Saturday, 25 October 2014 10:32

በ2 ደቂቃ 70 በመቶ ‘ቻርጅ’ የሚደረግ የሞባይል ባትሪ ተሰራ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

        ሲንጋፖር ውስጥ የሚገኘው የናንያንግ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ2 ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ቻርጅ ተደርጎ 70 በመቶ ሃይል ማጠራቀም የሚችልና ለ20 አመታት ያህል አገልግሎት መስጠት የሚችል የተሻሻለ ዘመናዊ የሞባይል ባትሪ መስራታቸው ተዘገበ፡፡
 ሳይንስ ዴይሊ ድረገጽ እንዳስነበበው፣ ተመራማሪዎቹ ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረውን ግራፋይት የተባለ የባትሪ አካል ከቲታኒየም ዳይ ኦክሳይድ በተሰራ የተሻሻለ መሳሪያ በመተካት ነው፣ ሃይል የማጠራቀም አቅሙ ከፍተኛ የሆነ አዲስ የሞባይል ባትሪ የሰሩት፡፡
ይህ የባትሪው አካል የኬሚካል ኡደቱን የሚያፋጥን ሲሆን፣ ባትሪው ተደጋግሞ ቻርጅ መደረግ የሚችልበት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አስችሎታል ተብሏል፡፡ መደበኛው ሊቲየም አይዎን ባትሪ በአገልግሎት ዘመኑ ሃይል የማጠራቀም አቅሙ ምንም ሳይቀንስ በተደጋጋሚ ቻርጅ ሊደረግ የሚችለው ለ500 ጊዜያት ያህል ብቻ ሲሆን፣ አዲሱ ባትሪ ግን እስከ 10 ሺህ ያህል ጊዜያት ቻርጅ ሊደረግ ይችላል፡፡ አዲሱ የሞባይል ባትሪ በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ በብዛት ተመርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡
ሳይንቲስቶቹ ከሞባይል ባትሪው በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን ባትሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ አሻሽለው የመስራት እቅድ እንዳላቸው ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

Read 2137 times