Saturday, 08 November 2014 10:57

አክሰስ ከእዳው ሃብቱ እንደሚበልጥ ተገለፀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(9 votes)
  • የማህበሩንና የቤት ገዢዎችን ችግር ለመፍታት ኮሚቴ ተቋቁሟል


             አክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ካለበት እዳ ይልቅ ሃብቱ እንደሚበልጥ ተገለፀ፡፡ የማህበሩንና የቤት ገዢዎችን ችግር ለመፍታት ከትልልቅ ሚኒስቴር መ/ቤቶችና ከባለ ድርሻ አካላት የተወጣጡ የአብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡ ከትላንት በስቲያ በንግድ ሚኒስቴር በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የተዋቀሩት ኮሚቴዎች የአክሰስ ሪል ስቴትንና የቤት ገዢዎቹን ችግር ከመፍታት ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ያለውን የሪል እስቴት ችግር ለመቅረፍ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በንግድ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን መሃመድ አስታውቀዋል፡፡
የኮሚቴው የአጭር ጊዜ እቅድ በአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማህበርና በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ቤት ገዢዎችን ችግር በአንድ አመት ውስጥ እልባት መስጠት ሲሆን በረጅም ጊዜ እቅዱ በአገር አቀፍ ደረጃ በሪል እስቴት ዘርፍ፣ በመሬት አዋጅ ዙሪያ፣ በአክሲዮን ማህበራት ምስረታና አካሄድ ላይ ያሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያኙበትን እርምጃዎች አጥንቶ ለመንግሥት ፖሊሲ ውሳኔ ለማቅረብ ይንቀሳቀሳል ተብሏል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴት የቤት ገዢዎችን ችግር የሁሉንም መብት ባስከበረ መልኩ ለመፍታት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የሚመራ አብይ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን ኮሚቴውን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ በሰብሳቢነት፣ የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ደግሞ በምክትል ሰብሳቢነት ይመሩታል ተብሏል፡፡ ለስራው አመቺነት የአክሰስ ሪል እስቴት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የቤት ገዢዎች ተወካይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤት እና የፍትህ ሚኒስቴር የኮሚቴው አባላት በመሆን እየሰሩ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
አብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎቹ የተቋቋሙት በአሁኑ ሰዓት በአክሰስ ሪል እስቴትና በቤት ገዢዎች መካከል የተነሳው ቀውስ በተናጠልና በፍ/ቤት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን ሁለገብ የመንግሥት ድጋፍ ስለሚያስፈልገው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ችግሩ እልባት እስከሚያገኝም ሶስተኛ ወገኖች በትእግስት እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
አክሰስ ሪል እስቴት ያሉትን የገንዘብና የአይነት ሃብቶች፣ በአክሰስ ሪል ስቴት ስም ያሉትን፣ በስሙ ያልተመዘገቡትንና ወደ አክሰስ ሪል እስቴት መግባት ያለባቸውን መሬቶች፣ የተገነቡና የተሸጡ ህንፃዎችን እንዲሁም የደረቅ ቼኮችን ሁኔታ የቴክኒክ ኮሚቴው እየመረመረና ወደ መፍትሄ እየመጣ መሆኑን አቶ ኑረዲን ገልፀው፤ አክሰስ ሪል እስቴት ራሱ ውል ሰጪና ተቀባይ ሆኖ የተፈራረመባቸው ሰነዶች፣ ደረቅ ቼኮችና ተያያዥ የተጭበረበሩ ጉዳዮች በመገኘታቸው በዶክመንትነት ተይዘው እየተመረመሩ እንደሆነና ጅቡቲ ወደብ ላይ የደረሱ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና ብረታ ብረቶች እንዳሉ እንደተደረሰበትም ተገልጿል፡፡
በቀጣይ ደረቅ ቼኩ ምን ይደረግ? ገንዘባቸውን የሚፈልጉ ቤት ገዢዎች የትኛው የማህበሩ ንብረት ተሸጦ ይመለስላቸው? የማህበሩን ህልውና ለማስቀጠልና የቤት ገዢዎችን ጥያቄ በአመርቂ ሁኔታ ለመመለስ ምን ምን ስራዎች ይሰሩ? የሚለው ላይ የቴክኒክ ኮሚቴው በትጋት እየሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በመሬት አዋጁ፣ በሊዝ አዋጁና በአክሲዮን ምስረታ አካሄድ ላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በእነዚህ ዘርፎች የሚታዩ የተዝረከረኩ አሰራሮች እንዲስተካከሉ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴት መስራችን በተመለከተም ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ከአብይ ኮሚቴው ጋር በመነጋገር በዲፕሎማሲያዊ ጥረትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እየተሰራ ሲሆን አክሰስ ሪል እስቴት ህልውናውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የገንዘብና ሌሎች አቅሞች እንዳሉት የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን ወክለው በመግለጫው ላይ የተገኙት የቴክኒክ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ገ/ጊዮርጊስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

Read 5312 times