Saturday, 08 November 2014 12:05

የአንጀት ቁስለት ህመምና መዘዙ

Written by 
Rate this item
(61 votes)
  • በሽታው በፍጥነት ህክምና ካላገኘ ለሞት ሊዳርግ ይችላል
  • የበሽታው ምልክቶች ከአሜባ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው
  • በሽታውን ለማከም ይሰጡ የነበሩት መድሃኒቶች ከባክቴሪያው ጋር ተላምደዋል


             “የምግብ ፍላጐቷ እየቀነሰ፣ ሰውነቷ እየከሳና እየደከመ ሲሄድ ሃሳብ ገባኝ፡፡ በየዕለቱ ምግብ በቀመሰች ቁጥር ሽቅብ ሲተናነቃት ስመለከት ደግሞ ልቤ ሌላ ነገር ጠረጠረ፡፡ ምልክቶቹ በአብዛኛው ከእርግዝና ምልክቶች ጋር የሚመሳሰሉ በመሆናቸው ሁኔታዋ እጅግ አስደነገጠኝ፡፡
ሁለታችንም ከወላጆቻችን ጋር አብረን የምንኖርና የመሰናዶ ተማሪዎች በመሆናችን በዚህ ሁኔታና በዚህ ዕድሜዋ ማርገዟ አሳዘነኝ፡፡ ምንድነው የማደርገው? ወላጆቻችንስ እንዴት ነው የሚነገራቸው? የሚለው ሃሳብ እንቅልፍ ነሣኝ፡፡ በሁለት ዓመት የምበልጣት ታላቋ ብሆንም እንደ እኩያዬ ነበር የማያት፤ የምትደብቀኝም ሆነ የምደብቃት ሚስጢር አልነበረም፡፡ አሁን ግን ድብቅ የሆነችብኝ መሰለኝ፡፡ ነገሩን ለማውጣጣት ያላደረግሁት ሙከራ አልነበረም፡፡ ሆኖም ምንም ፍንጭ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆዷ እንደ ከበሮ እየተነፋና እየተወጠረ ሄደ፡፡ ከእንብርቷ በታችም ከፍተኛ ስቃይ ያለው ህመም እንደሚሰማትም ነገረችን፡፡ የምግብ ፍላጐቷ ጨርሶውኑ በመጥፋቱ ሚሪንዳና ጭማቂዎችን ትንሽ ትንሽ ልንሰጣት ሞከርን፡፡ የምትወስደው ምግብ ሁሉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ይወጣል፡፡ ሠገራ መቀመጥ ስቃይ ሆነባት፡፡ ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ ወደ ዩኒቨርሳል ክሊኒክ ይዘናት ሄድን፡፡ በክሊኒኩ በተደረገላት ምርመራም የአንጀት ቁስለት በሽታ እንዳለባትና የአንጀቷ ግድግዳዎች ክፉኛ መጐዳታቸው ተነገረን፡፡
በሽታው ያለበት ደረጃ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑም አስቸኳይ ህክምና ሊደረግላት እንደሚገባ ተነገረን፡፡ በዚህ መሰረትም ህክምናውን ማድረግ ጀመረች፡፡
“በሽታው ሥር የሰደደ በመሆኑና የአንጀቷን አብዛኛውን ክፍል በማጥቃቱ በቀላሉ ሊድን አልቻለም፡፡ ለሁለት ሳምንታት ህክምናው ሲደረግላት ብትቆይም አልዳነችም፡፡ ገና በ18 ዓመት ዕድሜዋ ህይወቷ አለፈ፡፡
“የእህቴን ሞት ባሰብኩ ቁጥር እጅግ የሚፀፅተኝ ችግሯን ቶሎ አውቀንላት ወደ ህክምና ልንወስዳት አለመቻላችን ነው፡፡ ስለ በሽታው ምልክቶች ቀደም ብዬ ባውቅ ኖሮ እርግዝና ነው ከሚለው ጥርጣሬዬ ተላቅቄ፣ እህቴ በወቅቱ ህክምና እንድታገኝና ህይወቷ እንዲተርፍ  ልታደጋት እችል ነበር፡፡” ይህንን አሳዛኝ ታሪክ የነገረችኝ በቅርቡ ታናሽ እህቷን በሞት የተነጠቀችው ትዕግስት መንግስቴ ናት፡፡ ህክምና በወቅቱ ባለማግኘቷ የተነሳ በሽታው የአንጀቷን አብዛኛውን ክፍል ጐድቶ ለሞት እንደዳረጋት እህቷን የመረመራት ሐኪም እንደነገራቸው ገልፃልኛለች፡፡
ለመሆኑ የትልቁ አንጀት ቁስለት በሽታ ምንድነው? ምልክቶቹና መንስኤዎቹስ ምንድናቸው? ህክምናውስ የሚለውን ጉዳይ እንዲያብራሩልን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑትን ዶክተር ታዲዮስ መንከርን አነጋገርናቸዋል፡፡
1.5 ሜትር ርዝመት ያለውና በትንሹ አንጀታችን ዙሪያ የሚገኘው ትልቁ አንጀት የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን በአግባቡ እንዲሆን የሚያደርግና ከጨጓራ ተፈጭቶና ልሞ ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚሰራጩት ምግቦች ውስጥ በቆሻሻነት የሚወገዱትን ወደ ታች ገፍቶ በሰገራ መልክ የሚያስወግድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከቆሻሻው ውሃንና አንዳንድ ጠቃሚ ንጥረነገሮችን መጥጦ ወደ ደም እንዲገቡ ያደርጋል፡፡
ትልቁ አንጀታችን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስበትና አየርና አይነምድርን ቋጥሮ ሲይዝ፣ ድንገት ሆዳችን ይወጠርና ግሣትና እረፍት የለሽ ስቃይ ይገጥመናል፡፡ ይህ አይነቱ ችግር በሚከሰትበት ወቅት ታማሚው አስቸኳይ የቀዶ ጥገና ህክምና ካላገኘ ህይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለ በሽታው ምንነትና መንስኤዎቹ ዶክተር ታዲዎስ ከዚህ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

