Saturday, 25 October 2014 11:00

የታገቱት ናይጀሪያውያን ልጃገረዶች እስከ ሰኞ ይለቀቃሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

* ተኩስ ሊያቆምና ያገተውን ሊፈታ ተስማምቷል የተባለው ቦኮ ሃራም፣ ግድያና ጠለፋውን ቀጥሏል

   ቦኮ ሃራም የተባለው የናይጀሪያ አሸባሪ ቡድን፣ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሸሪያ ህግ ተግባራዊ እንዲሆን የማስቻል አላማውን ለማሳካት ባለፉት አምስት አመታት፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን እንደፈጸመና ከ5ሺህ በላይ ናይጀሪያውያንን እንደገደለ ይነገራል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ሚያዝያ ወር ቺቦክ ወደተባለችው ከተማ ድንገት ብቅ ብሎ የፈጸመው ድርጊት ግን፣ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ የታጠቁ የቦኮ ሃራም ወታደሮች፣ አገር አማን ብለው ወደ ትምህርት ቤታቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ 276 ልጃገረዶችን አፍነው፣ ወዳልታወቀ ስፍራ አጋዙ፡፡
ይህ ድርጊት የአገሪቱን መንግስት፣ የልጃገረዶቹን ወላጆችና የቺቦክ ከተማ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ናይጀሪያዊና አፍሪካውያንን ብሎም አለምን አስደነገጠ፡፡ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው አስተጋቡት፡፡ በአሸባሪው ቡድን የታገቱት ናይጀሪያውያን ልጃገረዶች ዕጣ ፋንታ ብዙዎችን አስጨነቀ፡፡
የተወሰኑ ልጃገረዶች ለማምለጥ ቢችሉም፣ እንደታገቱ ያሉት 219 ያህል ልጃገረዶች ጉዳይ ይህ ነው የሚባል እልባት ሳያገኝ ስድስት ወራት አለፉ፡፡ የአገሪቱ መንግስት ያሰረብኝን ታጣቂዎቼን ካልፈታ፣ ልጃገረዶቹን ለባርነት እሸጣለሁ በማለት ሲዝት የቆየው ቡድኑ፤ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን አጠናክሮ እንደገፋበት ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“አላህ ልጃገረዶቹን መሸጥ እንዳለብኝ ነግሮኛል፡፡ እሸጣቸዋለሁ፡፡” ብሏል የቦኮ ሃራም መሪ ነኝ ያለ ግለሰብ ከሶስት ሳምንታት በፊት በይፋ፡፡የናይጀሪያ መንግስትም ለታገቱት ዜጎቹ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም የሚል ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ የጦር ሃይል አባላት የሆኑ ወታደሮችም፣ መንግስት የቡድኑን ጥቃት በተገቢው ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል ድጋፍ እያደረገላቸው አለመሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ሲኤንኤን፣ የአሜሪካ መንግስት እገታው ከተፈጸመ ከአንድ ወር በኋላ፣ ልጃገረዶቹን የሚያፈላልጉ 80 አሜሪካውያን ወታደሮችን ወደ ቻድ መላኩን አስታውሷል፡፡በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ግን፣ የናይጀሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተስፋ ሰጪ መግለጫ አወጡ፡፡ የአገሪቱ መንግስት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ባለፈው ሳምንት በቻድ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙንና ቡድኑ ያገታቸውን ልጃገረዶች ለመልቀቅ መስማማቱን አስታወቁ፡፡
በጀርመን መዲና በርሊን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የናይጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሚኑ ዋሊ በበኩላቸው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ስምምነት ላይ መደረሱንና ልጃገረዶቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚለቀቁ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
“አሸባሪ ቡድኑ ልጃገረዶቹን እስከ መጪው ሰኞ ለመልቀቅ ተስማምቷል” ብለዋል፡፡ የናይጀሪያ መንግስት ቃል አቀባይ ማይክ ኦሜሪም፤ የታገቱት ልጃገረዶች በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ቦኮ ሃራም በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የራሱን መግለጫ አለማውጣቱ ብዙዎችን አጠራጥሯቸዋል፡፡ የአለማቀፍ ፖለቲካ ተንታኞችም በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰውን ስምምነት በጥርጣሬ እንደሚያዩት አስታውቀዋል፡፡
ቡድኑ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ዓላማውን ለማሳካት በጦርነት ሊቀጥል ይችላል የሚሉት እነዚሁ ተንታኞች፣ ስምምነቱን ያደረገውም የበለጠ ለመደራጀትና ራሱን ለማጠናከር የሚሆን ጊዜ ለመግዛት ሲል እንደሚሆን ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ከቡድኑ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን ቢያስታውቅም፣ የቦኮ ሃራም አባላት እንደሆኑ የተነገረላቸው ታጣቂዎች ግን በሁለት መንደሮችና በአንድ ከተማ ላይ በከፈቱት ተኩስ ስምንት ያህል ሰዎችን ሲገድሉ፣ ሌሎች ልጃገረዶችንም አግተዋል፡፡

Read 2879 times