ ማሳሰቡ በግርድፉ ሲመዘን መልካም ነው ብሎ መውሰድ ይቻል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጅ ፅሁፉ የአንድ ወገንን አስተያየት ብቻ ይዞ መውጣቱ አግባብ ነው ብለን አናምንም፡፡ ምንጊዜም ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ግለሰብ ወይም ተቋም በገንቢነታቸው የሚሰጡትን አስተያየቶች መውሰድ አለበት፡፡ ተቋማችንም ከዚህ የተለየ አቋም የለውም፡፡
ፀሀፊው በፅሁፉ ካሰፈራቸው አስተያየቶች ለአብነት እየጠቀስን ብንመለከት ‘’ዩኒቨርሲቲው በጣም ሞቃት ስለሆነ ተማሪዎች ’’ሰመራ’’ በማለት በሰየሙት ----’’ የሚለው ገለፃ ከመጠየቅ ስንፈት የመጣ ስህተት ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኦዳያኣ ግቢ በተለምዶ ’’ሰመራ’’ ተብሎ ይጠራ የነበረው፣ ከከፍተኛ ሙቀቱ የተነሳ ሳይሆን ግቢው ገና ስራ እንደጀመረ (1999 ዓ.ም) የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በጊዜያዊነት (ለአንድ ወሰነ ትምህርት) በዚያ ግቢ በትውስት ተቀብሎ ስላስተማረ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ፅሁፍ ላይ ያስተዋልነው ነገር ቢኖር ጋዜጣው (ፀሃፊው) ራሱም እንዳስቀመጠው ለፅሁፉ መነሻ የሆነው መኪና ላይ ያገኛቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ይጠቅስና ደግሞ ወደ ታች ወረድ ብሎ በቦታው ተገኝቶ ራሱ ያየው እንደሆነ ያወራል፣ ደግሞ ከዛው ሳይወጣ ስለ ቅበላ ማውራቱን ትቶ አምና ተከሰተ ስለሚለው ነገር ያወራል፡፡ ይህ የሚያሳየን እርስ በርሳቸው የተጣረሱ እና የማጣራት ስራ ያልተሰራባቸው ስህተቶችን ነው፡፡
በፅሁፉ ውስጥ ደረቅ እንጀራ አቅራቢዎች በዱቤ ያቀርቡ እንደነበረና አስተዳደሩ ሲቀየር ገንዘባቸውን ሳይቀበሉ በክስ ሂደት ላይ እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲው መክሰስም ሆነ መከሰስ የሚችል በአዋጅ የተቋቋመ ህጋዊ ተቋም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተነሳው ጉዳይ ግን ተጋኖ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲውም እንጀራ በዱቤ የገዛባቸው ጊዜያት የሉም፡፡
እነዚህ በአብነት የተጠቀሱት ስህተቶች የተከሰቱት ፀሀፊው የዩኒቨርሲቲውን የአስተዳደር አካላት ሳያነጋግር በፅሁፉ ላይ እንደተጠቀሰው በግለሰቦች አስተያየት ላይ ብቻ በራሱ መላምቶች ተመርኩዞ በመፃፉ ነው፡፡ ግለሰቦቹ የተሰማቸውን አስተያየት የመስጠት መብታቸው በህገመንግስታችን የተቀመጠ ዴሞክራሲያዊ መብት በመሆኑ ለምን ሰጡ ብለን ክርክር የምንገጥምበት ጉዳይ አይኖረንም፡፡ በተመሳሳይ ፀሀፊው ዩኒቨርሲቲያችን ላይ ያዩትን (የማየት እድሉ ከነበራቸው) ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን የመፃፍ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ፅሁፍ ሲጻፍ በተባራሪ ወሬ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ተመርኩዞ፣ ግራ ቀኙን አይቶ ሁለቱንም ወገን አነጋግሮ፣ ቢቻል በአካል አረጋግጦ መሆን እንዳለበት የጋዜጠኝነት ስነምግባሩም ሆነ የፕሬስ ህጋችን የሚጠይቁት  ግዴታ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ዝግጅት ክፍሉም ይህንን ሀቅና ሀገራዊ መርህ እንደሚያምንበት እሙን ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡
