Saturday, 25 October 2014 10:33

“አዲስ ቢልድ” ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂን የሚያስቃኘው “5ኛው አዲስ ቢልድ ኮንስትራክሽን” ትናንት ተከፈተ፡፡ ኤግዚቢሽኑ እስከ ማክሰኞ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ በኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቱርክ፣ ከግብፅ፣ ከጀርመን፣ ከኢጣሊያ፣ ከቻይና፣ ከሕንድ፣ ከፊንላንድ፣ ከተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከሞሮኮ፣ ከግሪክ፣ ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር መድረክ መፍጠር ያስችላል ተብሏል፡፡
ከቱርክ ከ50 በላይ፣ ከአውሮፓና ከሌሎች አገሮች ከ25 በላይና ከኢትዮጵያ ከ20 በላይ ኩባንያዎች በኤግዚቢሽኑ እየተሳተፉ ሲሆን ከውጭ አገር ኩባንያዎች ዋና ዋናዎቹ ቢኬቲ ጎማ አምራች፣ አልካአያ እብነበረድ፣ ዚዛያን፣ ፎርሙላና ካልድ ፓይፕ አምራች፣ ጉሲያን የኤሌክትሪክ ዕቃዎች አምራች፣ ካስታሞኑ የእንጨት ዕቃዎች አምራች ሲሆኑ ከአገር ውስጥ ደግሞ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፣ በርታ ትሬድ፣ ዩታፍ አሉሙኒየም፣ ሄንግሰን ላምበር ማኑፋክቸሪንግ ኤድናሞል፣ ፊስኮም ኢንጂነሪንግ፣ የምብካል ጄኔራል ኢምፖርት ኤክስፖርት፣ ቬዴዲያስ ኤምፖርት፣ የቤል ኢንዱስትሪያል ጥቂቶቹ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
በኤግዚቢሽኑ የሚቀርቡት የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና ዕቃዎች፣ ሳተላይት ሲስተም፣ የመታጠቢያ ቤት ዕቃዎች፣ የግድግዳ ንጣፎች፣ ኬብሎች፣ የደህንነትና የሴኩሪቲ ዕቃዎች፣ የወለል ንጣፎች፣ የጋዝ ዕቃዎች፣ መግጠሚያ፣ መዝጊያዎች፣ ጄኔሬተሮች፣ እብነበረድ፣ የግራናይትና ሴራሚክስ ዕቃዎች፣ የኪችን ዕቃዎችና መሳሪያዎች፣ ፒቪሲ ማሽኖች፣ የብረት ምርቶች ጥቂቱ ናቸው፡፡

Read 1574 times