Monday, 03 November 2014 07:52

አቶ ሃብታሙ አያሌውና ሌሎች 10 ሰዎች በሽብርተኝነት ተከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ሁሉም ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል
     ከአራት ወር ገደማ በፊት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አራት የፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በ10 ግለሰቦች ላይ የግንቦት 7 የሽብርተኛ ቡድን አባል በመሆን የተለያዩ ተልዕኮዎችን ተቀብለው መንግስትን በሃይል ለመጣልና የማህበራዊ ተቋማትን ለማውደም ተንቀሳቅሰዋል በሚል በትናንትናው እለት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው 1ኛ ተከሳሽ በዩኒቨርስቲ የማስተርስ ተማሪ የሆነው አቶ ዘላለም ወርቅ አገኘውን ጨምሮ፣ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሠማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሸዋስ አሠፋ እንዲሁም በግል ስራ የሚተዳደሩት ዮናታን ወልዴ፣ አብርሃም ሰለሞን፣ ሠለሞን ግርማ፣ ባህሩ ደጉ እና ተስፋዬ ተፈሪ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በአጠቃላይ በተከሳሾቹ ላይ 4 ክሶች የቀረቡ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ፤ በመንግስት “አሸባሪ” የተባለው ግንቦት 7 ቡድን ያቀረበለትን የአባልነት ጥሪ ተቀብሎ አባል በመሆን፣ ሰዎችን ለቡድኑ በመመልመል፣ ወደ ኤርትራ ሄደው እንዲሠለጥኑ በማድረግ፣ ለአመጽ ምቹ ቦታዎችን ለይቶ በመምረጥ መንግስትና ህገመንግስታዊ ስርአቱን እንዲሁም ማህበራዊ ተቋማትን በሽብር ለማፈራረስ ተንቀሳቅሷል የሚል ክስ ተመስርቶበታል፡፡  በሁለተኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት አራቱ የፓርቲ አባላት ህጋዊ ፓርቲን እንደሽፋን በመጠቀም የግንቦት 7 ጥሪን በመቀበል፣ አላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል፤ ከግንቦት 7 አመራር አባላት ጋርም በመገናኘት የተለያዩ የሽብር ተልዕኮዎች ተቀብለዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አቶ ዘላለምን ጨምሮ አራቱ የፓርቲ አባላት ከግንቦት 7 የሽብር ቡድን ጋር በመገናኘት ሽብር በማሴር፣ በማቀድና ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን ከአቃቤ ህግ ክስ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሌሎች በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች፣ የሽብር ቡድኑ አባል በመሆንና በሽብርተኛ ድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም መልኩ በመሳተፍ አላማውን ለማስፈፀም ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በአቃቤ ህግ የቀረበውን ክስ በንባብ ያሰማው ችሎቱ፤ ተከሳሾቹ የሚያቀርቡትን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት መዝገቡን ለጥቅም 26 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት ቀጥሯል፡፡

Read 3496 times Last modified on Monday, 03 November 2014 08:01