Print this page
Saturday, 08 November 2014 10:54

“የፓርቲዎች ትብብር” የህዳር ወር የተግባር እንቅስቃሴ ይፋ ሆነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)
  • የ24 ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ውይይት ለማካሄድ ታቅዷል
  • እውነተኛ ምርጫ ካለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሸንፋሉ ብለዋል


          ከሁለት ሳምንት በፊት በዘጠኝ ብሔር ተኮርና ህብረ - ብሄር ፓርቲዎች የተመሰረተው የፓርቲዎች ትብብር፤ የህዳር ወር የተግባር እንቅስቃሴውን ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡ ስድስት ዋና ዋና እንቅስቃሴዎችን ለመከወን እቅድ ያወጣው የፓርቲዎቹ ትብብር፤ የ24 ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍና በአዲስ አበባ ሶስት አማካይ ዞኖች የሚካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡
የህዳር ወርና ቀጣይ የተግባር እንቅስቃሴዎች በዋናነት ትኩረት የሚያደርጉት በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ እንደሆነም የትብብሩ አመራሮች ገልፀዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ2007 ምርጫ ያዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳ ለማወያየት በሚል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስብሰባ መጥራቱን ያስታወሱት አመራሮቹ፤ ከዚህ ስብሰባ አስቀድሞ የዚህ ትብብር አባል ፓርቲዎችን ጨምሮ 12 ፓርቲዎች ጥቅምት 5 ቀን 2005 ለቦርዱ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች አለመመለሳቸውን፣ ገዢው ፓርቲና አጋሮቹን ጨምሮ ሁሉም ህጋዊ ፓርቲዎች ተገናኝተው በምርጫና በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚወያዩበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ጠቁመው ሁኔታው የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል ሳይሆን ተዘግቷል ወደሚል ድምዳሜ የሚያደርስ ነው ብለዋል፡፡
 “የፖለቲካ ምህዳሩ የቱንም ያህል ቢዘጋም ግን ህዝቡ ተገቢ መብቶቹን እስኪቀዳጅ ድረስ የትግሉን አስፈላጊነት አምነንበት በጥንካሬ እንጓዛለን” ብለዋል - አመራሮቹ በሰጡት መግለጫ፡፡ በምርጫው መሳተፍ አለመሳተፋቸውን እስኪወስኑ ድረስ በቀሪዎቹ ወራት የምርጫው ሂደት ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት የተግባር እንቅስቃሴውን እንደሚቀጥል ያስታወቀው ትብብሩ፤ የህዳር ወር የተግባር እንቅስቃሴው ህዝቡ በየቤተ - እምነቱ የፀሎት ፕሮግራም እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፍ፣ በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይት ማድረግ፣ የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ ለመንግስታዊ ተቋማት (ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና መሰል መ/ቤቶች) ደብዳቤ ማስገባት፣ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማትና የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታት እንዲሁም ድጋፍ ማሰባሰብ የሚሉትን እንደሚያካትት ገልጿል፡፡
“አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታና ቀደም ካሉት የምርጫ ሂደቶች ተሞክሮ በመነሳት ገዢው ፓርቲ በጉዳይ ፈፃሚው በምርጫ ቦርድ በኩል የሚሰራውን ቧልት እናውቃለን” ያሉት የትብብሩ ሰብሳቢ ኢ/ር ይልቃል፤ ይህንን ቧልት ራቁቱን በማስቀረት ለነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒና አሳታፊ ምርጫ ሜዳው እንዲስተካከል፣ በሰላማዊ ትግል አዎንታዊ ተፅዕኖ ለማሳረፍና ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል፤ ትብብሩ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
እውነት የዚህች አገር የፖለቲካ ችግር በፀሎት ይፈታል ወይ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ ሰብሳቢው ኢ/ር ይልቃል ሲመልሱ፤ “እንደኛ ደረቅ ፖለቲከኞች ቢሆን ይህች አገር ጠፍታ ነበር፤ እስካሁንም በእምነታቸው በፀኑ አባቶችና እናቶች ፀሎት ነው የኖረችው፤ ፀሎት መፍትሔ እንደሚያመጣ እናምናለን፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የእነ አቡነ ጴጥሮስ አገር ናት” ብለዋል፡፡
 የ24 ሰዓቱ ሰላማዊ ሰልፍ መቼና የት ይካሄዳል ለሚለውም ሰልፉ ህዳር 27 እና 28 እንደሚካሄድ፤ ነገር ግን ጃንሜዳ ይሁን መስቀል አደባባይ ገና እንዳልተወሰነ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ ከእንቅስቃሴው የሚጠበቀው ውጤት ምን እንደሆነ የተጠየቁት አመራሮቹ፤ ተስፋ ያለው አማራጭ የፖለቲካ ሃይል ሆኖ በመቅረብ ትግሉን ማካሄድ እንደሆነና ህዝቡ የኢህአዴግን አምባገነንነት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ አማራጭ የፖለቲካ ሃይል ካገኘ ቀስቃሽ ሳያስፈልገው ስልጣኑን የራሱ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ “በምርጫ ትሳተፋላችሁ አትሳተፉም? እስከ ዛሬ ካደረጋችሁት ሰላማዊ ሰልፍስ ምን አተረፋችሁ?” በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበው ጥያቄም፤ “እውነተኛ ምርጫ ካለ 99.6 በመቶ የሚያሸንፉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው” ያሉት ሰብሳቢው፤ “ነፃ፣ ፍትሃዊና ግልጽ የምርጫ ሂደት በሌለበት በምርጫ መሳተፍ ማለት የዚህችን አገር ችግር ማባባስ፣ ለኢ-ዴሞክራሲያዊነትና ለስርዓት አልበኝነት መተባበር እንዲሁም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መሳለቅ በመሆኑ አንሳተፍም“ ብለዋል፡፡
 ሆኖም አሁን ሙሉ በሙሉ አንሳተፍም ብለን አልደመደመንም፤ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ምርጫ ቦርድም ገለልተኛ የሚሆኑበትን አማራጮች ለመፍጠር እንጥራለን ሲሉ ሰብሳቢው ገልፀዋል፡
“በንጉሱ፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ጊዜ ምርጫዎች ተካሂደዋል፤ ሆኖም ይህቺን አገር ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት አላሸጋገራትም” ያሉት የትብብሩ ም/ሰብሳቢ፤ ለዚህ ምክንያቱ በአንዱም ዘመን እውነተኛ ምርጫ ባለመካሄዱ ነው ብለዋል፡፡
ሌሎች ፓርቲዎችም ወደ ትብብሩ ተቀላቅለው ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ጥሪ ያስተላለፉት አመራሮቹ፤ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

Read 3458 times