Saturday, 25 October 2014 10:11

“ከክፉ በሬ ጋር ውለህ፣ ወደክፉ ሚስት አትሂድ” የአፍሪካ ተረት

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሚስቱ ላይ የሚኮራ የሚኩራራ ጉረኛ ባል ነበረ፡፡ አንድ ማታ ሲመጣ ክፉኛ ተፈንክቷል፡፡
“ምነው ውዴ! ምን ነካህ?” አለችው ሚስቱ፡፡
“ዛሬ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” አለና ጀመረ፡፡
“ምን ሆነ የእኔ ጌታ?”
“አንዱ አጉል ልታይ ልታይ ባይ ጉራውን ሲነዛ አግኝቼው ‹እረፍ!› አልኩት”
“ማ? ማነው እሚያርፈው?” አለኝ፡፡
“አንተ ነሃ! ካንተ ሌላ ጉራ እሚነዛ አለ እንዴ?”
“አፍህ ካላረፈ እኔ ራሴ አሳርፍሃለሁ! አይለኝም?!”
‹በቃ ወጣ ብለን መተያየት ነዋ!› አልኩትና ቀድሜ ወጣሁ ከቡና ቤቱ፡፡”
ሚስትየውም “ከዛስ?” አለችው፡፡
ባል “እሱም ተከትሎኝ ወጣ!”
ሚስት “ከዛስ?”
ባል “ቀድሜ ቡጢ አቀመስኩት”
ሚስት “ከዛስ? ወደቀ?”
“አይ አልወደቀም”
“ታዲያ ምን ሆነ እሺ?”
“ተቀማመስን”
“ከዚያስ?”
“ከዚያማ እንደምታይኝ ተፈነከትኩ”
“ይሄማ ቡጢ አይደለም!... ዱላ ይዞ ነበር?”
“አይ አንቺ! ወንድ መስሎሻል? ዱላ ይዞ የሚዞር፣ የእኔኑ ነጥቆ ነው እንጂ!?”
*  *    *
የሀገራችን ታሪክ ይሄው ነው! ዱላ ያልያዘው መቺ ነው! ምነው ቢሉ፤ ባለ ዱላው ያቀብለዋልና! ተከራካሪው የሚያቀርበውን ሙግት ተፃራሪው ወስዶ ይሟገትበታል፡፡ “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣልም” ነው፡፡ ያም ሆኖ የማታ ማታ ዱላ አቀብሎ ለመፈንከት አጉል መፎከር የቂል ቆንሲል መሆን ነው፡፡ ውስጠ - ሚስጥሩ ጥልቅ ነው፡፡ እነ ሆቺ ሚን በየዋሁ ዘመን “የመሣሪያ ምንጫችን ጠላታችን እራሱ ነው ይሉ ነበር!” ዛሬ ያ የሞኝነት መንገድ ይመስላል!
ችግር እያለብን ችግር የለብንም አንበል፡፡ “መንግስት ማለት የአገሩ አዕምሮ እንጂ የልቡ ሮሮ ብቻ አይደለም” ይላል የአገራችን ዋና ገጣሚ፡፡ ይህን አንርሳ!
“የአብራሄ - ህሊና፣ ዘመን  ፈላስፎች እነስፒኖዛ፣
ሎክ፣ ካንት፣ ሚል፣ ቮልቴር እና ዘመናዊዎቹ እነ ራሰልና ፐፐር … ሁሉም፡፡ ህይወት ማለት ችግር መፍታት ነው፤ ይላሉ፡፡ ምንም ፍፁም ነገር የለም! እድገት ሊመጣ የሚችለው ጥብቅና ኮስታራ እሳቤ ካለ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከጭንቀት ነፃ የሆነ ነፃነትና ለታላቅነት ዕውቅና የመስጠት ብቃት ሲኖር ነው፡፡ ግን ድክመትን ለማሳየት አለመፍራት! ካለ ነው!” ይላሉ፡፡ የተባለውን ማጣራት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ህይወት ማለት ችግር መፍታት ነውና፡፡ ይህን ያላስተዋለ በችግር ላይ ችግር ቢፈጥር ውጤቱን እሱና እሱ ብቻ ነው የሚያገኘው!!
ከትዕዛዝ አክባሪነት ይልቅ ምክን ሊመራን ይገባል (ስፒኖዛ)፡፡  ትዕዛዝ አለማክበር በፍፁም ግብረገብነት አኳያ ሲታይ እንደጥፋት ይቆጠር ይሆናል፡፡ እንደሎሌነት ሲታሰብ ግን ትዕዛዝን መበገር አግባብ ይሆናል፡፡ ጌታ የሚያዘው የጌትነቱን ልክ ማሳያ አድርጎ ነውና!! አንዳንዴ “ልጅነትን የመሰለ ንፅህና የለም” የሚባለውን ለመቀበል መገደድ አግባብ ነው”፡፡ ቅንነት ወሳኝ ነው ለማለት ነው! ከትላንት ለመማር ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ ቂም በቀል ሆድ ውስጥ ካመቅን ነገ ተመልሰን ወደዚያው ስህተት እናመራለን፡፡ ያ ከሆነ ከድጡ ወደማጡ መሄድ ነው፡፡ በራሳችን የትላንት ንፍቀ ክበብ ታጥረን፣ ሌላ ለማየት ተገድበን ያለፈው መርግ ከተጫነን፤ አባዜው አልለቀቀንም ማለት ነው፡፡ ገጣሚው እንዳለው፡-
“ያለፈው አልፏል እያልን፣ ዛሬም ወደዚያው ከሄድን
ድግግሞሹ ካጫጨን፣ እኛስ ከትላንት ምን ተሻልን?!”
ከክፋት ወደ ክፋት፣ ከኋላ ቀርነት ወደ ኋላቀርነት፣ ከጥፋት ወደ ጥፋት እንዳንሄድ አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡ በስራም ቦታ፣ በፖለቲካ ዳርትም ሥፍራ፣ በህዝብ መሰብሰቢያም ሸንጎ፣ በኮንፈረንስና በሴሚናርም፣ በማህበረሰብም፣ በቤተሰብም፣ መልካም ነገሮችን ካላቆየን፤ ከአንዱ ወደ አንዱ መሄድ ከውድቀት ወደ ውድቀት፤ ከድቀት ወደ ድቀት እንደ መጓዝ ነው፡፡ የሀገራችን ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፤
“ያገሬ ሰው ነገር፤ አብረን ወደላይ እንብቀል ሲሉት፤ አሸብልቆ ወደታች ወደመሬት ማጎንቆል” ይሆናል፡፡ የዚህ ውጤቱ የአፍሪካው ተረት ነው - “ከክፉ በሬ ጋር ውለህ፣ ወደ ክፉ ሚስት አትሂድ!”


Read 8714 times