Saturday, 08 November 2014 10:42

የደ/አፍሪካው ኩባንያ የሃበሻ ሲሚንቶ ድርሻውን ወደ 51 በመቶ አሳደገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

          ፖርትላንድ ፕሪቶሪያ ሲሜንት (ፒፒሲ) የተሰኘው ተቀማጭነቱ በደቡብ አፍሪካ የሆነ የሲሚንቶ አምራች ኩባንያ፣ በሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ውስጥ የነበረውን 27 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ወደ 51 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቤኪ ሲባያ ባለፈው ረቡዕ ለዴስቲኒ ኮኔክት ድረ ገጽ እንደተናገሩት፣ ከሁለት አመታት በፊት ከሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር 27 በመቶ የአክስዮን ድርሻ የገዛው ፒፒሲ፤ ድርሻውን ወደ 51 በመቶ ማሳደጉ፣ በአፍሪካ አህጉር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማጐልበት የቀየሰውን ስትራቴጂ የበለጠ ለማፋጠን አቅም ይፈጥርለታል፡፡
በ135 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከአዲስ አበባ በ35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ግንባታው በመከናወን ላይ የሚገኘው የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ከሁለት አመታት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ የማምረት ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅና በአመት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ሲባያ ተናግረዋል፡፡
ቀሪው 49 በመቶ የሃበሻ ሲሚንቶ የአክሲዮን ድርሻ ከ16 ሺ በላይ በሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት እንደሚቀጥልም ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል፡፡

Read 1932 times