ከዚህ አንጻር ፅሁፉ የሁለት ወገንን ሀሳብ ያላካተተ መሆኑ ከመጀመሪያው ሚዛናዊነቱን ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው አከራካሪ አይሆንም፡፡ አጠቃላይ ጉዳዮችን ለማብራራት ያህል ግን በእኛ በኩል በያዝነው ዓመት በተቻለ መጠን የተማሪዎቻችንን አቀባበል ስነስርዓት ምቹ በሆነ መንገድ ለማከናወን የተቻለንን ጥረት አድርገናል፡፡ ይህ ማለት ግን ምንም እጥረት የለውም ለማለት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ፅሁፉ ላይ የተጠቀሱት በተለይ ደግሞ የተመደበው አንድ አውቶብስ ብቻ ነው የሚለውን ብንወስድ ከእውነት የራቀ አስተያየት ነው፡፡  በእኛ በኩል ያሉንን ተሽከርካሪዎች በተገቢው መንገድ አሰማርተን፣ አሽከርካሪዎች ለምሳ በሚል እንኳን አገልግሎት እንዳያቋርጡ በሽፍት እንዲጠቀሙ አድርገን አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ እዚህ ላይ እንደ አስተያየት ሰጪው ግለሰብ ሲታይ፣ ምን አልባት በግለሰቡ አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከህግ አንጻርና እንደ ጋዜጠኛ ሲታይ፣ ግለሰቡ የሰጡትን አስተያየት በመያዝ ከጉዞ ቀርቶም ቢሆን በአካል ተገኝቶ ሁሉንም ጥያቄዎችም ሆነ አስተያየቶች አጣርቶ መሄድ ይጠበቅበት ነበር (ያውም ራሱ ጋዜጠኛው ’’ሰዎቹ ስለዩኒቨርሲቲው የሚናገሩት ፈፅሞ ለማመን የሚያዳግት ነው፤--- ሰዎቹ እንደሚሉት ይሆናል ብዬ ስለማልገምት---’’ እያለ!)፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሌሎች የተሸከርካሪ አማራጮች ማለትም የባጃጅና የጋሪ አገልግሎት ተከለከልን ለሚለው  አስተያየት ከምን አንጻር እንደሆነ ሊመዘን ይገባ ነበር፡፡ ከአሁን በፊት ከነበሩን የተማሪ አቀባበል ስነስርዓቶች በርካታ ልምዶችን ወስደን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡ በፊት ካየናቸው እጥረቶች አንዱ፣ ተማሪዎቻችን በሚገቡበት ወቅት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸው እና አልፎ አልፎም የእቃ መጥፋት ሁኔታ ያጋጥማቸው የነበር መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ አመት ተቋማችን ከከተማው ፖሊስና ትራፊክ ፅ/ቤት ጋር ቅንጅት በመፍጠር አውቶብሶች ወደ መናሃሪያ ከመሄዳቸው በፊት ወደ ዩኒቨርሲቲያችን እየገቡ የጫኗቸውን ተማሪዎች እንዲያወርዱ በመደረጉ፣ከአሁን በፊት ሲያጋጥሟቸው የነበሩ በርካታ ችግሮች ተቀርፈዋል፡፡ አልፎ አልፎ ወደ ግቢ መግባት ያልቻሉ አውቶብሶች ሲኖሩ ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን መገንጠያ ሲደርሱ እንዲያቆሙ እየተደረገ፣ በተቋማችን ተሸከርካሪዎች ተማሪዎቻችንን የምናስገባበት አሰራር ነበር ተግባራዊ የተደረገው፡፡ ይህ ደግሞ ተማሪዎቻችን ለወጪ እንዳይዳረጉና ከተለያዩ ተፅዕኖዎች ነፃ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ የሚያስመሰግን እንጅ የሚያስነቅፍ አልነበረም፡፡ በተቃራኒው በአቀበባል ስነስርዓቱ እረክተው ቢሮ ድረስ ቀርበው ያመሰገኑ ወላጆችም እንደነበሩ ልንገልፅ እንወዳለን፡፡
