Saturday, 08 November 2014 11:21

አገሩን በማስጐብኘት የከበረው የቀድሞ ኮንትሮባንዲስት

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(1 Vote)

“በዙሪያ ከከበቡኝ ሰዎች 99 በመቶው አይሳካልህም ይሉኝ ነበር”

          ዛሬም እንደ ባለፈው ሳምንት ከCNN ያገኘሁትን የስኬት ታሪክ አካፍላችኋለሁ፡፡ የዛሬውን ባለ ታሪክ ለየት የሚያደርገው የሚያውቁት ሁሉ እንደማይሳካለት እየነገሩ ቢያጣጥሉትም በትጋትና በቁርጠኝነት እምነታቸው የተሳሳተ እንደነበር ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡ ይሄም ታሪክ መቼቱ በዚህችው በአህጉራችን በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ታሪኩ ለስኬት እንደሚያነቃቃችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አሞስ ዌኬሳ፤ በአገሩ በኡጋንዳ ብዙ ለውጦችን አይቷል፡፡ ዛሬ በጥረቱ ራሱን ሚሊዬነር ማድረግ የቻለው ዌኬሳ፤ በዩጋንዳ እጅግ ግዙፍና ታዋቂ ከሚባሉት የአስጐብኚ ድርጅቶች (tour operators) አንዱ የሆነውን “ግሬት ሌክ ሳፋሪስ” በባለቤትነትና በሥራ አስኪያጅነት ይመራል፡፡
ይሄ ኡጋንዳዊ የከበረው አዲስ ነገር በመፍጠር ወይም በምርት ሥራ ላይ ተሰማርቶ አይደለም፤ የአገሩን የተፈጥሮ ሃብት በማስጐብኘት ነው፡፡ ደንበኞቹን በንግስት ኤልዛቤት ፓርክ ውስጥ በዝሆን ጀርባ በማንሸራሸር ወይም ሙርቺሰን ፏፏቴ ጋ የሚገኙትን የአካባቢውን ዝንጀሮዎች ቀረብ ብለው የማየት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግና የአገሩን አስደማሚ ውበት በማስተዋወቅ ሚሊዮን ዶላሮችን እንዳካበተ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“በግሌ መላውን ዓለም ተጉዣለሁ፤ በዚህ ሥራ ተጠቀምኩ ከምላቸው ነገሮች መካከል በአስጐብኚነት የራሴን አገር ተዟዙሬ ማየቴና ቱሪስቶች በአካባቢው ውበት ምን ያህል እንደሚደመሙ ለመታዘብ መቻሌ ነው” ይላል ዌኬሳ፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ቢመጣም ሁሌም ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ ባለፈው ዓመት 1.2 ሚሊዮን ቱሪስቶች (ካለፉት 5 ዓመታት የ50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል) ተስተናግደዋል፡፡ ደም የማፍሰስ ጥማት የነበረበት የኢዲ አሚን አገዛዝ መገርሰሱን ተከትሎ ግን ለበርካታ አስርት ዓመታት የአገሪቱ ቱሪዝም አንዳችም እንቅስቃሴ አልነበረውም፡፡
ዌኬሳ ከመወለዱ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር አምባገነኑ ኢዲ አሚን፤ አገሪቱን በሃይል በቁጥጥሩ ስር ያደረጋት፡፡ ራሱን የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት አድርጐ የሾመው አሚን፤ የብሪቲሽ ኢምፓየር ድል አድራጊና የስኮትላንድ የመጨረሻ ንጉስ እንደሚሆን አውጆ ነበር፡፡ (The Last King of Scotland የሚል ፊልም መሰራቱን ልብ ይሏል) “ቢግ ዳዲ” ተብሎ መጠራትንም ይወድ ነበር፡፡ የአገሬው ሰው ግን የሽብር አገዛዙን የሚመጥን  የተለየ ቅጽል ስም አወጣለት - “የኡጋንዳው ጨፍጫፊ” በማለት፡፡
“እኔ በተወለድኩበት ወቅት ለእያንዳንዱ ኡጋንዳዊ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ሰዎች በህይወት ለመቆየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡” ሲል ፈታኙን የልጅነት ዘመኑን አስታውሷል፡፡
