Saturday, 08 November 2014 11:26

የአፍሪካ ህብረት የቡርኪናፋሶ ጦር በ2 ሳምንት ውስጥ ስልጣን እንዲያስረክብ አሳሰበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ስልጣኑን ካላስረከበ አገሪቱን ከህብረቱ አባልነት አግዳለሁ ብሏል
ፓርቲዎች እስከ 1 አመት የመንግስት ሽግግር ለማድረግ ተስማምተዋል

            ቡርኪናፋሶን ለ27 አመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ በህዝብ አመፅ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ የአገሪቱ የጦር ሃይል ስልጣን የያዘበት አካሄድ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን የተከተለ አይደለም ሲል የተቃወመው የአፍሪካ ህብረት፤ ጦሩ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሲቪል መንግስት ስልጣን እንዲያስረክብ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከንቅናቄ መሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉት የአገሪቱ የጦር ሃይል መሪ ሌ/ኮሎኔል አይዛክ ዚዳ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ስልጣን እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ፤ ጦሩ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ስልጣኑን የማያስረክብ ከሆነ፣ ቡርኪናፋሶን ከህብረቱ አባልነት ከማገድ አንስቶ በጦር መኮንኖች ላይ የጉዞ ማዕቀብ እስከመጣል የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
ድንገት የተቀሰቀሰው የቡርኪናፋሶ ህዝባዊ አመጽ ብሌስ ኮምፓዎሬን ከስልጣን ማውረዱን ተከትሎ፣ አገሪቱን የማስተዳደሩን ስልጣን የተረከበው የጦር ሃይል በአፋጣኝ ስልጣኑን ለተገቢው መሪ እንዲያስረክብ ሁኔታዎችን የማመቻቸት አላማ የያዘው የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች የልኡካን ቡድን፣ ወደ አገሪቱ በማምራት በጉዳዩ ዙሪያ መምከሩን ዘገባው ገልጿል፡፡
ጦሩ ስልጣኑን በአፋጣኝ እንዲያስረክብ ለማግባባት ወደ ቡርኪናፋሶ ያመሩት የጋና፣ የናይጀሪያና የሴኔጋል መሪዎች ከትናንት በስቲያ ከጦር ሃይሉ መኮንኖች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ አካላት፣ ከጎሳ መሪዎችና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር መወያየታቸውንና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጪው አመት ህዳር ወር ላይ እስከሚካሄድ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤትም በወሩ መጨረሻ በሚጠራው ስብሰባ አገሪቱን ከቀውስ ለማዳን በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ እንደሚመክርም ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፤ ህገመንግስቱን በማሻሻል ያለ አግባብ በቀጣዩ የአገሪቱ ምርጫ ለመወዳደር መሞከራቸውን ተከትሎ፣ ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞ ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል፡፡

Read 2341 times