Saturday, 25 October 2014 10:13

የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የመንግሥት ስልጠና

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“ስልጠናው ለመማር ማስተማሩ የጨመረው ነገር የለም” - መምህር
“ስልጠናው ውጤታማ ነው፤ መግባባትም ተፈጥሯል” - መንግሥት

    ለዩኒቨርሲቲ መምህራን በመንግስት ፖሊሲዎችና በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከተሰጠው  ስልጠና ምንም አዲስ ነገር አለማግኘታቸውን የተናገሩ ሰልጣኞች፤ ለአስር ቀናት የዘለቀው ስልጠና ውጤታማ ነበር ለማለት አያስደፍርም ይላሉ፡፡  መንግስት በበኩሉ፤ ለተማሪዎችም ሆነ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የተሰጠው ስልጠና ለበርካቶች ግንዛቤ እንደፈጠረና ውጤታማ እንደነበርም ገልጿል፡፡ ከአብዛኛው ሰልጣኝ ጋርም መግባባት ተፈጥሯል ይላል፤ መንግስት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ በቆየው ስልጠና፣ በቀን 4 ጊዜ አቴንዳንስ (የተሳታፊ መቆጣጠሪያ መዝገብ) ላይ እየፈረሙ መሳተፋቸውን የሚናገሩት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “ስልጠናው፤ ኢህአዴግ በኔ ካመናችሁ መንግስተ ሰማያት ትገባላችሁ በሚል ምሁራኑን ለራሱ ፖሊሲ ማስፈፀሚያነት ለመጠቀም የተንቀሳቀሰበት ነው” ብለዋል፡፡
በስልጠናው የታዘቡትን የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፤ ተሳታፊዎች እሳቸው ከጠበቁት በላይ  የሃገሪቱን ዋና ዋና የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ማንሳታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከመደብ ጥያቄ እስከ አካዳሚክ ነፃነት ድረስ እንዲሁም ስለ ሙስና፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ፌደራሊዝምና የመሳሰሉት ጉዳዮችም በስፋት ተነስቷል፤ ነገር ግን በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ከመድረኩ በቂ ምላሽ አልተገኘም ባይ ናቸው - ምሁሩ፡፡
በስልጠናው ወቅት የዩኒቨርሲቲ መምህራኑን እንደተማሪ ቆጥረው በቀን 4 ጊዜ የተሳታፊ መቆጣጠሪያ መዝገብ ላይ ማስፈረማቸው ስልጠናው በግድ የተካሄደ ነው የሚያሰኝ ነው ብለዋል፤ ዶ/ር መረራ፡፡ መምህራኑ በተለይ የአካዳሚክ ነፃነትን በተመለከተ ላነሱት ጥያቄ አሰልጣኞቹ ምላሽ መስጠት ተስኗቸው፣ ነገሮችን አድበስብሶ ለማለፍ ሲሞክሩ እንደነበር ያስታወሱት ምሁሩ፤ በብሄራዊ መግባባትና በሃይማኖት ነፃነት ላይ የቀረቡ ሃሳቦች ብዙ ጥያቄና ሰፊ ክርክር እንዳስነሱ ተናግረዋል፡፡  
“ለምንድን ነው ከብሄራዊ እርቅ የምትሸሹት? አሁን እንኳ ወደኛ ስትመጡ የእባብ ልብ ይዛችሁ ነው” የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሲቀርቡ ታዝቤያለሁ ያሉት ዶ/ር መራራ፤ ስልጠናው መምህራን በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ስሜታቸውን ያንፀባረቁበት፣ ቀድሞ በሃገሩ ጉዳይ ላይ ዝምታን መርጦ የነበረው ሁሉ ከተኛበት ተነስቶ  ጠንከር ያለ አስተያየትና ጥያቄ ያቀረበበት ነበር ብለዋል፡፡ በተለይ ስለ ወደብ ብዙ ጥያቄ መቅረቡን የገለፁት ምሁሩ፤ ኢህአዴግ የተኛውን ጭምር  በራሱ ላይ የቀሰቀሰበት መድረክ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነፅሁፍ ምሁር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ ለመምህራኑ የተሰጠው ስልጠና ቀድሞ ከሚታወቁት ጉዳዮች የተለየ አዲስ ነገር ይዞ የቀረበ አይደለም ብለዋል፡፡ የማወያያ ሰነዶች የተባሉትም ሆነ ርዕሰ ጉዳዮቹ ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆኑና የመንግሥትን አቋም የሚያንፀባርቁ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ምናልባት መንግሥት ምሁራኑ ያላቸውን አስተሳሰብና ምልከታ ለማወቅ ይረዳው እንደሆን እንጂ፣ ለመምህራኑ የሚጨምረው አዲስ እሴት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ያሉት ዶ/ር