Saturday, 25 October 2014 10:43

“...በኤችአይቪ ቫይረስ መያዝ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ ከመውለድ አያግድም...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

የኤችአይቪ ቫይረስ በወሊድ፣ በእርግዝና እንዲሁም በጡት ማጥባት ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው ተገቢው የህክምና ክትትል ካልተደረገም የመተላለፍ እድሉ ከ25-35% የጨመረ ነው፡፡
 Prevention of Mother-to-Child Transmission (PMTCT) of HIV/AIDS in Ethiopia: IntraHealth  International/Hareg Project End-of-Project Report: September 15, 2004 - December 31, 2007
ደሴ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር PMTCT ኤችአይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚሰራባቸው የተለያዩ የግል የህክምና ተቋማት ከሚገኙባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነች፡፡ እነዚህ ህክምና ተቋማት እናቶች ተመርምረው እራሳቸውን እንዲያውቁ ብሎም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ እየሰሩ ያሉትን ስራ በጥቂቱ ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ በባቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ያገኘናቸውን ሲስተር ዘነበች መኮንንን እናስቀድም፡፡ በሆስፒታሉ ያለው የነብሰጡር እናቶች ክትትል ምን ይመስላል? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ እንዲህ ብለውናል፡-
“ሆስፒታሉ ይህን አገልግሎት በመስጠት ቀደምት እንደመሆኑ መጠን ክትትላችን ጥሩ     ነው አንድ እናት ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ልጅ እንድትወልድ ነው የምንፈልገው ስለዚህ     ነብሰጡር እናቶች ሲመጡ ቅድሚያ የኢችአይቪ ምርመራ እንዲያደርጉ የምክር     አገልግሎት እናደርጋቸዋለን የምንሰጣቸው ከዛ በኋላ ፈቃደኛ ከሆኑ ምርመራ     ይደረግላቸዋል ፖዘቲቭ ከሆኑ መድሀኒቱን ለመጀመር እንዲያስችላቸው በሳምንቱ  ሲዲፎራቸውን እንለካለን ከዛም በየስድስት ወሩ ያለውን ለውጥ እናያለን ይህም     መድሀኒት ከመጀመራቸው በፊትና ከዛ በኋላ ያለውን ለውጥ እንድናውቅ ይረዳናል፡፡”     ጨምረውም ሆስፒታሉ ለደሴ ከተማ ነዋሪዎች ብቻም ሳይሆን ባቅራቢያው ለሚገኘው    ማለትም ከሰሜን ሸዋ፣ ከሚሴ፣ አጣዬ፣ ሸዋሮቢትና ኮምቦልቻ እንዲሁም በደሴ ዙሪያ     ከሚገኙት አሳይታ፣ ዱብቲ፣ ወልዲያ፣ መርሳ፣ ውጫሌና ሀይቅ ለሚመጡ ነዋሪዎችም     ጭምር ግልጋሎት እንደሚሰጥ ገልፀውልናል፡፡
የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ያወቀች እናት ለትዳር አጋሯ እንዲሁም ለሌሎች የቤተሰብ አባላት በግልፅ መንገሯ ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳይዛመት በይበልጥም እናቲቱ የሚያስፈልጋትን እንክብካቤ እንድታገኝ በማድረግ እረገድ የሚኖረው አስተዋፅኦ ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ይሁንና ከቫይረሱ ጋር የምትኖር አንዲት እናት ወደ ሌሎች የህክምና ተቋማት ስትሄድ ሊደረግላት የሚገባውን እንክብካቤ በሚመለከትም የሚከተለውን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡-“ቫይረሱ በደሟ የተገኘባት እናት መጀመሪያ ለማን መንገር እንዳለባት ምክር     እንሰጣታለን ለባሏ፣ ለምትቀርበው ዘመድ ለእህትም ይሁን ለጓደኛ ማሳወቅ     እንዳለባት እንነግራታለን፤ እንዳንዶች ፈቃደኝ አይሆኑም፡፡
