Monday, 20 October 2014 07:55

የጉራጌ አገር የጉዞ ማስታወሻዬ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

ዘሙቴ ማሪያም
 “ክትፎ ልበላ ሄጄ ከብዙ መልካም ሰዎች ተዋውቄያለሁ!”

    ስለ ዘሙቴ ከማውራት አስቀድሞ አቅጣጫዋን መጠቆሙ የአባት ነው፡፡ ዘሙቴ በዓለም ገና በኩል በቡታ ጅራ በኩል ቡኢንና ኬላን አልፎ ወደ ቀኝ ወደ በኬ በሚገባው ኮረኮንች (ፒሳ) መንገድ ተሄዶ በተራሮች መካከል የምናገኛት ከሩቅ ከዳገቱ ቁልቁል የምናያት ማሪያምን በአረንጓዴ ሀር ፀጉር እንደተከበበ ሳዱላ ሆና የምትገኝ ቦታ ናት!
ስለዘሙቴ ማርያምና ስለዘሙቴ የነገሩኝ በርካታ ሰዎች ናቸው!
አንደኛው የሰፈር የመንደሩ ግንድ የሚባሉት አቶ ታደሰ ተክሌ ናቸው፡፡ እንዲህ አሉኝ፡-
“ያኔ ቤትዎን ሳላይ?” አልኳቸው ጨዋታ ለመጀመር፡፡
“ምነው?” አሉኝ፤ በአዛውንት ወግ፡፡ ሰውን መጠየቅ ምን ገደደ ነው ነገሩ፡፡
“ብዛት ስለነበረው ሰዉ ወደርስዎ መምጣት አልተመቸኝም! እንግዶች በብዛት ስለነበሩ እኔ ከነሱ ጋር ቀረሁ፡፡ በኋላ ደሞ እናንተም ወደኛ መጣችሁ፡፡ ቁርስ ብጤ ተዘጋጅቶ፡፡ ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍነው - እኔ እንግዲህ እንደገጣሚ፣ እንደደራሲም፣ እንደጋዜጠኛም፣ እንደሰውም ሆኜ ነው የመጣሁት፡፡ እኛ በብልጭልጭ ተከበን የእናንተ ዓይነት አረንጓዴ አገር አይታየም፡፡
“አረንጓዴው ተራራችን ድንቅ ነው” አሉ፡፡
“ከዘሙቴ መስራቾች አጠናካሪዎች መካከል እርሶ አንዱ ነዎት ይባላል?...”
እርሶ የተወለዱት ዘሙቴ ነው?”
“አዎ ዘሙቴ ነው የተወለድኩት… የነግርማ አባትና የእኔ አባት ወንድማማቾች ናቸው ማለት ትችላለህ፡፡”
“እኔ ዲያቆን ነበርኩኝ”
“ኦ ዲያቆን ነበሩዋ!”
“አዎ! እኔ ዲያቆን አባቴ ቄስ ነበሩ! ኪዳነምህረትም፣ ማሪያምም ነው የምንዲያቁን፡፡ ዘሙቴ ማሪያም በወር ነው የምትቀደስ፤ በየሳምንቱ ነው የምትታጠን”
“ማን ያጥናታል ማሪያምን?”
ቄሶች፡፡ ፊት የኔ አባት ነበር፡፡
“ተክሌ ማናቸው? አባትዎ?”
“ተክሌ ደሚሶ … መምሬ ወልዴም፡- ወልዴ ደሚሶ!”
“ወልዴ ማናቸው?… ልጆች አላቸው?”
“በቀለች ሸለሜ…” የሚባሉ አሉ፡፡
“በዓመት ስንት ጊዜ ይሄዳሉ ዘሙቴ?”
“በዓመት አንዴ … አሁን ህመሙም በረታ … መኪና፤ ቤት ድረስ አይገባም”
“አዎ ያ መንገድ፣ ትንሽ ድካም አለው ለኔም ጭምር ይከብደኛል”
“አዎ”
“መስራቹ እነማናቸው?”
“አያት ቅድመአያቶቼ ናቸው፡፡”
“የመጀመሪያ በመሆን ከዘሙቴና ከኪዳነምረት ማን ይቀድማል?
