Monday, 20 October 2014 08:38

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(63 votes)

    ማታ ከራት በኋላ መኝታ ክፍሌ ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ፡፡ በሩ ተንኳኳና ከፈትኩት፡፡ ጋናዊቷ ሄለንና ሲዳናዊቷ አህላም ቆመዋል፡፡ ተዘግቶ ከነበረው በር በስተጀርባ እንደ እኔ ለሥልጠና የመጡ ሴቶች ቆመው አያለሁ የሚል ደቃቅ ግምት እንኳን ስላልነበረኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ እኔ ዩኒቨርሲቲ ስማር ሴቶች ወደ ወንዶች፤ ወንዶችም ወደ ሴቶች መኝታ ክፍል ድርሽ እንዲሉ አይፈቀድም ነበር፡፡ ግር ቢለኝም ቀድሜ፣ “ታዲያስ! እንዴት ናችሁ?” ያልኳቸው እኔ ነበርኩ፡፡ ፊቴ ግን፣ “ምነው በሰላም ነው ወደ ወንዶች ዶርም የመጣችሁት?” የሚል ጥያቄ ከአንደበቴ በላይ ጮኸ እንደጠየቃቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ምናልባት በቃል ካቀረብኩት ሰላምታ ይልቅ ፊቴ ላይ የተንፀባረቀው ጥያቄ በጉልህ ተሰምቷት ይሆናል፤ ጋናዊቷ ሄለን ለሰላምታዬ ምላሽ ሳትሰጥ፣ “አህላም አብረኸን ወደ ባሩ እንድንሄድ ትፈልጋለች፡፡” አለችኝ ፈገግ ብላ፡፡ ከእንግሊዝኛዋ ከምዕራብ አፍሪካ ከመጡ ሰልጣኞች ጋር ጭራሽ የማይነፃፀር ጥርት ብሎ የሚሰማ ነው፡፡ ዩጋንዳ የገባሁት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር፡፡ እዚህ በምዕራብ ዩጋንዳ፣ ኪባሌ ደን ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ወደሚገኘው የማካራሬ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ሥልጠና ጣቢያ ከሌሎች ሃያ ስድስት ሠልጣኞች ጋር የደረስነው ትላንት ነው፡፡
“አህላም ራሷ አትናገርም እንዴ ሄለን የምታወራላት?” ብዬ እያሰብኩ ዞር ብዬ በትዝብት ሳያት፣ ሱዳናዊቷ አህላም፣ “አዎ፣ ከእኛ ጋር እንድትመጣ ፈልገን ነበር፡፡” ብላ ቀይ ፊቷን በውብ ፈገግታ አደመቀችው፡፡ ፊቷ ላይ የዋህነትና ግልጽነት ይነበባል፡፡ ረጅምና ደርባባ ናት፡፡
መኝታ ክፍሌ ተንኳክቶ በሴቶች ስጋበዝ ከኩራት ይልቅ የተሰማኝ መደነቅ ነበር፡፡ የእኛ አገር ሴቶች መቼም እንዲህ አያደርጉም፡፡ ሱዳኖች እንዲህ ያደርጋሉ ማለት ነው? … አልመሰለኝም፡፡ አህላም የተለየች መሆን አለባት፡፡ ወይም ከእኔ ጋር ማምሸት እንደምትፈልግ ስትነግራት ሄለን አደፋፍራት ይሆናል ወደ መኝታ ክፍሌ የመጡት፡፡ … ለነገሩ ከሌሎች አፍሪካውያን ይልቅ እኔ ከሷ ጋር የሚቀራረብ መልክ አለኝ፡፡ ገና ካሁኑ ዘመዶቿን ናፈቀች ማለት ነው? ብዬ እያሰብኩ፣ ሰለቀኑ ውሏቸው እየጠየቅኳቸው ወደ ባሩ ስንወርድ አህላም ቁጥብ ለመሆን ሞከረች፡፡ እንግሊዝኛዋ ጥሩ ፍሰት የለውም እንጂ ለመግባቢያ በቂ ነው፡፡ ባሩ በረንዳ ላይ ተቀምጠን ለስላሳ ጠጣን፤ ዳማ ተጫወትን፡፡ አህላም ወሬ ለመፍጠር አልሞከረችም፡፡ ጭምት ሆነችብኝ፡፡ አንደበቷን ገና በእንግሊዝኛ ስላላፍታታችም የፈለገችውን እንደልብ ለማውራት ይቸግራታል፡፡ ከሷ ይልቅ በጣም ጥሩ እንግሊዝኛ ከምታወራው ከሄለን ጋር ብዙ ሳናወራ አልቀረንም፡፡ ከሷ ጋር ብዙ ባንጫወትም አህላም አጠገቧ በመቀመጤ ደስተኛ ነበረች፡፡
(ከደራሲ ኢዮብ ጌታሁን “አለላ መልኮች” የተሰኘ ልብወለድ የተቀነጨበ)

Read 8239 times