Monday, 03 November 2014 07:27

ክቡር ፕሬዚደንት ይቅር ብለናል ግን…

Written by  አብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል
Rate this item
(1 Vote)

           የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ንግግር በማድረግ የዓመቱን የሕግ አወጣጥ መርሐ-ግብር (Legislative Program) ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ የዘንድሮው የፕሬዚደንቱ ንግግር ለየት ያለ ሃሳብ የተካተተበት መሆኑን አስተውያለሁ፡፡ ክቡር ፕሬዚዳንቱ በኢህአዴግ የሃያ አራት ዓመት የአስተዳደር ዘመን ተገልፆ የማያውቅ ቃል መናገራቸውንም አድምጫለሁ፡፡ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት እንዳየነው፣ ኢህአዴግ በታሪኩ በርዕሰ ብሔር ደረጃ ቀርቶ በተራ ካድሬ ደረጃ ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ አያውቅም፡፡ ዘንድሮ ግን የመብራት መቆራረጥን በተመለከተ በክቡር ፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ በማካተት በይፋ ይቅርታ ጠይቋል፡፡
ኢህአዴግ ይህንን ያደረገው “ካንጀት” ይሁን “ካንገት” ባይታወቅም፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አሊያም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለተፈጸመ ስህተት ይቅርታ መጠየቅ የስልጡንነት ምልክት እንጂ፣ ሽንፈትንም ሆነ ድክመትንም የሚያሳይ አይደለም፡፡ መሳሳትም ሆነ ድክመት በኢህአዴግ የተጀመረ ይመስል ኢህአዴግ ይህንን ቃል ለዘመናት ለምን ሲፈራውና ሲሸሸው እንደኖረ ግን ከቶም ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ ነው፡፡ እነሆ! ዘንድሮ ይህንን እንደ መርግ የከበደ ቃል ከሀገሪቱ የመጀመሪያው ሰው (ከርዕሰ ብሔሩ) አንደበት ሰምተናል፡፡ እናም ይህንኑ ቃል መነሻ በማድረግ ይህቺን ማስታወሻ ለክቡር ፕሬዚዳንቱ ይድረስ ማለትን ወደደሁ፡፡
ክቡር ፕሬዝደንት! የማይሳሳት የማይሰራ ብቻ ነው፡፡ እናም ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት እኔና ቤተሰቤ መንግስትዎን (መንግስታችንን) በይፋ ይቅር ብለናል፡፡ ይቅር ያልነው ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስታችንን ፈርተንና ተሸማቀን ሳይሆን፤ ይቅርታ መጠየቅ የጀመረው ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስታችን ይቅርታ መጠየቅ የሚያሳፍር መስሎት “ተሸማቆ” ይቅርታ መጠየቅ እንዳያቆም በማሰብ ነው፡፡
ክቡር ፕሬዝደንት! የእርስዎን ፕሬዝዳንታዊ ንግግር ካዳመጥን በኋላ “እውነት የመብራት መቆራረጥ ብቻ ነው እንዴ ይቅርታ ሊጠየቅበት የሚገባው ጉዳይ?” የሚለውን ጥያቄ እኔና ቤተሰቤ አንስተን ተወያይተናል፡፡ ለቀረበው የይቅርታ ጥያቄ “ይቅር” ብንልም ይቅርታ ሊጠየቅበት የሚገባው ጉዳይ ግን “የመብራት መቆራረጥ” ብቻ አለመሆኑን በታላቅ አክብሮት ልንገልጽልዎ እንወዳለን፡፡ የእኛ ይቅርታ እርስዎ ለዜጎች እንደሚያደርጉት ይቅርታና ምህረት “ፍትህ ሚኒስቴር ይየው፣ መንግስት ያቅርበው፣ ምናምን…” ማለት