በድሉ፤ በመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቦርድ  ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ካሣ ተክለብርሃን በተመራው ውይይት ላይ ስለትምህርትና ተያያዥ ጉዳዮች ከመነሳቱ ውጪ በሌሎች ቀናት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ብቻ ለውይይት መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ “ያም ቢሆን ከመምህራኑ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ የተገኘበትና ለችግሮች መፍትሄ ያበጀ ነው ለማለት አያስደፍርም” ብለዋል፤ መምህሩ፡፡
አንድ ስልጠና ወይም ስብሰባ ውጤታማ ሆነ ሊባል የሚችለው ከስብሰባው በፊት ያለው ነገር ከስብሰባው በኋላ ሲለይ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ በስልጠናው ከዚህ አንፃር አዲስ ነገር ተፈጥሯል ማለት እንደማይቻልና ውጤታማ ነበር ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የመብራት መቋረጥ ችግር እንዳለ የጠቆሙት ዶ/ር በድሉ፤ ለስልጠናው በወጣው ወጪ ጀነሬተር ቢገዛበት በመማር ማስተማር ሂደት ላይ በተግባር የሚታይ ለውጥ ያመጣ ነበረ ሲሉ ተችተዋል፡፡ ስልጠናው ለመማር ማስተማሩ ሂደት የጨመረው ነገር የለም ብለዋል - ምሁሩ፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በዩኒቨርስቲው የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ክፍል መምህር፤ ስልጠናው ቀድሞ ከሚታወቁ ጉዳዮች የተለየ አዲስ ነገር ይዞ ያልመጣ፣ የሚታወቁና የነበሩ ነገሮችን የደጋገመ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ በፖለቲካው ዙሪያ የተነሱ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን ተቀብሎ በጉዳዮቹ ላይ ማስተካከያ እናደርጋለን ወይም አስተያየቶቹን ተቀብለናል የሚል ነገር ከመድረክ መሪዎቹ አልሰማሁም ያሉት መምህሩ፤ “እውነታው ይሄ ነው፤ በቃ ተቀበሉ አይነት መድረክ ነበር” ይላሉ፡፡
መንግሥት ከማን ጋር ምን መስራት እንደሚፈልግ እንደማያውቅ፣ በተለይ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምሁራኖችንና ኤክስፐርቶችን ያለመጠቀም ችግር እንዳለበት የተረዳሁበት አጋጣሚ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ለምሳሌ የድንበር ጉዳይን ከምህንድስና ባለሙያዎች ጋር ከመወያየት ይልቅ ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ጋር መወያየት ይሻል ነበር ብለዋል፡፡
በቀን 4 ጊዜ ‘አቴንዳንስ’ መቆጣጠር በራሱ አስገራሚ ነበር ያሉት መምህሩ፤ ሂደቱ በዚህ መልክ ባይሆን ይመረጥ እንደነበር ጠቁመው ስልጠናው በብዙ መመዘኛ ማራኪና ውጤታማ ነበር ለማለት ይከብደኛል ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ክፍል መምህር እንዳሉት፤ ስልጠናው መከናወኑ የሚነቀፍ ባይሆንም ለስልጠናው የተመረጡት ርእሰ ጉዳዮች ግን ምሁራኑን የሚመጥኑ አይደሉም፡፡ “ብዙ የተመራመሩ ምሁራኖች ባሉበት መድረክ ስለ ሃይማኖት ገለልተኝነት፣ ስለ ኒዮሊበራሊዝም፣ ስለ ፌደራሊዝም የመሳሰሉትን ጉዳዮች አንስቶ በዚህ ዙሪያ እውቀት ያጥራችኋል፤ እናሰልጥናችሁ መባሉ ተገቢ አልነበረም” ያሉት መምህሩ፤ አሰልጣኞቹ ኋላ ላይ ለቀረቡላቸው ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እያቃታቸው ከመምህራኑ ጋር ይፋጠጡ ነበር ብለዋል፡፡
ስልጠናው ውጤታማ ነበር ወይንስ አልነበረም የሚለውን የስልጠናው ባለቤት ራሱ ቢገመግም መልካም ነው ያሉት መምህሩ፤ በግላቸው ቀድሞ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ከነበራቸው እውቀት የተለየ የጨመረላቸው ነገር እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