ለአንጀት ጤና ችግር መነሻው
የትልቁ አንጀት መኮማተር
ይህ አይነቱ የጤና ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው በወጣትነትና በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ውጥረት፣ ጭንቀትና እረፍት የለሽ ህይወት ለዚህ ዓይነቱ የጤና ችግር ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡
ኢንፌክሽን
በቫይረስ፣ በባክቴሪያና በተለያዩ ጥገኛ ህዋሳቶች አማካኝነት አንጀታችን ሲመረዝ፣ የአንጀት ቁስለት ይከተላል፡፡ ይህም አንጀት ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን በማድረግ አጣዳፊ የሆድ ውስጥ ህመም፣ ማስመለስና ማቅለሽለሽ እንዲሁም ትኩሳትና ድካም ያስከትላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ችግር የሚከሰተው በአብዛኛው ንፅህናቸውን ባልጠበቁ ምግቦች ውሃ ሳቢያ ነው፡፡
የትልቁ አንጀት ቁስለት
በሰውነታችን ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ኢንፌክሽን በሚፈጠርበት ወቅት ሰውነታችን ኢንፌክሽኖቹን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ተፈጥሮአዊ ትግል አንጀታችን ለጉዳት ሊዳርገው ይችላል፡፡ ይህም የአንጀት ጉዳት ትልቁ አንጀታችን እንዲላጥና እንዲቆስል በማድረግ ለህመም ሊዳርገን ይችላል፡፡ የአንጀት ቁስለት ህመም አልፎ አልፎ በዘር ሊከሰትም ይችላል፡፡
የአንጀት ካንሰር
ይህ አይነቱ የአንጀት ህመም እጅግ አደገኛና ከጡት፣ ከማህፀንና ከሳንባ ካንሰር ቀሎ ብዙዎችን ለስቃይና ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ በሽታው ዕድሜያቸው ከአርባ አመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል፡፡
ጮማና ስብነት ያላቸውን ምግቦች መመገብ የሚያዘወትሩ፣ በሽታው በቤተሰባቸው ውስጥ ያለባቸውና በሆዳቸው አካባቢ የጨረር ህክምናን የወሰዱ ሰዎች ለዚህ ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡
የፊንጢጣ ኪንታሮት
በፊንጢጣ አካባቢ በሚገኙ የደም ስሮች ማበጥ ሳቢያ የሚከሰት ችግር ሲሆን ችግሩን ሰገራ ለመውጣት ማማጥ፣ ለረዥም ጊዜ መቆም፣ በሙቀት ውስጥ ለረዥም ሰዓት መኪና ማሽከርከርና እረፍት ማጣት ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡ የሆድ ድርቀትም በሽታውን ሊያባብሱት ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
የምግብ መመረዝ
በተለያዩ ለጤና ጎጂ በሆኑ ባክቴሪያዎች የተመረዙ ምግቦችን በምንመገብበትና የተበከለ ውሃን በምንጠጣበት ወቅት ተህዋስያኑ ወደ አንጀታችን ውስጥ በመግባት አጣዳፊ የሆድ ህመምን፣ ማስመለስንና ተቅማጥን ሊያመጡብን ይችላሉ፡፡ ይህ ችግርም በወቅቱ ህክምና ካላገኘ  ተባብሶ አንጀታችንን በማቁሰል ለአንጀት ቁስለት ሊዳርገን ይችላል፡፡
ምልክቶቹ
የትልቁ አንጀት ህመም ውስጣዊና ውጫዊ ምልክቶች አሉት፡፡ አንድ ሰው የትልቁ አንጀት ቁስለት እንዳለበት ጠቋሚ ከሆኑት ምልክቶች መካል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው:-
ውስጣዊ ምልክቶች
ከእንብርት በታች ሃይለኛ ስቃይ ያለው የህመም ስሜት
ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና፣ የድካም ስሜት
የሆድ መነፋት፣ መጮህና የሆድ ድርቀት
የፈስ መብዛት፣ ማስማጥና በፊንጢጣ ደም መውጣት
ውጫዊ ምልክቶች
በቆዳ ላይ እጅብ ያለ ሽፍታ መውጣት
በተለያዩ የሰውነት ክፍሎችና በአጥንት መገጣጠሚያዎች ላይ እብጠት
ክብደት መቀነስ፣
የሆድ መነፋት ወይም ግልፅ ሆኖ የሚታይ የሆድ መነረት ናቸው፡፡
ትልቁ አንጀትን የሚያጠቁት በሽታዎች በርካቶች ቢሆኑም በአገራችን በብዛት የተለመዱትና ለበርካቶች ህመምና ሞት ምክንያት የሚሆኑት ቀደም ሲል የተዘረዘሩት ሲሆኑ የአንጀት ካንሰር  በገዳይነቱ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል፡፡