“ማሪያም ትቀድማለች!”
ኪዳነ ምህረት በሳምንት በሳምንት ይቀደሳል፡፡ አማኑኤል ድርብ ነው … ብቻ በየሳምንቱ ይቀደሳል …
“ምን ያህል ጊዜ ነው ከተቋቋመች?
“ው እኔ ሳልወለድ በፊት ነው …”
“እርሶ ዕድሜዎ ስንት ነው?”
“ወደ 80 ልጠጋ ነው፡፡”
“እሷ ከናንተ ሁሉ ቀዳሚ ናት?”
“እንዴታ የትና የት!”
“እንዲህ ህመም ዕድሜም ሳይመጣ እርሶ ይሄዱ ነበር ማለት ነው?”
“እንዴታ! አሳምሬ ነዋ!
“ዋ! መድኀኒዓለም፣ ኪዳነ ምህረት፣ ዘሙቴ ማርያም እኛ ነበርን የምናገለግል…”
“በስንት አመትዎ ወደዚህ መጡ?”
“18 ዓመት ግድም!”
“አባቴ ሲሞቱ ነው የመጣሁ?”
“ንግድ ጀመሩ ማለት ነው?”
“ሰው ቤት ተቀጥሬ አገለግል ነበር”
“ከዛ ለራሴም ንግድ ከፈትኩ፡፡ አሁን ዝግ ነው፡፡”
“እነ አቶ ጎሣዬ ገዳንና ወይዘሮ ዘነበችን ያቁዋቸዋል?”
“አዎ… ዘመድ ነን!”
“የዘሙቴ ቤትዎን ማን ይጠብቀዋል?”
“አሉ የወንድም የእህት ልጆቼ - የተዳሩ የተኳሉ!”
“እንሰቱን ምኑን? ከብቱን የሚጠብቅ አለ?
“አለ! እንዴ ሶስት ክፍል ቤት አለ፡፡ የከብቶች ቤት፣ ሳሎን፣ ዕቃ ቤት በኣመት በሁለት ዓመት እንገባለን እኛ …”
አሁን እነፀሐይነሽ መጡ፡፡ ፀሐይነሽ የአቶ ታደሰ ልጅ ናት፡፡ አንደኛዋ እህታቸው ናት፡፡
“ዘመቴ ነበርሽ አደል?” አልኳት፡፡
“አዎ”
እነፀሐይነሽ ብዙ ሆነው ነበር የመጡት፡፡ በዓመት በሁለት ዓመት እሄዳለሁ እያሉ ነው ብዬ ለፀሐይነሽ ስነግራት “በአለፈው አሜሪካን ነበር ጋሼ (አባቷ ማለት ነው)፡፡ አንዴ ደሞ ትንሽ ታመመ” ገለፀችልኝ፡፡ “ዘንድሮ ግን ግድ ይዘነው መሄድ አለብን አልን እግዚሐር ይመስገን ቢያመውም እሺ ብሎን ሄድን፡፡”
“በርከት ብላችሁ ደስ ትሉ ነበር”
“አዎን እሱም ደስ ብሎት ነበር”
አቶ ታደሰ ወደኔ እያሳዩ፤ “እሳቸውም ገቡ” አሉ፡፡
“ዲያቆን ከሆኑ ጥሩ የቅዳሴ ድምፅ ነበረዎታ?” አልኳቸው ጣልቃ ገብቼ፡፡
“መቼም ደህና ሳይሆን አይቀርም አሁነ አረጀሁ”
“አጎቶችና ወንድሞችዎስ? ስለ አባ ወልዶስ ምን ያውቃሉ?”
“አባ ወልዶ ሲባል … ጎሳ ነው፡፡”
“አባ ወልዴ ኬት መጡ?”
