Monday, 03 November 2014 08:02

ለህክምና ሄዶ በሽታ መሸመት!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

        ጤናዎ ተጓድሎ ህመም ሲሰማዎና ስቃይ ሲበዛብዎ፣ ለስቃይዎ እፎይታን፣ ለህመምዎ ፈውስን ፍለጋ የሆስፒታሎችንና የክሊኒኮችን በራፍ ማንኳኳትዎ አይቀሬ ነው፡፡
እነዚህ የበሽታ ፈውስን ሽተው የሚሄዱባቸውና ከሥቃይም እንደሚገላግልዎት ተስፋ ያደረጉባቸው ቦታዎች ከከፍተኛ የአካል ጉዳት እስከ ሞት ሊያደርሱ የሚችሉ ሆስፒታል ወለድ በሽታዎችን የሚሸምቱባቸው ስፍራዎች ጭምር እንደሆኑ ቢነገርዎ ምን ይሰማዎታል? ለመታከም ገብተው ተጨማሪ ህመም ይዘው የሚወጡባቸው የጤና ተቋማት ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችም ይህንኑ እውነታ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ችግሩ በአገራችን ብቻ የሚከሰት ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለበርካታ ሰዎች ህመምና ሞት መንስኤ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ ህመሞች ተይዘው ህክምና ለማግኘት ከገቡበት ሆስፒታል ሸምተዋቸው በሚመጡት የሆስፒታል ኢንፌክሽኖች (Nosocomial Infection) ሳቢያ ከባድ የአካል ጉዳትና ሞት የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በተለያዩ ህመሞች ተይዘው ለመታከም ሆስፒታል ከገቡ ህሙማን መካከል አብዛኛዎቹ ሆስፒታል ውስጥ በያዛቸው ኢንፌክሽን ሳቢያ ታመዋል፡፡ ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ አደረግሁት ያለውን ጥናት ጠቅሶ እንደገለፀውም፤ ወደ ጤና ተቋማት ለህክምና ከሚሄዱ ህሙማን መካከል ከ10 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሄዱበት ተቋም በሽታ ሸምተው ይመለሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በስፋት የተሰሩ ጥናቶች ባይኖሩም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል (ክሮኒቫል፣ ጌዴቦ እና ሀብቴ ገብሬ) በተባሉ ምሁራን በ1997 ዓ.ም የተደረገና “Hospital Acquired Infections Among Surgical Patients in Tikur Anbessa Hospital” በሚል ርእስ የተሰራ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ጥናቱ ከተደረገባቸው 1006 ህሙማን መካከል 165 የሚሆኑት በሆስፒታል ወለድ በሽታዎች ተይዘው ተገኝተዋል፡፡ በዚሁ ሆስፒታል የተደረገ “The Bacteriology of Nosocomial Infections at Tikur Anbessa Teaching Hospital” የተሰኘና በ2006 ህሙማን ላይ የተደረገ ሌላ ጥናት በበኩሉ፤ ከህሙማኑ 13 በመቶ የሚሆኑት በሆስፒታል ወለድ ኢንፌክሽኖች ተጠቅተዋል፡፡ ከእነዚህ ተጠቂዎች መካከልም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በሆስፒታሉ የማዋለጃ ክፍል ውስጥ የነበሩ ህሙማን እንደሆኑ ጥናቶቹ ይጠቁማሉ፡፡
ይህ አሀዝ በሆስፒታሎቹ በየጊዜው እያደገ ከሚመጣው የተገልጋይ ቁጥርና የበሽታ ዓይነቶች ብዛት ጋር ተያይዞ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልም ጥናቶቹ ይገልፃሉ፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ የጤና ተቋማት የሚገለገሉ ህሙማን በተመሳሳይ ሁኔታ በሆስፒታል ወለድ በሽታዎች ሊጠቁ እንደሚችሉ የሚጠቁመው ጥናቱ፤ ለችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መሄድ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው ብሎ ከዘረዘሯቸው ጉዳዮች መካከል ሆስፒታሉ የሚያስተናግዳቸው ተገልጋዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ፣ ባለሙያዎቹ የኢንፌክሽን ቁጥጥር