Monday, 03 November 2014 07:58

በከተሞች 59፣ በገጠር 33 በመቶ ሕዝብ የሚታከመው በግሉ ዘርፍ ነው ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

      የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ሕክምና ማኅበር በ7ኛ ዓመታዊ ጉባኤው፣ በገጠርም ሆነ በከተማ የጤና ሽፋኑን መቶ በመቶ ለማድረስ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
መንግሥት ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ለመላው ኅብረተሰብ ለማዳረስ የጀመረውን የጤና መድን ዋስትና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ “አቅም የሌለውን ወገን ያማከለ የጤና መድህን ስርዓትን ለመዘርጋት፣ አጠቃላይ የጤና ሽፋንን እናረጋግጣለን!!” የሚለውን የጉባኤያቸው መሪ ሐሳብ አድርገዋል፡፡
የግሉ የጤና ዘርፍ የአገሪቱን አጠቃላይ የጤና ሽፋን ለማሳደግ እየተጫወተ ያለው ሚና በግልጽ የሚታይና በመንግሥትም እውቅና ያገኘ ነው ያሉት የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ ዶ/ር ብርሃኑ ተክሌ፤ ማህበረሰቡን ያማከለ የጤና መድን ስርዓት ለመዘርጋት የግሉ የጤና ዘርፍ ከመንግሥት የጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀት ጥራቱን የጠበቀ፣ ተወዳዳሪ የሆነ፣ አቅም የሌለውን ወገን ያካተተና የሚደግፍ የጤና አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ በአጽንኦት መግለጽ እሻለሁ ብለዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የግሉን የጤና ዘርፍ የማይናቅ ሚና እንዳለው የጠቆመው አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ፤ በከተሞች 59 በመቶ፣ በገጠር ደግሞ 33 በመቶ ሕዝብ የሚታከመው በግል የጤና ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሶ፣ የግሉ የጤና ዘርፍ ከአጠቃላይ ጠየና ሽፋን 34 በመቶ ድርሻ አለው ብሏል፡፡
የመንግሥት የመጨረሻ ግብ ለ500 ቤተሰቦች አንድ ሐኪም እንዲደርሳቸው ማድረግ ነው ያሉት ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢው፣ ይህን ዕቅድ፣ ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት ባለፉት 5 ዓመታት ለጤና ተቋማት ግንባታ 43 ቢሊዮን ብር አውጥቷል፡፡ በሚቀጥለው 20 ዓመትም 1,200 ሆስፒታሎችና 12,000 ጤና ጣቢያዎች ለመክፈት ማቀዱ፣ ለግሉ የጤና ዘርፍ አመቺ ሁኔታ እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
11,060 የጤና ተቋማት፣ 65,200 ክሊኒኮችና መድኃኒት ቤቶች፣ 343 መድኃኒት አስመጪዎችና አከፋፋዮች፣ 15 የመድኃኒት ፋብሪካዎች በግል የጤና ዘርፍ ባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው ያሉት አቅራቢው፤ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ 34,000 የሕክምና ባለሙያዎችና 159 ሐኪሞች ተቀጥረው እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

Read 2211 times