ስለማያስፈልገው በኛ በኩል ይቅርታ ላልቀረበባቸውም ጉዳዮች ሁሉ ይቅር ብለናል፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ የእኛን ፈለግ ተከትሎ ይቅር እንደሚልም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ክቡር ፕሬዝደንት! “ይቅርታ ሊጠየቅበት የሚገባው ጉዳይ የመብራት መቆራረጥ ብቻ አይደለም” የምንለው ከመሬት ተነስተን አይደለም፡፡ ይህንን ለማስረገጥ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የእርስዎንም የዚህን ጋዜጣ አንባቢዎችንም ጊዜ ላለማባከን ከመብራት፣ ከውሃና ከትራንስፖርት ጋር የተያያዙ ጥቂት ማሳያዎችን ብቻ አነሳለሁ፡፡
እኔና ቤተሰቤ የምንኖረው በኦሮሚያ ክልል፣ ፊንፊኔ ዙሪያ ዞን፣ ለገዳዲ - ለገጣፎ ከተማ ነው፡፡ የለገዳዲ - ለገጣፎ ከተማ ከአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ጋር ያለው ቅርበት የዓይንና የአፍንጫን ያህል ነው፡፡ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለው ድንበር የጣሊያኗን ሮም እና የቫቲካን ሲቲን እስኪመስል ድረስ ተገጣጥመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በቤት ኪራይ የተማረሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ወደ ታዳጊዋ ለገጣፎ ተሻግረው መኖር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ለገጣፎ ብቻ ሳትሆን በአጠቃላይ በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ ከተሞች የአዲስ አበባን ችግር እያቃለሉ በመሆኑ፤ ቀደም ሲል የነበሩት የእነዚህ ከተሞች መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ የሕዝቡን ፍላጎት መሸከም አልቻሉም፡፡ ከነዚህ የመሰረተ ልማት ችግሮች አንዱ መብራት ነው፡፡
ክቡር ፕሬዝደንት! እርስዎ በዓመታዊ ንግግርዎ የጠቀሱት “የመብራት መቆራረጥ”ን በተመለከተ ነው፡፡ የለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ ችግር ግን የመቆራረጥ ችግር ብቻ አደለም፡፡ ቀድሞ ነገር መብራት መቼ ገባልንና ነው የሚቆራረጠው ክቡር ፕሬዝደንት?! መቆራረጥ ብቻማ ቢሆን ያው እን’ዳገር እንሆን ነበር፡፡ ከአዲስ አበባም ከመብራት ኃይልም ጓሮ የምትገኘውና የአዲስ አበባን ችግር ባልጠና ጀርባዋ የተሸከመችው የለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ነዋሪዋ በቤቱ የመብራት ቆጣሪ አልገባለትም፡፡
ክቡር ፕሬዚደንት! የመብራት ጎርፍ በደጃፋችን አልፎ በሰሜንም በደቡብም ያሉ የገጠር ከተሞችን ብርሃን በብርሃን ሲያደርግ እዚሁ ፊንፊኔ ጓሮ ተቀምጠን ሰማይ ጠቀስ የመብራት ኃይል ምሰሶዎችን ተደግፈን እንቆዝማለን፡፡
በኩራዝም በፋኖስም፣ በሻማም በእንጨትም በደህና ከምንኖርበት ሁኔታ መብራት ኃይል “አለሁላችሁ” ብሎ እንድንጠቀም አደረገን፡፡ ከተማችን እየሰፋች ስትመጣ መብራት ኃይል “የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ” ማለት አበዛ፡፡ እዚህ ላይ ‘ታዲያ እንዴት ሆናችሁ ነው እየኖራችሁ ያላችሁት?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ በኔ የመሀይም ግምት ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የለገዳዲ-ለገጣፎ ነዋሪ በአሁኑ ወቅት መብራት የሚያገኘው ቀደም ሲል መብራት ከገባላቸው ወንድሞችና እህቶች በቀጫጭን ገመዶች እየወሰደ ነው፡፡  