“ቤተሰቤ ለድንበር አካባቢ ቅርብ ነበር፤ ማድረግ የሚችሉት ብቸኛ ነገር ከኬንያ ሸቀጦችን በኮንትሮባንድ ማስገባት ነበር፡፡ እኔም በ7 ዓመት የልጅነት ዕድሜዬ በህገወጥ መንገድ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የተሳተፍኩ ይመስለኛል” ብሏል - ዌኬሳ፡፡
የ50 ሳንቲም ደሞዝ
ከአንዱ ወደ ሌላው እያለ ብዙ ሥራዎችን ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በወር 10 ዶላር (200 ብር ገደማ) እየተከፈለው ወለል ያፀዳ ነበር፡፡ “ሃቁን ለመናገር የአንድ ሳምንት በጀቴ ግማሽ ዶላር (50 ሳንቲም) ነበር” ይላል፡፡  ቱሪስቶችን የማስጐብኘት ሥራ ማግኘቱ ግን የማታ የማታ የህይወት አቅጣጫውን ቀየረለት፡፡ እሱም ቢሆን ግን አድካሚ እንደነበር አልደበቀም፡፡
“የመጀመሪያ ጉዞዬን በደንብ አስታውሳለሁ፡፡ ሦስት ቱሪስቶች ይዘን ለ15 ቀን ገደማ ነበር የሄድነው፡፡ ሜዳ ላይ ድንኳኖችን መትከል ነበረብን፤ ለቱሪስቶቹ ቁርስ እናዘጋጃለን፤  ሜዳ ላይ የሚቀጣጠለውን እሳት (ካምፕፋየር) የመጨረሻው ሰው እስኪነሳ ድረስ (እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ሊሆን ይችላል) መቆስቆስ የግድ ነው፤ በጣም አድካሚ ስራ ነበር” በማለት የመጀመሪያ የአስጐብኚነት ሥራውን ያስታውሳል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም የራሱን ድርጅት ለማቋቋም ሲወስን ማንም ያበረታታው አልነበረም፡፡ እንኳን ማበረታታት እንደ ፍጥርጥሩ እንዲሆን እድል አልተሰጠውም፡፡ የሚያውቁት ሁሉ “ከድሃ ቤተሰብ ስለተወለድክ፤ ቢዝነስ መስራት አትችልም” ይሉት እንደነበር ይናገራል፡፡ እንዲህ የሚሉት ጥቂት ሰዎች ቢሆኑ ይቋቋመው ነበር፡፡ ችግሩ ሁሉም ሰው አንድ አቋም መያዙ ነበር፡፡
“በዙሪያዬ ከከበቡኝ ሰዎች 99 በመቶው ‘የቢዝነስ መሰረት ስለሌለህ አይሳካልህም’ ይሉኝ  ነበር፡፡ እኔ ግን አሁንም ድረስ እግዚአብሔር ይሄን ዕድል የሰጠኝ ሊፈትነኝ እንደሆነ አስባለሁ፤ እናም በዚህ ሥራ ስኬታማ መሆኔን ማረጋገጥ እሻለሁ” ብሏል፡፡እንዲህ ይበል እንጂ ስኬቱን አረጋግጧል፡፡ ዛሬ ዌኬሳ ሚሊዬነር ሆኗል፡፡ ከራሱ ተርፎ በአስጐብኝነት ዕውቅና በተቀዳጀው  ኩባንያው አማካኝነት ለ180 ኡጋንዳውያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
“ኩባንያው በአገሪቱ ከሚታወቁት 3 ምርጥ የአስጐብኚ ኩባንያዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ እኔን ከሚያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ ግን በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ የመኝታ ክፍሎችን በመገንባት የመጀመሪያው ኡጋንዳዊ መሆኔ ነው፤  ብዙ ኡጋንዳውያንም ተመሳሳይ ግንባታ ለመጀመር እያኮበኮቡ ነው፡፡” ሲል ለሲኤንኤን ገልጿል፡፡
አሁን በርካታ ኡጋንዳውያን “ዌኬሳ መስራት ከቻለ፤ እኛም አያቅተንም” እያሉ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “ከድሃ ቤተሰብ ስለተወለድክ ቢዝነስ መስራት አትችልም” የተባለው ዌኬሳ፤ ዛሬ ለአያሌ ኡጋንዳውያን የብርታትና የመነቃቃት ምንጭ ለመሆን ችሏል፡፡ የስኬት ምስጢሩ በተለያዩ ሰዎች አስተያየት ሳይወናበዱ የራስን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በፅናት መትጋት  እንደሆነ ከዚህ የቢዝነስ ጀግና መማር አያዳግትም፡፡ ሠናይ ሰንበት ይሁንላችሁ!!

Read 1561 times