Saturday, 15 November 2014 10:38

ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ እየተመከረ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(50 votes)

በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት መካከል የድንበር ይገባኛል ጦርነት መካሄዱን ተከትሎ የሁለቱ መንግስታት ግንኙነት ከተቋረጠ ወዲህ የተጐዳውን የህዝቦች ግንኙነት ለማደስ ያለመ ጉባዔ ትናንት በግዮን ሆቴል ተካሄደ፡፡ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ የሠላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲቲዩት አስተባባሪነት የተደረገው ጉባዔ ቀጣይ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ ጉባዔ ላይ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንና ትስስሩን ለማጠናከር ያግዛሉ የተባሉትን መንገዶች በመከተል፣ በህዝቦቹ መካከል እርቅ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጉባዔው አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሠላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲቲዩት ምክትል ኤግዝኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ተክለሚካኤል በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ሠላምና እርቅ እንዲፈጠርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ምክትል ዳይሬክተሩ በንግግራቸው ላይ እንደጠቆሙት፤ በሁለቱ አገሮች መካከል የቀጠለው የፖለቲከኞች ጠላትነት የአካባቢው ሰላም ጠንቅ ማሳያ ሆኖ ከመቆየቱም በላይ የሁለቱን አገራት ህዝቦች የመገናኘት ዕድል ዘግቷል፡፡ ይህም የህዝቦች ዝምድና መገለጫ የሆነውን ነፃ ግንኙነት  ገድቦት ቆይቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢንስቲቲዩቱ ህዝባዊ ውይይቶች እንዲደረጉ፣ ሁለቱን ህዝቦች የሚወክሉ ወገኖች ተገናኝተው እንዲነጋገሩ፣ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማስቀጠል የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመፈለግ የሚያግዙ ዕድሎችን አመቻችቷል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራውያን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸውን ጥቅም ለመከታተል እንዲችሉ እንዲሁም የኤርትራ ወጣቶች በኢትዮጵያ ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉ፣ ለ“ህዝብ ለህዝብ” ግንኙነቱ መታደስ ቀና ጅማሬ እንደሆነ የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ጅማሬውን በማስቀጠል የሁለቱ አገራት ህዝቦች ሰላምና ትስስር እንዲጠናከር ይደረጋል ብለዋል፡፡
በእርቅ ጉባኤው ላይ በታዋቂው ኤርትራዊ ድምፃዊ ርዕሶም ገብረጊዮርጊስ የተዘጋጀና በኢንስቲቲዩቱ ስፖንሰር የተደረገ የሁለቱን አገራት ህዝቦች መልካም ግንኙነት የሚያመላክት የ“ዕርቅ” የሙዚቃ ክሊፕ ተመርቋል፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት መካከል በተደረገው የድንበር ይገባኛል ጦርነት ሣቢያ  የሁለቱ አገራት ህዝቦች ላለፉት 17 ዓመታት ተለያይተው የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በየዕለቱ ከ200 በላይ ኤርትራውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ ታውቋል፡፡  

Read 16907 times