ስብና ፕሮቲን የበዛባቸውን ምግቦች አዘውትረው የሚመገቡ፣ በተፈጥሮ የአንጀት ቁስለትና አንጀት ላይ የሚፈጠሩ ትናንሽ እብጠቶች ያሉባቸው ሰዎችን በይበልጥ የሚያጠቃው ይህ በሽታ፤ ወደተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች የሚሰራጭና የማይሰራጭ አይነቶች አሉት፡፡ በአገራችን በስፋት የሚታየው በሰውነት ውስጥ የሚሰራጨው አይነቱ ካንሰር ነው፡፡ የትልቁ አንጀት ካንሰር ምልክቶች አሜባ እየተባለ ከሚጠራው በሽታ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ማስማጥ፣ ደም የተቀላቀለበት ተቅማጥ፣ የሆድ ህመምና ቁርጠት በሁለቱም በሽታዎች ላይ የሚታዩ ሲሆን አሜባ በአጭር ጊዜ ህክምና መዳን መቻሉና በሰገራ ምርመራ የበሽታው ምንነት መታወቁ ከአንጀት ካንሰር ይለየዋል፡፡
የትልቁ አንጀት ካንሰር በአገራችን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ የተደረጉ ጥናቶች አለመኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ታዲዮስ መንክር፤ ከሆስፒታሎች የሚገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በጉልምስና ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የበሽታው ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡
የተሟላና የተጠናከረ መረጃ የመያዝ ልምድ ባለመኖሩ ትክክለኛውን የአንጀት ቁስለት በሽታ ታማሚዎች ቁጥር ለይቶ መናገር አስቸጋሪ እንደሆነም ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡
የሽንት ቱቦ፣ የፊኛና የማህፀን ካንሰር ምልክቶች ከትልቁ አንጀት ካንሰር በሽታ ጋር የመመሳሰል ባህርይ ስለአላቸውም አንዳንድ ጊዜ በምርመራ ወቅት የጤና ባለሙያዎችን ሊያሳስቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ባለሙያዎች የትልቁ አንጀት ካንሰር ምርመራን በሚደርጉበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል ሲሉ ዶክተሩ አሳስበዋል፡፡ አንድ ሰው የአንጀት ካንሰር በሽታ ምርመራ ተደርጎለት በሽታው መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በሽታው በሰውነቱ ውስጥ ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩ ሌሎች ምርመራዎች ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህም በሽታው የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹን መንካት አለመንካቱን ለማወቅ ይጠቅማል፡፡ በዚህም በሽታው ያለበትን ደረጃ ማወቅና የህክምናውን ዓይነት መወሰን ይቻላል፡፡  የህመምተኛውን የመዳን እድል ለማወቅም ይረዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለአንጀት ቁስለት ህመም በስፋት የሚታዘዘው መድኀኒት Amoxicillin የተባለው ሲሆን Omepazole እና Clarithromycine የተባሉት መድኀኒቶችም በሽታውን ለማከም አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ቀደም ሲል የአንጀት ቁስለት ህመም መድኀኒት የነበሩት Tetracycline እና Metronidazole (ሜዝል) እየተባሉ የሚጠሩትን መድኀኒቶች የአንጀት ቁስለት አምጪ ባክቴሪያዎች ስለተለማመዷቸውና መድኀኒቶቹ በሽታውን የማዳን ኃይላቸውን በማጣታቸው ምክንያት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እየተደረገ መሆኑን ሃኪሙ ተናግረዋል፡፡
ህክምናው
የቆሰለው የአንጀቱ ክፍል የሚደማ ከሆነ በኢንዶስኮፒ የሚደማውን ቦታ በማከም፣ ደሙን ማቆም፡፡
ህመምተኛው ደም የሚያንሰው ከሆነ፣ የደም ዓይነቱን በመለየት ደም እንዲሰጠው ማድረግ፡፡
ለቁስለቱ መነሻ ምክንያቱ ባክቴሪያ ከሆነ፣ ባክቴሪያውን የሚያጠፉ መድሃኒት መስጠት፡፡
ህመምተኛው የመጠጥ፣ የጫትና የሲጋራ ሱስ ካለበት ሱሱን እንዲያቆም ማድረግ፡፡     

Read 58097 times