“ከጎንደር ነዋ! ትውልዳቸው ጎንደር ነው፡፡ የመጡት ኪዳነምህረት ነው መጀመሪያ”
“ለምን መጡ”
“አባ ወልዶ እንግዲህ ቄስ ካህን ናቸው .. ከሳቸው ጀምሮ እኛ ድረስ ካህን ነን! አባ ወልዶ ብዙ ወልደው ብዙ ካህን ፈጥረዋል! በየቤተክርስቲያኑ ተበትነዋል የካህን ዘር ናቸው! እስከ 7 ትውልድ ድረስ ካህን ናቸው! አዲሳባም እኮ የአባ ወልዶ ሰዎች አሉ፡፡ እነ ኃይሉ፣ ባህሩ፣ ጉልላት ወዘተ..”
አባ ወልዶ ዕድር የሚባለውስ?”
“አለ - እዚህ አገር፡፡”
“መርካቶ?”
“አዎ”
“ሁላችንም ዕድሩ ላይ አለን - ልጆቻችንም”
“መምሬ ወልዴ መምሬ ደበላ መምሬ ሀብተማርያም መምሬ ምህረቱ - ዋና ዋናዎቹ ካህናት ናቸው፡፡”
“ዘሙቴ የካህናት ዝርያ ገዳም ነው ለማለት ይቻላላ! የእርሶ ልጆችስ ካህናት አልሆኑም?”
“እነሱ ንግድ ውስጥ ገቡ - አበቃ!... ዋጮ ከእኛ በላይ ነው
የእኛ ዋና ሥር፤ ወልዴ ደምቢሶ - ደበላ ደምቢሶ፣ ምህረቱ ደምቢሶ፣ ተክሌ ደምቢሶ
እነዚህ አራት ሰዎች ናቸው ዋርካዎች!”
“ማሪያንም በምን አገለገሉዋት
“በድቁና፣ አባቴ እያለ ሳር ጎጆዋን ቆርቆሮ አለበስኳት፡፡ ቄሶቹን አልብሻለሁ፡፡
የቤተክርስያኗን አልባሳትም ረድቻለሁ! …
እ …የዘሙቴ ዕቁብ በመሰብሰብ ለዘሙቴ እርዳታ እንዲውል አድርጌያለሁ! መምህራን፣ ዲያቆናት፣ ቄሶችን ይዤ እገባለሁ! አሁን ተረካቢዎችና ተተኪዎች እነ ግርማ መጥተዋል፡፡
ለቅዳሴ የመጡ ምዕመናንን በሬ አርደው ያበሉ ነበር፤ ብላ ፀሐይነሽ ጨመረችበት፡፡
“ከሞላ ዲባቦ (አሁን በህይወት ያሉ) ጋር አዲሱን መንገድ ለመስራት አግዣለሁ፡፡ ት/ቤትም እዚያ መኪና ያቆማችሁሙበት አካባቢ ተሰርቷል፡፡”
“ህክምናስ?”
ዘና መድኀኒዓለም - እነ ወይዘሮ ታደለች ጤፍ ኬላ እየሰሩ ነው፤ አሉ?”
“አዎ ሰምቻለሁ” አለ፡፡
እንዳቶ ታደሰ ግምት፤ የዘሙቴ ህዝብ ግምቱ 2000 ህዝብ ገደማ ነው፡፡
ቤተክርስቲያኗ በዘሙቴ እድር በሌላም መዋጮ መጠናከር አለባት፡፡ ዘሙቴ በሚኒልክ ጊዜ እንደነበረች የሚነገርላት ናት! በጠላት ጊዜ ፅላቷን ሊያጠፋ የመጣውን ጠላት ነብር ከጫካ ወጥቶ እንዳዳነው ይነገራል፡፡ ሁለተኛ ጊዜ ሌባ ፅላቱን ሊወስድ መጥቶ እባብ ተጠምጥሞበት አድኖታል፤ ይባላል፡፡
ዘሙቴ ለመግባት አበሳ የሚያበላ ዳገት ነበረ አሉ፡፡ በአምባሬ በአጨበር በኩል ተመጥቶ ነው ተራራው ጫፍ ሚደረሰው፡፡ ታቹን ወንዝ አለ፡፡ በወንዙ ታጥቦ ነው ዘሙቴ እሚገባው፡፡
