Saturday, 25 October 2014 10:04

በኢ/ር ግዛቸው ስልጣን መልቀቅ የደንብ ጥሰት አልተፈፀመም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ ፕሬዚዳንት ካቢኔያቸውን አዋቅረዋል

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸው የፓርቲው የዲሞክራሲ ባህል የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላከተ ነው ያለው ፓርቲው፤ በሂደቱ ላይም የደንብ ጥሰት እንዳልተፈፀመ አስታውቋል፡፡ “አንዳንድ ወገኖች በሽግግሩ የደንብ ጥሰት የተፈጸመ በማስመሰል ጫጫታ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው” ያለው ፓርቲው፤ የስልጣን ሽግግሩ ደንቡን ተከትሎ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ሂደት ያለፈና የፀደቀ ነው ብሏል፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በገዛ ፍቃዳቸው ለፓርቲው ቀጣይ ጉዞ ይበጃል በማለት ስልጣን መልቀቃቸው የፓርቲው የዲሞክራሲ ባህል የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱ በትክክል የታየበት፣ ፓርቲው በተሻለ ቁመና እንዲጓዝ በር የከፈተ ትልቅ እርምጃ በመሆኑ ሊደነቅ እንደሚገባው ጠቁሞ፤ አንድነት ልዩነቶችን በውይይትና በመረጋጋት መፍታት የሚችል፣ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ልምድ ያለው ፓርቲ እንደሆነ አሳይቷል ብሏል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ፤ ካቢኔያቸውን አቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን የጠቆመው አንድነት፤ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግም ፓርቲውን የማጥራትና የማስተካከል ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው አንዳንድ የዳያስፖራ ደጋፊዎች ፓርቲውን በገንዘባቸው ለመጠምዘዝ ይፈልጋሉ በማለት ሥልጣን የለቀቁት በተፅዕኖ እንደሆነ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ የፓርቲው ተጠባባቂ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም በበኩላቸው፤ በዚህ አይስማሙም፡፡ “ኢ/ሩ ለብሄራዊ ምክር ቤቱ የገለፁት ከህሊናቸው ጋር ተማክረው ለፓርቲው ቀጣይ ሂደት ይጠቅማል በሚል በገዛ ፍቃዳቸው ስልጠናቸውን መልቀቃቸውን እንጂ በተፅዕኖ ነው የለቀቅሁት አላሉም” ብለዋል፡፡ በግፊትና በተፅዕኖ ነው የለቀቁት የሚለው አያስኬድም ያሉት አቶ አስራት፤ “ኢ/ር ግዛቸው ሌላ ፍላጎት ቢኖራቸው የስልጣን ገደባቸው እስኪጠናቀቅ ፓርቲውን መምራት ይችሉ ነበር፤ ሆኖም ለፓርቲው ይበጃል ያሉትን እርምጃ ወስደዋል” ብለዋል፡፡
ኢ/ር ግዛቸው የፓርቲው ህልውና ተጠብቆ እንዲጓዝ ትልቅ እርምጃ መውሰዳቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣን ለመልቀቅ በመወሰናቸው ፓርቲው በእጅጉ ያከብራቸዋል፤ በቀጣይም  አመራሩን በምክር ያግዛሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል - ኢ/ር ግዛቸው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆነው እንደሚቀጥሉ በማመልከት፡፡በፓርቲው ዙሪያ ብዙ አፍራሽ አስተያየቶች እየተሰነዘረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አስራት፤ አሁን ያለው አመራር የፓርቲውን ቀጣይ ህልውና ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ቀጣዩን ምርጫ ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ አዲሱ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ ባለፈው እሁድ 12 አባላት ያሉት የስራ አስፈጻሚ አባላት መርጠው በም/ቤቱ አፀድቀዋል፡፡ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ ዋና ፀሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ፣ የማህበር ጉዳይ ኃላፊ አቶ አለነ ማህፀነቱ፣ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ደምሴ መንግስቱ፣ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ብሩ ብርመጂ፣ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ እንግዳ ወልደፃድቅ ሲሆኑ ቀደም ሲል ከኢ/ር ግዛቸው ጋር መስራት አንችልም በማለት ከስራ አስፈፃሚነታቸው ለቀው የነበሩት አቶ ተክሌ በቀለ እና አቶ ዳንኤል ተፈራ በአዲሱ አመራር ውስጥ ተካትተዋል፡፡ የፓርላማ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉም የስራ አስፈፃሚው አባል ሆነዋል፡፡  

Read 2111 times