ከባላቸው እራሱ ይደብቃሉ፡፡ ቤቴ ይፈርሳል በሚል ለባላቸው እንኩዋን አይነግሩም፡፡ PMTCT     ኤችአይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለው የህክምና አገልግሎት     አንዲት ነብሰጡር እናት ምንም እንኳን ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ቢኖርም የህክምና     ክትትል በማድረግ ብቻ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መውለድ እንድትችል የሚደረግበት አገልግሎት ነው፡፡
 ሲስተር ዘነበች እንደገለፁልን ሆስፒታላቸው ይህን አገልግሎት በተሟላ መልኩ በመስጠቱ ቀደም ሲል የነበረው የህፃናት ሞት እንዲሁም በቫይረሱ መያዝ በእጅጉ ቀንሷል፡፡ “አገልግሎቱን ከጀመርን በኋላ የተወለዱት ህፃናቶች ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ ቀንሷል” ሲሉ የሚከለተውን ብለውናል፡-
“በአሁኑ ሰአት ምንም አያስፈራም ምክንያቱም ሰዉ ስለ ኤችአይቪ ያለው ግንዛቤ ጥሩ ነው፡፡ ቀደም ሲል ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ነሽ የሚል ውጤት ሲሰሙ በጣም ይደነግጣሉ፡፡ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ አሁን ግን የትኛዋም እናት ስትመጣ የኤችአይቪ ምርመራ እናደርግላሻለን ስንላት በቀላሉ ትቀበለናለች ፖዘቲቭ ብትሆን እንኳን ጉጉቷ ልጇ ነፃ ሆኖ እንዲወለድላት ነው ስለዚህ የመተላለፍ እድሉም ቀንሷል የሰዉም ግንዛቤ ጥሩ ነው፡፡”  
             -----------///----------
በቀጣይ ያነጋገርናቸው በደሴ አዲስ ህይወት ሆስፒታል ያገኘናቸው ሲስተር አዝመራ ስዩምን ነው፤ ”...ሆስፒታላችን በወር ከመቶ ሀያ እስከ መቶ ሰላሳ ለሚሆኑ እናቶች የእርግዝና ክትትል አግልግሎት ይሰጣል፡፡ ባሳለፍነው ነሀሴ ከተመረመሩት እናቶች ውስጥም ሶስቱ ብቻ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል ይህም ቁጥር ካለፈው ጋር ሲነፃፀር እጅግ ትንሽ ነው” በማለት ሲስተር አበባ ይገልፃሉ፡፡ የህክምና ገልግሎቱን እንዲሁም በታካሚዎቹ ዘንድ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች የሰጡንን ምላሽ እነሆ፡-
ጥ፡ አንዲት እናት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ነሽ ስትባል እንዴት ነው የምትቀበለው እናንተስ እንዴት ነው የምታነጋግሯት?
መ፡ በዚህ ላይ ስልጠና ወስደናል ስለዚህ መጀመሪያ ከመመርመራችን በፊት የምክር አገልግሎት እንሰጣቸዋለን፡፡ በኋላ ላይ ውጤቱን ስንነግራቸው አዲስ  አይሆንባቸውም፡፡ ከዛም በኋላ መድሀኒቱን ማቋረጥ እንደሌለባቸው የእድሜ ልክ እንደሆነ በደንብ እንነግራቸዋለን ስለዚህ ብዙም ችግር አይኖርም፡፡
ጥ፡     ለክትትል የመጡ ሁሉ እናንተ ጋር ይወልዳሉ?
መ፡     ብዙዎቹ እኛ ጋር አይወልዱም፡፡ ምክንያቱም ከቦታ እርቀት፣ ከትራንስፖርት እጥረት     ወይም ከገንዘብ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች ለአንድ ግዜ ክትትል ነው     የሚመጡት፡፡    የተወሰኑት ግን እኛ ጋር ይወልዳሉ፡፡
ጥ፡    ወደ ገጠሩ አካባቢ ያሉትን እናቶችስ በምን መልኩ ነው የምታስተምሯቸው?  
መ፡     ኤችአይቪ ይኑራትም አይኑራትም አንዲት እናት በህክምና ብትወልድ ነው የሚመረጠው፡፡ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ካለ ደግሞ እቤት መውለድ ለእሷም፣     ለልጇም፣ ለሚያዋልዷትም ሰዎች መልካም ስለማይሆን ልጇም ጤነኛ ሆኖ     እንዲወለድ ለእራሷም ጤንነት ወደ ጤና ተቋም ሄዳ እንድትወልድ እንገፋፋታለን፡፡
ጥ፡     ከወለዱስ በኋላ ለክትትል ይመጣሉ ታገኙዋቸዋላችሁ?
