Saturday, 25 October 2014 11:02

የካናዳው የተኩስ ጥቃት አነጋጋሪ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ጥቃቱ ከአይሲስ ጋር ሊያያዝ ይችላል እየተባለ ነው
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ በካናዳ ርዕሰ መዲና ኦትዋ በሚገኘው የአገሪቱ የጦርነት መታሰቢያ አደባባይና በፓርላማ ውስጥ በተከሰተውና ሁለት ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የተኩስ ጥቃት ዙሪያ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሲ ኤን ኤን ዘገበ፡፡
ሚካኤል ዜሃፍ ቢቤው የተባለ የታጠቀ ግለሰብ፣  የአገሪቱን የጦርነት መታሰቢያ አደባባይ በመጠበቅ ላይ በነበሩ ሁለት ወታደሮች ላይ ተኩስ በመክፈት አንደኛውን የገደለ ሲሆን፣ ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሌሎች ሶስት ወታደሮችን ካቆሰለ በኋላ የግለሰቡ ህይወት ማለፉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በአገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ንግግር እያደረጉ የነበሩት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሃርፐር ጉዳዩን በተመለከተ ረቡዕ ምሽት በሰጡት መግለጫ፣ አገሪቱ በመሰል ጥቃቶችና ነውጦች እንደማትሸበር ገልጸው፣ ጥቃቱ ካናዳ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ጽንፈኝነትን ለመዋጋት የያዘችውን አቋም የበለጠ እንድታጠናክር የሚያደርግ ነው፤ ጽንፈኞች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ምቹ ቦታ አያገኙም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቃቱን የፈጸመው ሚካኤል ዜሃፍ ቢቤው የተባለ ግለሰብ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ማንነቱንም ሆነ ድርጊቱን ለመፈጸም ያነሳሳውን ምክንያትና አላማውን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ያልሰጡ ሲሆን፣ ስለአሸባሪው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና ሌሎች ተባባሪዎች እንዳሉት ለማጣራት የተጀመረው ምርመራ በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጤት ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡በወሩ መጀመሪያ ላይም የካናዳ መንግስት በኢራቅ የሚገኙ የአይሲስ ታጣቂዎችን ለማጥቃት በሚደረገው ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እቅድ እንዳለው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞ አንድ የአገሪቱ ወታደር አሸባሪ ተብሎ በተጠረጠረ ግለሰብ ሞንትሪያል ውስጥ በመኪና ተገጭቶ መገደሉን ተከትሎም፣ አገሪቱ ያለባትን የሽብር ስጋት መጠን ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ ከፍ ማድረጓን አስታውሷል፡፡
ካናዳ አይሲስ የተባለውን ጽንፈኛ ቡድን ለመዋጋት በተጀመረው አለማቀፍ እንቅስቃሴ እንደምትሳተፍ በይፋ ማስታወቋንና በቡድኑ ላይ ለሚደረገው የአየር ድብደባ ላይ የሚሳተፉ ስድስት ተዋጊ ጀቶችን ለመላክ መወሰኗን ተከትሎ ጥቃቱ መከሰቱ፣ ጉዳዩ ከአይሲስ ጋር ተያያዥ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩን ዘገባው አስታውቋል፡፡አይሲስ ካናዳውያንን ለሽብር ጥቃት እየመለመለ እንደሆነ በቅርቡ ማስታወቁን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርትም፣ 130 ያህል ካናዳውያንም ወደሌሎች አገራት በመሄድ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር መቀላቀላቸውንና ከእነዚህ ውስጥም 30 የሚሆኑት በሶርያ በሚካሄደው ጦርነት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ማስታወቁን ገልጧል፡፡
በአገሪቱ መሰል የሽብር ጥቃቶች በጂሃዲስቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ ይገመት እንደነበር የጠቆመው ሲ ኤን ኤን፤ አሜሪካም መረጃ አግኝቻለሁ በማለት በቅርቡ በካናዳ በሚገኘው ኤምባሲዋና ቆንስላዋ ላይ ያለውን የደህንነት ሁኔታ በጥብቅ መከታተል መጀመሯን አስታውሷል፡፡አይሲስም ሆነ ሌሎች ቡድኖች ለጥቃቱ ሃላፊነት አለመውሰዳቸውን የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤትም አይሲስ ወይም ሌሎች የሽብር ቡድኖች ከጥቃቱ ጋር በቀጥታ እንደሚያያዙ የሰጠው መግለጫ በይፋ ባያስታውቅም፣ በጉዳዩ ላይ ጥብቅ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ቢቢሲ በበኩሉ፤ በካናዳ የተለያዩ የጽንፈኛ ቡድኖች አባላትና ግለሰቦች አክራሪነትን መስበክ ከጀመሩ መቆየታቸውን በመጥቀስ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ብጥብጦችን መፍጠር እንደሚገባ ብዙዎችን ማሳመን መቻላቸውን ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ 90 ተጠርጣሪዎችን ያሳተፉና ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ 63 የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮችን በመመርመር ላይ እንደሚገኝ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁንም አስታውሷል፡፡
Read 3826 times