መመሪያዎችንና ሆስፒታል ወለድ በሽታዎች መከላከያ መንገዶችን በአግባቡና በጥብቅ አለመከታተላቸው፣ ለኢንፌክሽኖች መከላከያ የሚሰጡ ፀረ ጀርም መድኀኒቶች ከተዋህስያኑ ጋር መላመዳቸውና የሰዎች በሽታን የመከላከል አቅም በተለያዩ ምክንያቶች እየተዳከመ መምጣት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ሆስፒታሎች (የጤና ተቋማት) በተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች የተያዙ በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ የሚገኙባቸው ስፍራዎች በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚሹ የገለፁት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ቴዎድሮስ ታዬ፤ ከልዩ ልዩ ጎጂና በሽታ አስተላላፊ ተዋህስያን ጋር ወደ ጤና ተቋማት ለህክምና የሚመጡ ህሙማን አስፈላጊውና ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች ማስተላለፋቸውና ለሌሎች ጠንቅ መሆናቸው አይቀርም ብለዋል፡፡
ሆስፒታል ወለድ በሽታዎችን በሁለት ዋና ዋና ዓይነቶች ከፍለን ልናያቸው እንችላለን ያሉት ዶክተሩ፤ የመጀመሪያው ታማሚው ሰው በቀጥታ በሽታውን ወደ ጤናማዎቹ ሰዎች እንዲተላለፍ የሚያደርግበት መንገድ ሲሆን ይህም እንደ ቲቢ ያሉና በአየር ተላላፊ የሆኑ እንዳሁም፣ በንክኪና መሰል ሁኔታዎች ከታማሚው ሰው ወደ ጤነኛው በቀላሉ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች ናቸው፡፡ ይህም ህሙማኑ በተጨናነቀ ሁኔታ በሚጋሯቸው የመኝታና የመፀዳጃ ክፍሎች፣ ንፅህናቸውን ባልጠበቁ አልጋዎች፣ ብርድልብሶችና አንሶላዎች እንዲሁም አልባሌ ስፍራ በሚጣሉ አገልግሎት ላይ የዋሉ መጠቀሚያዎች ሳቢያ በሽታው በቀላሉ ወደ ጤነኛው ሰው ሊተላለፍ ይችላል፡፡ የጤና ባለሙያዎች በሽታን ወደ ጤናማው ሰው የሚያስተላልፉበት መንገድም ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ የጤና ባለሙያው አንድ ህመምተኛን ለማከም የተጠቀመበትን ጓንት ሳይቀይር ሌላ ታማሚን ለማየት (ለመመርመር) ሲነሳ የተለያዩ በሽታ አምጪ ቫይረሶችን ከአንዱ ወደ ሌላው ማስተላለፉ አይቀሬ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ሌላውና በበርካታ የጤና ተቋማት ውስጥ እንደ ትልቅ ችግር ሆነው የሚታዩት ሆስፒታል ወለድ በሽታዎች በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች ናቸው፡፡ በአገራችን በአብዛኛው የሚታዩት የኢንፌክሽን አይነቶች አራት ሲሆኑ እነሱም - surgical wound infections urinary tract infections እና Dosokimital Nimonia የተባሉት ሲሆኑ ሴቶች በወሊድ ወቅት የሚገጥማቸው ኢንፌክሽንም ተጠቃሽ ነው፡፡ እነዚህን ዘርዘር አድርገን ለማየት እንሞክር፡-
surgical wound infections
በቀዶ ጥገና ወቅት ከውጪ በሚገቡ የተለያዩ ጀርሞችና ባክቴሪያዎች አማካኝነት ቀዶ ጥገናው የተካሄደበት የሰውነት ክፍልን በንፅህና ካለመያዝና ንፅህናው በአስተማማኝ ሁኔታ ባልተጠበቀበት ሁኔታ ቀዶ ጥገናውን በማድረግ ሂደት የሚከሰት ኢንፌክሽን ሲሆን ይህም በርካታ ታማሚዎችን የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው፡፡
Urinary Tract Infections
(በሽንት መተላለፊያ ቱቦ ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች)