ሌላው በፅሁፉ የቀረበው ጉዳይ የተቋማችን የአጥርና አጠቃላይ የግንባታዎች ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻርም ጸሀፊው እንከን የለሽና ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ በአካል ማየትና እውነታውን  ከተቋሙ በኩል የማረጋገጥ ግዴታም ነበረበት፡፡ ከላይ እንደገለጽነው በዚህ በኩልም ምንም እንከን የለብንም የሚል አቋም የለንም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአጠቃላይ በሀገራችን በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የግንባታ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ይህ መልካም እድል ከገጠማቸው ተቋማት አንዱ የእኛ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለተቋማችን እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ገፀ በረከታችን ነው፡፡
የአጥርም ሆነ ሌሎች ግንባታዎችን በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ተቋማችን ብቻ ሳይሆን የሚመለከታቸው  ባለድርሻ አካላትም የዞን እና የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው በጋራ እየተረባረብን እንገኛለን፡፡
ፀሀፊው ያልተገነዘበው አንዱ ነገር፣ ዩኒቨርሲቲያችን 13 ወር ሙሉ የመማር ማስተማር ስራ የሚያከናውንና በ2006 ዓ.ም የክረምት መርሃ ግብርም በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ የቆየ ሲሆን የክረምት ተማሪዎችን ከሸኘ በኋላም መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ይህም በመሆኑ ምንም አይነት ተዘግቶ የከረመና ፀሀፊው በከፍተኛ ግነት ነገሩኝ ያላቸው ግለሰቦች እንደገለፁት፣ በአቧራ ተሞልቶ ተባይ አስከሚያፈራ የደረሰ መኝታ ቤትና የተበለሻሹ ግብዓቶች የመኖራቸው ጉዳይም ትክክል አለመሆኑን ታዝበናል፡፡
ይልቁንም ለእያንዳንዱ የተማሪ መኝታ ክፍል ህንጻዎች የጽዳት ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች  ያሉበት፣ ተማሪዎቹም ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት በማከናወን ተማሪዎቻችንን የተቀበልን መሆናችን ልብ እንዲባል እንፈልጋለን፡፡
ተማሪዎች እንደማንኛውም የተሻለ ምቾት ሊመርጥ እንደሚችል ግለሰብ ሁሉ የታሸገ ወይም የቀዘቀዘ ውሃ ገዝተው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይህ እውነታ በከፍተኛ ሁኔታ ተኳሽቶ፣ ምንም አይነት ውሃ በግቢ ውስጥ እንደሌለና ተማሪዎችም እግራቸውን እንኳን የሚታጠቡበት አጥተው እንደተቸገሩ አድርጎ ማቅረቡ፣ ከአንድ ጋዜጠኛ የማይጠበቅ ስነምግባር ነው፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ ለሁሉም ህንጻዎች  የሚዳረስ፣ ከዚህ በፊት ከሚጠቀሙበት የተሻለ መጠንና ጥራት ያለው ውሃ ተገኝቶ፣ የሙከራ ስርጭት ተደርጎ፣ በየህንጻው ላይ ያሉ የመፀዳጃ ቤቶች ክፍት እንደሚሆኑ እየገለፅን፣ ጸሀፊው ሰባት መቶ ሜትር ሄደው ጫካ ይፀዳዳሉ ብሎ ላቀረበው ሃሳብ፣ ከህንፃዎች ውጪ ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤቶችን በመገልገል ላይ ያሉ በመሆኑ የፀሀፊው ሃሳብ እኛን አይገልፀንም፡፡ በአካል ተገኝቶ ለማየት እንደሚቻለው ሁሉ በኦዳያኣ ግቢ (በፀሐፊው አገላለፅ ’’ሰመራ’’ ግቢ) ውስጥ ተማሪዎችም እንደሚመሰክሩት፣ጭቃ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ መኝታ ቤቶችን ከመንገድ፣ መማሪያ ክፍሎችን ከመንገድና እርስ በርሳቸው የሚያገናኙ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች (ኮብል ስቶን መንገድ) ተሰርተዋል፡፡ ከከተማው አስተዳደር ጋር ተያይዞም ፅሁፉ ላይ የተቀመጠው ጉዳይም ሚዛናዊነቱን የጠበቀ አይደለም፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ሆነ የከተማው ማህበረሰብ ዩኒቨርሲቲውን አይፈልገውም የሚለው ጫፍ የወጣ ዘገባ ማስቀመጥም ከግዴለሽነት የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር አንድም የከተማው ማህበረሰብ ተጠይቆ አልፈልግም ባላለበት ሁኔታ መንገደኞችን አነጋግሮ ጥርጣሬ አለኝ ብሎ ማስቀመጥ፣ አጠቃላይ ማህበረሰቡን ካለመረዳት የሚመነጭ በመሆኑ ከህግም አንጻር ሲታይ ተገቢ ያልሆነና ሊያስጠይቅ የሚችል ጉዳይ እንደሚሆን ይሰማናል፡፡
የአካባቢው መስተዳድርና ማህበረሰብም ከዩኒቨርሲቲው ተጠቃሚ እንደሆኑ አጥብቀው የሚያምኑና  የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ በአፅንኦት ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ነገር ግን ከአፍራሽነት የሚመነጭ፣ ተቋሙንና ማህበረሰቡን ለማቃረን የማለም እቅድ ካልሆነ በስተቀር ይህንን በአካል ቀርቦ ተቋሙ ለማህበረሰቡ እየሰጠ ያለውን ድጋፍና ተተግብረውም የመጡትን ለውጦች አይቶ በመገምገም ሚዛናዊ ፅሁፍ መፃፍ ይቻል እንደነበረ ግልፅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ዩኒቨርሲያችን የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ እንደሚያደርጉት በግንባታም ይሁን በአጠቃላይ የትምህርት ስራ እንቅስቃሴ ራዕዩን ለማሳካት በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ እንዲታወቅና በዚህ የልማት እንቅስቃሴ ወቅት የሚከሰቱ መጠነኛ ችግሮችን እያጎላን ልማታችንን ከማደናቀፍ በዘለለ ጠንካራ ጎኑንም በማየትና መጠነኛ ችግሮችን በጋራና በንቃት እየቀረፍን መጓዝ እንዳለብን የጋራ ስሜት መያዝ የተቋማችን ብቻ ሳይሆን የሚዲያዎች ሚናም እንደሆነ ስለምናምን፣በእናንተ በኩል ይህ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ ፅሁፍ ቢቻል ሁሉንም ጉዳዮች ከሚመለከታቸው የተቋማችን ኃላፊዎች ጋር በመገናኘትና ሁሉንም ተግባር በአካል በመጎብኘት እውነቱን እንድታረጋግጡ እንጋብዛለን፡፡ከአዘጋጁ፡ ዩኒቨርሲቲው ከላይ እንደገለጸው የተማሪ ቤተሰቦችን ቅሬታ ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲውን አካል ምላሽ ማካተት ተገቢ እንደነበር እናምናለን፡፡ ሆኖም በአካል ተገኝተን ሁኔታውን ለማየት በቂ ጊዜ ስላልነበረን ጋዜጣውን ወደ ማተሚያ ቤት እስከላክንበት የመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በሁለት የዩኒቨርሲቲው ስልኮች በመደወል ምላሽ የሚሰጠን አካል ለማግኘት የጣርን ቢሆንም ስልኩን የሚያነሳ ባለመኖሩ ሙከራችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ሳምንት ከተማሪ ቤተሰቦች ለተሰነዘረው ቅሬታ ከላይ የቀረበውን ምላሽ በጽሁፍ ስለላከልን ከልብ እናመሰግናለን፡፡




Read 3254 times