Saturday, 15 November 2014 10:22

የአዲስ አበባ ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ በጥር ወር ይጠናቀቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

“ተንጠልጣይ ድልድዮቹ በቀላሉ መጠገን አይችሉም” የሬልዌይ ኢንጂነር
“በቀላሉ ለመጠገን በሚያስችል መልኩ የተገነቡ ናቸው” ኮርፖሬሽኑ

የከተማዋን ትራንስፖርት ችግር እንደሚፈታ የተነገረለት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ከ82 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቀ የተገለፀ ሲሆን ከሶስት ወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
ከሶስት አመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክቱ፤ በዋናነት በቻይናው ኤግዚየም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን ለፕሮጀክቱ 470 ሚሊዮን ዶላር እንደተመደበለትም ይታወቃል፡፡
በሁለቱም መስመሮች 34 ኪ.ሜትር ርዝመት የሚያካልለው የባቡር መስመሩ፤ በአብዛኛው በተንጠልጣይ ድልድዮች የተዋቀረ ነው፡፡ አንዳንድ የባቡር ምህንድስና ባለሙያዎች፤ እየተገነቡ ያሉት ድልድዮች ብልሽት ቢገጥማቸው በቀላሉ መጠገን እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ መስመሮቹ ላይ የተዘረጋው ሃዲድ መበየዱና ተንጠልጣይ ድልድዮቹ የተገነቡበት ኮንክሪት ለሙሌት አስቸጋሪ መሆኑ ጥገና ቢያስፈልግ እንኳ አንዱን መስመር ዘግቶ ሙሉ ለሙሉ ማፍረስ ይጠይቃል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በውጭ ሃገር  የባቡር አገልግሎት ድርጅቶች ውስጥ በሬልዌይ ኢንጅነርነት እንደሰሩ የገለፁት ባለሙያ፤ በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የባቡር መስመር ቴክኖሎጂ ዘመናዊነትን ያልተከተለና ከተማን የማጨናነቅ ባህሪ ያለው ነው ሲሉም ይተቻሉ፡፡
የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበኩሉ፤ የተንጠልጣይ ድልድዮቹ ጥራት አስተማማኝ ነው ይላል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ምላሽ፤ “ድልድዮች ጥገና ቢያስፈልጋቸው እንኳ በቀላሉ ለመጠገን በሚያስችል መልኩ የተገነቡ  ናቸው፤ በዚህ በኩል ምንም ስጋት ሊሆን የሚችል ነገር የለም” ብለዋል፡፡
አያትና ቃሊቲ አካባቢ የተዘረጉ የሃዲድ መስመሮች ፈርሰው እንደገና እየተሰሩ መሆናቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ኃላፊው፤ “የተሰራው ፈርሶ በድጋሚ መስራት ያስፈለገው በአካባቢዎቹ ላይ ለሚገነቡት ዲፖቶች (ተርሚናሎች) ከ300-350 ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በማስፈለጉ ነው፤ በዚህም መሰረት የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡
ለሁለቱ የባቡር መስመሮች በአጠቃላይ 41 ባቡሮች የሚያስፈልጉ ሲሆን ባቡሮቹ በመጪው ወራት ከቻይና ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የገባችው አንዷ ባቡር ስታዲየም አካባቢ በተንጠልጣይ ድልድዩ ላይ በተዘረጋው ሃዲድ አረንጓዴ ሸራ ለብሳ ቆማለች፡፡
ባቡሮቹ ምን አይነት ቀለም ይኑራቸው የሚለውን ለመወሰን ህብረተሰቡ ቀለሙን እንዲመርጥ መጋበዙ የሚታወስ ሲሆን፡፡ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የባቡሮቹ ቀለም አረንጓዴና ሰማያዊ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን በበላይነት እንዲያንቀሳቅሱ ለከፍተኛ ስልጠና ወደ ቻይና ከተላኩት 254 ሰልጣኞች መካከል 52ቱ ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመለሱ ሲሆን ቀሪዎቹ ስልጠናቸውን እንደጨረሱ ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ከሶስት ወር በኋላ በጥር ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገለፀ ቢሆንም በትክክል መቼ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አልታወቀም፡፡

Read 4407 times