በዚያው ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ሌላው ስሜ አይጠቀስ ያሉ አስተያየት ሰጪ፣ ስልጠናው አቴንዳንስ የሚያዝበት ቢሆንም ከ10 ቀናት ውስጥ ለ3 ቀናት ብቻ ስልጠናው ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ በወቅቱ ሲነሱ የነበሩት ሃገራዊ ጉዳዮች ጥሩ እንደነበሩና የውይይት መድረክ አይነት ስሜት እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡ “እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ውይይት የሚካሄድባቸው መድረኮች ላይ ተሳትፌ አላውቅም” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ ለሌላቸው ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል፡፡ በተለይ በሳይንሱ ዘርፍ ሀገሪቱ የበለጠ ለማደግ ያላት ፍላጐት የሚበረታታ ነው የሚሉት መምህሩ፤ በቀጣይ መንግሥት ከምሁራኑ ጋር ተቀራርቦ መስራት አለበት፣ በየጊዜውም ከፖለቲካው ባሻገር በችግሮቻችን ላይ ውይይቶች መካሄድ አለባቸው ሲሉ መክረዋል፡፡
በቅርቡ ከአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርነታቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት የዩኒቨርሲቲ መምህር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፤ በስልጠናው ላይ ለአንድ ቀን ብቻ መሳተፋቸውን ገልፀው በቀሪዎቹ ቀናት አለመሳተፋቸውን፣ ስልጠናው አስፈላጊ አልነበረም ብለው እንደሚያምኑም፡፡
አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ፖለቲከኛ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ በስልጠናው ሙሉ ለሙሉ ባይሳተፉም ሰነዶቹ የፓርቲውን ፕሮግራምና አላማ እንዲሁም ርዕዮተ ዓለም የማስረፅ ሚና ያላቸው እንጂ እንደተባለው በመንግስት ፖሊሲዎች ላይ የሚሰጥ ስልጠና ሆኖ እንዳላገኙት ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው ለመምህራንና ተማሪዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠና የመጪው ምርጫ ቅስቀሳ አካል እንደሆነ መገንዘባቸውንም ፕ/ር በየነ ገልፀዋል፡፡ መንግስት ፖሊሲውንና የልማት ስራውን ለማስገንዘብ ብቻ አቅዶ የተንቀሳቀሰ ቢሆን ኖሮ ከስልጠና ይልቅ ሴሚናርና ዎርክሾፕ ማዘጋጀት ይበቃው ነበር ያሉት መምህሩ፤ የፓርቲ አጀንዳን በመንግስት ሃብትና መዋቅር ማስረፅ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በሁለተኛው መደበኛ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ስብሰባ ላይ በም/ቤቱ አባላት ለቀረቡ የማሻሻያ ሞሽኖችና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ “ለዩኒቨርስቲ መምህራንና ተማሪዎች በተሰጠው ስልጠና መንግሥት በተለያዩ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ሃሳቦችን አቅርቧል፤ መምህራንና ተማሪዎቹም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመስላቸውን ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል፤ በዚህም እጅግ ከአብዛኛው ሰው ጋር መግባባት ፈጥረናል” ብለዋል፡፡ ከመምህራኑ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ዩኒቨርስቲዎች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ በእውቀትና በክህሎታቸው የድርሻቸውን ለመወጣት መስማማታቸውንና መጓጓታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከመምህራኑ ጋር የተደረገው ውይይትም ስኬታማ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውይይቱ የሀገራዊ መግባባቱ አካል ነው ብለዋል፡፡ ለተማሪዎች በተሰጠው ስልጠና ላይም የጠባብነትና ትምክህተኝነት አስተሳሰቦች ላይ ውይይት ተደርጐ አመርቂ ውጤት እንደተገኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አክለው ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በነሐሴ ወር ላይ የተጀመረው ስልጠና፣ በአሁኑ ወቅት ለመንግሥት ሠራተኞች እየተሰጠ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  


Read 2106 times