Saturday, 15 November 2014 10:42

ከመሸ አትሩጥ ከነጋ አትተኛ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ አባት የመሞቻው ጊዜ ደርሶ ኖሮ ልጁን ወደ አልጋው እንዲመጣ ይጠራዋል፡፡ ልጁም ይጠጋውና፤
“አባቴ ሆይ ምን ላድርግልህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አባትየውም፤
“ልጄ ሆይ! እንግዲህ የመሞቻዬ ጊዜ ደርሷል፡፡ ነገር ግን አንተን ምድር ላይ ጥዬህ ስሄድ ምንም ያጠራቀምኩልህ ጥሪት ስለሌለ ትቸገራለህ ብዬ ተጨንቄያለሁ፡፡ ሆኖም አንድ አውራ ዶሮ አለኝ፡፡ የዚህን አውራ ዶሮ አጠቃቀም ካወቅህበት ብዙ ሀብት ታፈራበታለህ” ይለዋል፡፡
ልጁም፤ “እንዴት አድርጌ?” አለው፡፡
አባቱም፤ “አውራ ዶሮ ወደማይታወቅበት አገር ሂድ፡፡ የአውራ ዶሮን ጥቅም ንገራቸው” ብሎ ሃሳቡን አስፋፍቶ ተናግሮ ሳይጨርስ ትንፋሹ ቆመ፡፡
ልጅየው አባቱን ከቀበረ በኋላ አውራ ዶሮ የማይታወቅበት አገር ለመፈለግ ከቤቱ ወጣ፡፡ ብዙ አገር ዞረ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ቦታ መአት አውራ ዶሮ ስላለ ጥቅሙን ያውቁታል፡፡ በመጨረሻ ወደ አንድ ደሴት ሲገባ አንድም ዶሮ የላቸውም፡፡ ቀን መምሸት መንጋቱን እንጂ ምንም ሰዓት አይለዩም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አላቸው፡-
“ይሄ አውራ ዶሮ ይባላል፡፡ እዩ አናቱ ላይ ቀይ ዘውድ አለው፡፡ እንደ ጀግና ጦረኛም እግሩ ላይ ሹል ጫማ አለው፡፡ ሌሊት ሌሊት ሶስት ጊዜ ይጮሃል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ለእናንተው ጥቅም ነው፡፡ በየአንዳንዱ ጩኸቱ መካከል ያለው የጊዜ ርዝመት እኩል ነው፡፡ በመጨረሻ ሲጮህ ልክ ሊነጋ ሲል ነው ማለት ነው፡፡ ቀን ከጮኸ ደግሞ አየሩ ሊለወጥ መሆኑን መናገሩ ነው ማለት ነውና መዘጋጀት ይኖርባችኋል” አላቸው፡፡
ነዋሪዎቹ ሁሉ ተገረሙ፡፡ የዚያን እለት ሌሊት ማንም የተኛ ሰው የለም፡፡ አውራ ዶሮው በውብ ድምፁ አንድ ጊዜ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ፤ ጮኸ፡፡ ቀጥሎ አስር ሰዓት ላይ ጮኸ፡፡ በመጨረሻም ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ጮኸ፡፡ ህዝቡ ጉድ አለ! ስለዚሁ አውራ ዶሮ ሲያወራ ዋለ፡፡ ነገሩ ንጉሡ ጆሮ ደረሰ፡፡ ንጉሡም እንደ ህዝቡ በሚቀጥለው ሌሊት የአውራ ዶሮውን ጩኸት ሲያዳምጡ አደሩ፡፡ በጣም ተደንቀው ልጁን አስጠርተው፤
“ይሄንን አውራ ዶሮ ትሸጥልናለህ ወይ?” አሉት፡፡
ልጁም “አዎን ግን በወርቅ ነው የምትገዙኝ” ሲል መለሰ፡፡
ንጉሡም፤ “በምን ያህል ወርቅ?” አሉት፡፡
ልጁ - “አንድ አህያ ልትሸከም የምትችለውን ያህል” አለ፡፡
ንጉሡ አንድ አህያ የምትሸከመውን ኪሎ አስጭነው ሰጡትና ወደቤቱ የአባቱን ውለታ እያሰበ ሄደ፡፡ ንጉሡም አውራ ዶሮአቸውን ወሰዱ፡፡ ከዚያን እለት ጀምሮ የዚያ ደሴት ህዝብ ጊዜና ሰዓት ለየ፡፡
***
አውራ ዶሮ የሚሸጥልን አንጣ፡፡ ሰዓትና ጊዜን መለየት ለማንኛችንም ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ “የቸኮለች አፍሳ ለቀመችን”ና “የቆየ ከሚስቱ ይወልዳል”ን ዛሬም ባንረሳ መልካም ነው፡፡ ብልህ አባት ለልጁ የዘለአለም ሀብት ማውረሱን ካስተዋልን ዘላቂ ልማት፣ ዘላቂ አገር ይኖረናል፡፡ ቤትና ቀን የለየ፣ ጊዜና ሰዓት ያወቀ ወደፊት መሄድም፣ ባለበት መቆምም፤ ማፈግፈግም የሚያውቅ የነቃ የበቃ ወራሽ ካለን የነገን ጥርጊያ መንገድ አበጀን ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ቀለበት መንገድ መስራት ብቻ ሳይሆን ከቀለበት መውጪያውንም እንድንሰራ ፈር ይቀድልናል፡፡ ከተማረ የተመራመረ የሚለው ትርጉም የሚኖረው እዚህ ላይ ነው፡፡
“ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላል ጸሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ ጊዜን ያላወቀ እንኳን ሥልጣኑን ራሱን ያጣል፡፡ በማንኛውም ደረጃ ላይ ቢሆን “በትክክል ጊዜን መጠቀም እወቅበት፤ ይላሉ ጠበብት፡፡ አለልክ አትጣደፍ፤ ነገሮች ከቁጥጥርህ ይወጣሉና፡፡ የትክክለኛዋ ቅፅበት ሰላይ ሁን፡፡ የጊዜን መንፈስ አነፍንፈህ አሽትት፡፡ ወደ ስልጣን (ድል) የሚወስዱህን መንገዶች በዚያ ታገኛለህ፡፡ ጊዜው ካልበሰለ ማፈግፈግን እወቅበት፡፡ ሲበስል ደግሞ ፈፅሞ ወደኋላ አትበል!” የሚሉ ፀሐፍት ታላቅ ቁምነገር እየነገሩን ነው፡፡
ጊዜን በትክክል መጠቀም የሚችል ዝግጅትን ዋና ጉልበቱ ያደርጋል፡፡ ድግሱ ከመድረሱ በፊት የምግብ እህሉን፣ የጌሾ ጥንስስ ስንቁን ማደራጀትና በመልክ መልኩ መሸከፍ፣ መጥኖ መደቆስ፣ መብሰያና መፍያ ጊዜውን በቅጡ ለድግሱ ሰዓት ማብቃትን ከሸማች እስከ አብሳዩ ውል ሊያስገቡት ይጠበቃል፡፡
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሸቀዳድሞ  
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ”
የሚለው የደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ይሄንኑ ጊዜ እንኳን ከበሰለ በኋላ እንዲሁም መዘናጋት እንደማይገባ ያስገነዘቡት ነው፡፡
ያለመላ ግጭት ጅልነት ነው፡፡ የዝግጅት ጊዜ ወስዶ አስቦ፣ ሁሉን አመቻችቶ ነው ትግል፡፡ አንዴ ከገቡ ደግሞ መስዋዕት መኖሩን ሳይረሱ ምንጊዜም ሳያቋርጡ፣ ሳይማልሉና ሳይታለሉ መቀጠል ግድ ይሆናል፡፡
በሼክስፔር ሐምሌት ቴያትር ውስጥ፤
“ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!”
የሚለን የጊዜ ዕቅጩነት (Perfect - imning) ጉዳይ ነው፡፡
“አውራ ዶሮ ጮሆ፣ መንጋቱን ነገረኝ
ዛሬ ሌሊት ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ” ያለውን ያገራችንን ወጣት ገጣሚ ረቂቅነትም አለመዘንጋት ነው!!
የሁሉ ነገር መሳሪያ ጊዜ ነው!
ዘመን የጊዜ ጥርቅምና የቅራኔና የሥምረት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህም እንደታሪክ ክፉውንም ደጉንም ማጣጣሚያውና ያንን የመመርመር፣ ከስህተት የመማር፣ ነገን የመተለም ጉዳይ ነው ጊዜን ማወቅ ማለት መጪውንም ምርጫ በጊዜ ማስላት ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጊዜን ጨበጥክ ማለት ድልን ጨበጥክ ማለት ነው፤ የሚባለው እንዲያው ለወግ አይደለም! ጊዜን እንደመሳሪያ የምንቆጥረው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ አውራ ዶሯችንን በጊዜ እንግዛዛ - ሌሊትን፣ ተስፋንና ንጋትን - ይንገረን፡፡ ይህ ሚጠቅመን በማታ ሩጫ እንዳንጀምር ከነጋ በኋላም እንዳንዘናጋ ነው! “ከመሸ አትሩጥ፣ ከነጋ አትተኛ” የሚለው የወላይታ ተረት አደራ የሚለን ይሄንኑ ነው!!



Read 6216 times