 ይህ አይነቱ ኢንፌክሽን፤ ህሙማን ቀዶ ጥገና ለማድረግ በሚዘጋጁበት ጊዜ ወይንም በሌሎች ህመሞች ሳቢያ ሰው ሰራሽ የሽንት ማውጫ ቱቦ እንዲገባላቸው በሚደረግ ወቅት የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግርም ሆስፒታል ውስጥ ለህክምና ከሚገቡ ህሙማን መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የሚያጋጥም ችግር ሲሆን ችግሩ የሽንት ማውጫ ቱቦው (ካቴተሩ) ወደሰውነታቸው እንዲገባ በሚደረግበት ወቅት የሚፈጠር መሆኑን ዶ/ር ቴዎድሮስ ገልፀዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ህሙማኑ ወደ ሆስፒታል ገብተው ለቀዶ ህክምና ዝግጁ እንዲሆኑ ሲደረግ የሚገጠምላቸው ሰው ሰራሽ የሽንት ማውጫ ቱቦ ብቁ ባልሆኑ ሙያተኞች እንዲሰራ ይደርጋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በሆስፒታሎች ለስራ ልምምድ የሚገቡ ተማሪዎች ይህንን ዓይነቱን ስራ እንዲሰሩ ስለሚተውላቸው ታማሚው በሽንት መተላለፊያ ቱቦ ኢንፌክሽን በቀላሉ ሊጠቃ ይችላል፡፡
3. Dosokimial Nlimonia
ይሄ የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን የምንለው ሲሆን በዚህ ዓይነቱ ኢንፌክሽን የሚጠቁ ሰዎች ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ የሚገጠምላቸው በሽተኞች ሲሆኑ መሳሪያውን በመግጠም ሂደት ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት እንደሚከሰት ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡
4ኛ. በሴቶች ላይ ከወሊድ በኋላ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች (በቀዶ ጥገና በሚደረግ ወሊድና በስቲች)ይህ አይነቱ ኢንፌክሽን በአገራችን በስፋት የሚታይና በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሴቶች ለከባድ ህመምና ለሞት የሚዳርግ ችግር ነው፡፡
 በሆስፒታል ውስጥ ለሚከሰቱ ሆስፒታል ወለድ በሽታዎች በአብዛኛው ተጋላጭ የሚሆኑት ህፃናትና በዕድሜ የገፉ ሰዎች እንደሆኑ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ የጤና ተቋማቱ ተላላፊ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ለይተው የሚያክሙባቸው ቦታዎች አለመኖራቸው፣ በሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ የመፀዳጃና የጋራ መጠቀሚያ ስፍራዎች ንፅህና፣ በሆስፒታሎች ውስጥ ውሃ በበቂ ሁኔታ አለመገኘት፣ በየመኝታ ክፍሎችና ህክምና መስጫ ቦታዎች ላይ አየር በበቂ ሁኔታ የሚዘዋወርበት ሁኔታ አለመኖር ለችግሩ መባባስ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ሆስፒታል ወለድ በሽታዎችና ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የገለፁት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም ታማሚውን ለማዳን የሚደረገው ጥረት እምብዛም አርኪ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ሆስፒታል ወለድ ኢንፌክሽኖችን በቀላሉ ለማስወገድ ይረዱ የነበሩ መድሃኒቶች ከበሽታው ጋር በመላመዳቸው ሳቢያ በሽታው ለመድሃኒቶቹ መሸነፉን አቁሞአል፡፡ በዚህ ምክንያትም ቀላል በሽታ ለመታከም መጥተው በሆስፒታል ወለድ ኢንፌክሽኖች በመጠቃት ህይወታቸውን የሚያጡ ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዷል ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በእስራኤል አገር የኩላሊት ንቀላ ተከላ ህክምና የተደረገለት ታዋቂው የዜማና ግጥም ደራሲ አበበ መለሰ የዚህ ችግር ተጠቂ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አበበ በሆስፒታል ውስጥ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ከተደረገለት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ቤተሰቦቹ ደስታቸውን ለመግለፅ ሲሞክሩ በተፈጠረ ንክኪ ጤናውን ለአደጋ ሊጥል የሚችል ሁኔታ ተከስቶ ነበር ተብሏል፡፡ ጎበዝ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዳይሆንብንና ልንታከም ሄደን ታመን እንዳንመጣ ጠንቀቅ እንበል፡፡
 

Read 3153 times