አንዴ በግንድ፣ ሌላ ጊዜ በስኒ፣ ቆየት ብሎ በቆጣሪ፣… መታጣት እየተመካኘ ለገዳዲ-ለገጣፎ መብራት አሮባታል፡፡ ክቡር ፕሬዝደንት! እግር ጥሎዎት ወደ ለገጣፎ ቢመጡ በቀጫጭን ሽቦዎች፣ በቀጫጭን አጣናዎች ሁለት ሦስት ኪሎ ሜትር አቆራርጠው የሚሄዱ የመብራት ገመዶችን፤ አሊያም ከወዲያ ወዲህ፣ ከወዲህ ወዲያ የተዳወሩ የመብራት ገመዶች የሸረሪት ድር መስለው ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡
ይህ ብቻ አደለም፤ ሰሞኑን በመንደራችን ስዘዋወር ምን እንዳየሁ ያውቃሉ ክቡር ፕሬዝደንት!? መብራት በአንዲት መስመር ብቻ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ሲወሰድ ነው ያየሁት፡፡ ነገሩ ገረመኝና “ሁለተኛው መስመር የት አለ?” በማለት ጠየቅሁ፡፡ “ና ጉድ ተመልከት!” አሉና እውነትም “ጉድ” አሳዩኝ፡፡ ጫፏ ወሃ በያዘች ኩባያ ውስጥ የተነከረች አንዲት የኤሌክትሪክ ገመድ አሳዩኝ፡፡ መቼስ ኤሌክትሪክ ብርሃን የሚሰጠው በፖዘቲቭ እና በኔጋቲቭ (በእሳትና በውሃ ይሉታል ባለሙያዎች) መስመሮች አይደል?... አዎ! እሳቱን ከጎረቤት ውሃውን ከቤት አቀናጅቶ መብራት ያገኛል የለገዳዲ-ለገጣፎ ሕዝብ፡፡ ነገሩ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ ነው፡፡ በጥንቃቄ ጉድለት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ግን አስቡት! - በተለይ ምንም በማያውቁት ሕፃናት ላይ…!
የመብራት ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ነገር ልጨምር፡፡ ክቡር ፕሬዝደንት! በለገጣፎ ከተማ አንዲት አምፑል የመንገድ መብራት የለም፡፡ በአካባቢያችን ያን ያህል የከፋ ወሮበላ ባያስቸግረንም እኛን ብቻ ሳይሆን እኛን አልፎ አዲስ አበቤውን እያስቸገረ ያለው የጅብ መንጋ ሕፃናት ልጆቻችንን ሸክፈን ገና በአስራ ሁለት ሰዓት ቤታችን እንድንከተት እያደረገን ነው፡፡ ከመሸ መንቀሳቀስ ችግር ነው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር ልጆች የማታ ትምህርት መማር አልቻሉም፡፡
በእርግጥ እነዚህ ችግሮች የአካባቢያችን መስተዳደር የሥራ በድርሻ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ክቡር ፕሬዝደንት! እነሱስ ቢሆኑ በበላይ አካል “እንዲህ አድርጉ” ቢባሉ ምን ይላቸዋል? እንዲያውም ፕሬዝዳንታዊ ቃል ከንጉሳዊ ቃል የሚለይ ስለሆነ ተሰሚነቱ የላቀ ነው፡፡
ክቡር ፕሬዝደንት! የከተማችን አመራር ከኮብል ስቶንና ከውሃ ወይም ከመብራት ለእኛ የትኛው መቅደም እንዳለበት እንኳ ስላልገባው፣ ውሃና መብራቱን ትቶ የኮብል ስቶን መንገድ ሲሰራና ሲመርቅ ይውላል፡፡
እግራችንን ጭቃ እንዳይነካው ከሚጨነቅ ለሆዳችን ቢጨነቅልን የተሻለ ነበር፡፡ አብስለን የምንመገብበት ውሃና መብራት ትኩረት እንዲያገኝ ቢያደርግልን ወግ ያለው ሥራ ነው፡፡ ጭቃውን በቦት ጫማ እንወጣዋለን፡፡ እናም የኮብልስቶን በጀት ለጊዜው ወደ መንገድ መብራት እንዲለወጥልን በእርስዎ አማካይነት እናመለክታለን - ክቡር ፕሬዝደንት!
