Saturday, 08 November 2014 11:25

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ያሰሩት ቤተ መንግስት ተቃውሞ ገጠመው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

615 ሚ. ዶላር ወጥቶበታል፤ ተጨማሪ 85 ሚ. ፓውንድ ለማስፋፊያ ተመድቦለታል
ለፕሬዚዳንቱ ልዩ አውሮፕላን 115 ሚ. ፓውንድ ተከፍሏል
3 ሚ. ቱርካውያን ስራ አጦች ናቸው

           የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሪሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን፤ በ615 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያሰሩትና አንካራ ውስጥ በሚገኝ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ስኩየር ጫማ ቦታ ላይ ያረፈው ግዙፉ ‘ነጩ ቤተ መንግስት’ በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ለ12 አመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በቅርቡ የፕሬዚዳንትነት ስልጣን የያዙት ኤርዶጋን፤ ከታዋቂዎቹ ዋይት ሃውስና ቤኪንግሃም ቤተመንግስቶች እንደሚበልጥ የተነገረለትን ይህን ቤተመንግስት ማሰራታቸው፣ በአገሪቱ ግብር ከፋይ ዜጎች ዘንድ አላግባብ ወጪ የወጣበት የቅንጦት ግንባታ በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ከሳምንታት በፊት ግንባታው ተጠናቆ ስራ የጀመረውና “አክ ሳራይ” ተብሎ የሚጠራው ቤተ መንግስት፤ በከፍተኛ ወጪ ከመገንባቱ በተጨማሪ፣ በአረንጓዴ ቦታነት በተከለለ ስፍራ ላይ መሰራቱ በአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ እንዳስነሳ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
“ፕሬዚዳንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን ጨፍጭፈው በከፍተኛ ወጪ የራሳቸውን የቅንጦት ቤት የገነቡት፣ 3 ሚሊዮን ዜጎቿ ስራ አጥ በሆኑባት አገር ላይ ነው” ብለዋል - “ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ” የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከማል ኪሊዳሮግሉ ለቴሌግራፍ ጋዜጣ በሰጡት ቃል፡፡
በአገሪቱ ቤተ መንግስት ለመገንባት ከተመደበው በጀት ከሁለት እጥፍ በላይ ገንዘብ ፈሶበታል የተባለው ቤተ መንግስቱ 1 ሺህ ክፍሎች ያሉት ሲሆን እጅግ ዘመናዊ የሆነ ጥብቅ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሲስተም ተገጥሞለታል፡፡
 ቤተመንግስቱ እጅግ ውድ በሆኑ የግንባታ ቁሳቁሶች የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
‘ነጩን ቤተ መንግስት’ በቀጣዩ አመት የበለጠ እንዲያምርና እንዲስፋፋ ለማድረግ ተጨማሪ 85 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መመደቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ለፕሬዚዳንቱ ልዩ ኤርባስ አውሮፕላን ለመግዛት 115 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መመደቡንም ገልጿል፡፡

Read 3735 times