መ፡  በድጋሚ ለመውለድ ካልሆነ ብዙ ግዜ አይመጡም፡፡ ከሩቅ ስለሆነም የሚመጡት     መውለጃቸው ሲቀርብ ይታያሉ ከዛ በኋላ ባሉበት ቦታ ነው የሚወልዱት፡፡
ጥ፡     ልጆቹ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይኑር አይኑር እንዴት ማወቅ ይቻላል?
መ፡     ክትትላቸውን በሚያደሩጉ ግዜ ያለውን ነገር እንነግራቸዋለን፡፡ ተመልሰው የማይመጡ     ከሆነ ግን ባሉበት እንዲከታተሉ እንነግራቸዋለን፡፡
መ፡     የትዳር ጉዋደኞች (ባሎች) አብረው ለምርመራ ይመጣሉ?
መ፡     ብዙዎቹ አይመጡም፡፡ እንዲት እናት ገና ለእርግዝና ክትትል ሰትመጣ ባለቤቷ     አብሯት እንዲመጣ እንጠይቃታለን፡፡ አብሯት ከመጣ የምክር አገልግሎት ሰጥተን     ምርመራውን እናደርጋለን፡፡ ያለውን ሁኔታ እናት እንዴት መውለድ እንዳለባት፣ ምን     አይነት እንክብካቤ እንደሚደረግላት፣ እናት ህይወት እየሰጠች ህይወት ማጣት     እንደደሌለባት በሰፊው እንነግራቸዋለን፡፡
                                          --------------///---------------
ዶክተር ምስጋናው ከፍተኛ ክሊኒክ በደሴ ከተማ አገልግሎቱን በመስጠት ይታወቃል ሲስተር ዛሀራ አሊን PMTCT ክፍል ውስጥ ነው ያገኘናት፡፡
    “...በቫይረሱ መያዝ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መውለድ አያግድም በሚለው ሀሳብ     ትስማማለች ምክንያቱ ደግሞ በሆስፒታሉ ቁጥራቸው ሰላሳ አምስት የሚሆኑ ቫይረሱ     በደማቸው ያለ መድሀቱን የጀመሩ እናቶች ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ እንዲወልዱ በማስቻሉ     ነው፡፡
እናቶቹ መድኒቱን መጀመራቸው ታካሚዎቹን እንደልብ ለማግኘት እንደሚረዳ ይገልፃሉ
“አንድ እናት ፖዘቲቭ ከሆነች መድሀኒቱን ወዲያው ነው የምንጀምርላቸው ስለዚህ ሁልጊዜም አናጣቸውም”
አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና መገልገያ እቃዎች አቅርቦትንም በተመለከተ ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ
“አንዳንዴ ችግር ይፈጠራል፡፡ ነገርግን ይህነው የሚባል ችግር አልገጠመንም”
ሲስተር ዘሃራ አሊ በሆስፒታሉ የምትታወቅበት አንድ አገልግሎት አለ፡፡ ይኼውም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እናቶች ምርመራውን በጸጋ ተቀብለው ክትትሉን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን አሰራር ለመዘርጋት ቅርበትን መፍጠር የሚለው ነው፡፡ ሲ/ር ዘሀራ እንደገለጸችው፡-
“...አንዲት እናት ከቫይረሱ ጋር እንደምትኖር ውጤቱ ሲያሳይ እኔ ሴትየዋን ማግባባት እና የተፈጠረው ነገር ምንም እንዳልሆነ እንዲያውም በጊዜው ተመርምራ እራስዋን     በማወቅዋ እድለኛ መሆንዋን በዚህ የህክምና ዘዴ እራስዋን በደንብ መከታተል እንደምትችል ...ወዘተ እነግራታለሁ፡፡
 ከዚያም በስልክ በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙኝ እንደሚችሉ ቃል ስለምገባላቸው በምሽት ሁሉ ይደውሉልኛል፡፡ በዚህ መንገድ ቅርበትን     ስለምፈጥርላቸው በጥሩ ስሜት ወደእኔጋ ይመጣሉ፡፡ ሕክምናቸውም ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡”

Read 5802 times