ይህን ዳገት የወጡ የወረዱ 19 ዓመት ያስቆጠረው የዘሙቴ ማርያም ወዳጅነት ማኅበር አባላት፣ በፍቅር፣ በፉክክር፣ በመውደቅ በመነሳት፣ ይህን ተራራ ያውቁታል፡፡ ለሙሽራ ሚዜ ሆነው መጥተውበታል፡፡ ዘመድ ጥየቃ ተመላልሰውበታል፡፡ እነዚህ ማህበርተኞች እንደተለመደው መደበኛ የማህበር ስርዓተ - መዋቅር፡- ሊቀመንበር፣ ፀሐፊ፣ ገንዘብ ያዥ ሳያስፈልጋቸው፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን፣ መተዛዘንን፣ መተጋገዝን፣ ሐሙስ ሐሙስ መገናኘትን ብቻ ባህል አድርገው ቆይተዋል፡፡ 15 አባላት አሉት ማህበሩ፡፡ ሁሉም እኩል ይተሳሰባሉ፡፡ ትውውቃቸውና መተሳሰባቸው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡
አባላቱ 18ኛ ዓመት በዓላቸውን ሲያከብሩ ያሉትን ብጠቅስ ተገቢ ፍንጭ ይሰጠናል፡-
“… ይህ ማህበር እንዲህ ያለ ደረጃ ደርሶ ከመዋቀሩ በፊት የተጀመረው በጥቂት ወንድማማችና አብሮ አደጎች ነበር፡፡… ከሳምንት ሳምንት ሳንለያይ እየተቀራረብን፣ እየተዝናናን እናሳልፍ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሻይ ቡና ቢበዛ ጠላ እንጠጣ ነበር፡፡
ኋላ ግን ተሳታፊው ቁጥር ሲበዛ ልዩ ስሙ ጎርደሜ በሚባል ሰፈር አሁን በሀገር ውስጥ በሌለው ጓደኛችን በበድሉ እንዳለ ቤት ለረጅም ጊዜ መሰብሰብ ጀመርን፡፡ ይህ እያደገ ሄዶ በ1987 ዓ.ም በአቶ ዳኜ ዓለሙ በተከፈተው እንቁጣጣሽ ሆቴል ማታ ማታ እየተሰባሰብን መጨዋወት ቀጠልን፡፡
(ለጥቂት ጊዜ ተቋርጦ) በወንድማችን በአቶ ግርማ አበበ ወ/ማርም ሰርግ ምክንያት ሚያዚያ 27 1997 ዓ.ም በጉራጌ ዞን ወደምትገኘው ዘሙቴ ገባን፡፡ በድጋሚም በመስቀል በዓልና ለመልስ በ1998 ዓ.ም ዘሙቴ በመሄድ በዓሉን ካከበርን በኋላ ለምን በስፍራው በምትገኘው በዘሙቴ ማሪያም ቤተክርስቲያን ስም ማህበራችንን አንሰይምም የሚል ሃሳብ መጣ፡፡ … በ2001 ዓ.ም 15ኛ ዓመታችን በአቶ ግርማ አበበ ወ/ማርያም ቤት ተከብሮ በየዓመቱ እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡”
ታዲያ ዛሬ ዘሙቴ ሄደው በዓሉን እንዴት አከበሩ? የዘሙቴ ማርያም አከባበርና ክብረ - በኣል ምን ይመስል ነበር? ምን አስገራሚ አጋጣሚዎች አገኘሁ? ሁሉም የሚሉት አላቸው፡፡ አንዱ ወዳጄ ግን “የአባቴን ትዕዛዝ ስፈጽም ህሊናዬ አባቴን ማግኛ መንገድ የፈጠረልኝ ይመስለኛል” ይላል፡፡ ለምን? መልሱን በሚቀጥለው ሳምንት አወጋችኋለሁ፡፡ ታላቅ ወንድሙ ደግሞ “እዚህ ቦታ በባህላዊ መንገድ ጋብቻ እንድፈፅም አባቴ ያለኝን በማክበሬ የተባረኩ ይመስለኛል!” ይላል፡፡ ለምን? የሱንም በሚቀጥለው ሳምንት፡፡
(ይቀጥላል!)

Read 3809 times