Saturday, 25 October 2014 10:05

ጠበቃውን ገድለዋል የተባሉት ባለሃብት በቁጥጥር ስር ዋሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በሐዋሳ ከተማ የህግ ባለሙያውን አቶ ዳንኤል ዋለልኝን በጥይት ገድለው ተሰውረዋል ተብለው የተጠረጠሩት ባለሃብት ከ12 ቀናት የፖሊስ ክትትል በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፖሊስ ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ተጠርጣሪው ባለሃብት አቶ ታምራት ሙሉ ባለፈው እሁድ አዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
በአሁን ሰዓትም ለደህንነታቸው ሲባል ይርጋለም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የደቡብ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ታስረው እንደሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
 ባለሃብቱ ብሉናይል እና ኢቪኒንግ ስታር የተባሉ ሆቴሎች የነበራቸው ሲሆን፤ ኢቪኒንግ ስታር የተባለውን ሆቴላቸውን ለአንድ ባለሀብት ከሸጡ በኋላ በተፈጠረ አለመግባባት ለፍርድ ቤት ክስ አቅርበው እንደነበርና ሟች አቶ ዳንኤል ውክልና ወስደው ሲከራከሩ እንደነበር ታውቋል
ተጠርጣሪው “ለምን ከጠላቶቼ ጎን ቆምክ” በሚል ምክንያት በጠበቃው ላይ ግድያውን ሳይፈፅሙ እንዳልቀረ የሟች ቤተሰቦች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን ግለሰቡ ቀደም ሲል በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ወንጀል 12 ዓመት ተፈርዶባቸው በፖሊስ ሲፈለጉ እንደነበር ታውቋል፡፡
ተጠርጣሪው መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ዳሽን ባንክ ህንፃ ላይ ወደ ሚገኘው የሟች ቢሮ ከጠዋቱ 2፡30 ላይ በመግባት ሰላምታ የሚያቀርቡ መስለው በታጠቁት ሽጉጥ ግድያውን እንደፈፀሙና የሟችን ረዳት እንዳቆሰሉ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ሟች አቶ ዳንኤል ዋለልኝ በሃዋሳ ከተማ የታወቁ የህግ ባለሙያ እምደመነሩ የሚገልፁት ቤተሰቦቻቸው፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በህግ መምህርነት ከማገልገላቸውም ባሻገር ላለፉት 3 ዓመታት በጠበቃነትና በህግ አማካሪነት ሲሰሩ እንዲቆዩ ጠቁመዋል፡፡  


Read 2957 times