ወደ ውሃ ጉዳይ እንለፍ፡፡ ከአዲስ አበባ ነዋሪ ግማሽ ያህሉ የውሃ ፍጆታውን የሚያገኘው በእኛው ቀበሌ ከሚመረተው ከለገዳዲ የውሃ ግድብ እንደሆነ መገመት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ውሃን በተመለከተ እስከ ሰማንያ በመቶ ለሚሆነው የለገዳዲ ለገጣፎ ነዋሪ ከሞላ ጎደል የውሃ ቆጣሪ ገብቶልናል፡፡ ፈጣሪም መንግስትም ይመስገን! ውሃ የምናገኘው ግን በአስራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ ነው፡፡
 በእኛው በራሳችን መንደር መንጭቶ በበራችን እየተንፎለፎለ በሚወርደው ውሃ፣ ከእኛ ማዶ ያሉ ወገኖች እንደልባቸው እየተጠቀሙ፣ እኛ እንደ መብራት ሁሉ የበይ ተመልካች መሆናችን ሀዘናችንን መሪር ያደርገዋል፡፡
ከጀሪካን የዘለለ የውሃ መያዣ ለሌለን ምስኪኖች የውሃ ቆጣሪ አስገብቶ፣ ውሃን በአስራ አምስት ቀን አንድ ቀን መስጠት፣ ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሳት አይሆንም ክቡር ፕሬዝደንት? እዚያው ውሃው ዳር ስለሆናችሁ፣ እንስራችሁን ይዛችሁ መቅዳት ትችላላችሁ በሚል ስሌት ይሆን ይህ ግፍ በእኛ ላይ የተጫነው? የውሃ ልማት መስሪያ ቤት፤ የውሃ መስመሩን ከዘረጋ በኋላ የውሃ እጥረት አጋጥሞት ከሆነ፣ እንደ እኛ ላለ የውሃ መያዣ ሮቶ መግዛት ለማይችል ህብረተሰብ ጥቂት የቦኖ ውሃ ማሰራጫዎችን በየአካባቢው ቢያቆምልን ምን አለበት? ክረምቱንስ ከቆርቆሮ ጣሪያ የሚገኘውን ውሃ ጭምር እያጠራቀምን ችግሩን አለፍነው፡፡ የበጋው ነገር ገና ከወዲሁ እያሳሰበን ስለሆነ ለመንግስታችን አቤት እንላለን፡፡
በመጨረሻ የማነሳው የትራንስፖርት ጉዳይ ነው፡፡ ክቡር ፕሬዝደንት! በሕገ-መንግስታችን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት፤ እንደ ለገጣፎ ያሉ በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ ከተሞች ከአዲስ አበባ የሚያገኙት የአገልግሎት ድጋፍ እንደሚኖርና በህግ እንደሚደነገግ ተቀምጧል፡፡
 በዚሁ መሰረት፣ እዚሁ አጠገባችን አያት አደባባይ የደረሰው የአዲስ አበባ ከተማ ባቡር ወደ ለገጣፎ እንዲሻገርና እኛም ተጠቃሚ እንድንሆን መጠየቅ ቅንጦት ስለሚሆን፣ ለጊዜው እሱ ይቅርና ከአዲስ አበባ የሚነሱ የከተማ አውቶቡሶች ቁጥር ይጨምርልን፡፡
በተለምዶ “ሐይገር” የሚባሉት መካከለኛ አውቶቡሶች ይመደቡልን፡፡ የታክሲዎች አገልግሎት ተጠናክሮ ይቀጥልልን የሚለውም መልእክት ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ይነገርልን፡፡  
በአጠቃላይ፤ የእኛ ነገር ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸር፣ “እናቱ የሞተችበት እና ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳል” እንዲሉ ነው ክቡር ፕሬዝደንት! እናም ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባቀረቡት ንግግርዎ ላይ “የመብራት መቆራረጥን በተመለከተ መላውን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን፤ በተለይ የለገዳዲ-ለገጣፎ ነዋሪዎችን…” የሚል ማሻሻያ ሞሽን እንዳላቀርብ (በነገራችን ላይ ሕዝብም ሞሽን የማቅረብ መብት እንዳለው የምክር ቤቱ ደንብ እድል ይሰጣል) አሁን ጊዜው አለፈ፡፡ ብቻ ችግራችን በዚህ መልኩ እንዲታይልን ለመንግስትዎ እናመለክታለን፡፡

Read 2322 times