Saturday, 08 November 2014 10:39

የአንድነት አዲሱ አመራር መታገዱ ግራ መጋባት ፈጥሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    የአመራር አባላት ድብደባና እስር እየደረሰባቸው ነው አለ

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የአንድነት ፓርቲ አዲሱን ስራ አስፈፃሚ አላውቀውም በማለት ፓርቲውን ወክሎ እንዳይንቀሳቀስ ማገዱ በአመራሩ ዘንድ ግራ የመጋባት ስሜት ፈጥሯል፡፡  ፓርቲው ቦርዱን ማብራሪያ እንደሚጠይቅ ገልጿል፡፡
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ተጠባባቂ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም ስለ ሁኔታው ለአዲስ አድማስ ሲያብራሩ፤ “ኢ/ር ግዛቸው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ አዲሱ ስራ አስፈጻሚ የተመረጠው በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ነው” ብለዋል፡፡
በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ጠቅላላ ጉባኤው በማይኖርበት ወቅት ፕሬዚዳንት የመምረጥን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ብሄራዊ ምክር ቤቱ ውክልና ተሰጥቶታል ይላሉ፤ ኃላፊው፡፡ መተዳደሪያ ደንቡን ለምርጫ ቦርድ ካስገባን ከወር በላይ ሆኖታል ያሉት አቶ አስራት፤ በቦርዱ ደንብ መሰረት፣ አንድ ፓርቲ ያሻሻለውን መተዳደሪያ ደንብ ለቦርዱ ባስገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠው ደንቡን እንደተቀበለው ይቆጠራል፤ በዚህ መሰረት መስተናገድ አለብን፤ ይሄንንም ለቦርዱ እናሳውቃለን ብለዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት አዲሱን የአንድነት አመራር ባገደበት ደብዳቤው፤ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተሻሽሏል ተብሎ ለቦርዱ የቀረበው ደንብ የተለያዩ ጉድለቶች ስላሉበት እውቅና እንዳልሰጠው ጠቅሶ ደንቡ እውቅና ሳያገኝ ፕሬዚዳንቱን ከኃላፊነት ማንሳት ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡ አዲሱ አመራር ቦርዱ የመጨረሻውን ውሣኔ እስኪሰጥ ድረስም ፓርቲውን ወክሎ መንቀሳቀስ እንደማይችል የቦርዱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲው በትናንትናው እለት በፅ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በፓርቲው የአመራር አባላት ላይ ድብደባና እንግልት እንዲሁም እስር እየተፈፀመባቸው መሆኑን አስታውቆ፤ ድርጊቱ ገዥው ፓርቲ አንድነትን ለማዳከም ከከፈታቸው ዘመቻዎች አንዱ ነው ብሏል፡፡ ኢህአዴግ አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲያስብም ፓርቲው ጠይቋል፡፡  

Read 1703 times