Saturday, 15 November 2014 11:02

አሣሣቢው የአዕምሮ ጤና ችግር!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከ1ሚ. በላይ ህዝብ ተኝቶ መታከም በሚያስፈልገው የአዕምሮ ህመም ይሰቃያል
በአዕምሮ ህሙማን ህክምና ማዕከል ያሉት አልጋዎች ከ700 አይበልጡም


በርካታ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር እንደገጠማቸው የሚጠቁሙ ምልክቶች ቢታይባቸውም ታማሚነታቸውን አምነው ለመቀበልና ለችግራቸው መፍትሄ ለመፈለግ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አዕምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት ሊዳረግና የተለመደ ተግባሩን መወጣት ሊሳነው ይችላል፡፡ ለአዕምሮ መታወክ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ስነ ልቦናዊ ውጥረቶች፣ ስደት፣ ጦርነት፣ ተገዶ መደፈር፣ አደንዛዥ እፆች፣ የመኪና አደጋ፣ ኢንፌክሽን አምጪ በሽታዎችን አለመቆጣጠር፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎችን የሚያማክሩ የስነ ልቦና ባለሙያዎች አለመኖር… ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በአዳማ ከተማ “Media and Mental Illness” በሚል ርዕስ ወርክሾፕ አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ  የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚያመለክቱት፤ የአዕምሮ ጤና ችግር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን  ስቃይና ሞት ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡ በወርክሾፑ ላይ ጥናታቸውን ካቀረቡት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአዕምሮ ሀኪምና በዩኒቨርሲቲው የአዕምሮ ህክምና ክፍል መምህር፣ ዶ/ር መስፍን አርአያን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ፤ በአዕምሮ ጤና ችግር ዙርያ አነጋግራቸዋለች፡፡



የአዕምሮ ጤና ችግር ስንል ምን ማለታችን ነው?
የአዕምሮ ጤና ችግርን በሶስት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ ቀላል፣ መካከለኛና ከባድ ወይም በፈረንጅኛው ሳይኮሲስ የሚባለው ማለት ነው፡፡ ችግሮቹ እንደየሁኔታው የህክምና እርዳታ ሊደረግላቸው ይችላል፡፡ ቀላል የአዕምሮ ጤና ችግር የምንለው በተለያዩ ምክንያቶች አዕምሮአችን ሲወጣጠርና ሲጨነቅ የሚከሰት ሲሆን ይህ ችግር በከተማም ሆነ በገጠር ይስተዋላል፡፡ በዕለት ተዕለት ህይወታችን በሚገጥሙን ነገሮች ስንጨናነቅ ሊከሰት የሚችል ችግርም ነው፡፡ ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን በሚገባ ስለሚያውቁ ወደ ሀኪም ሔደው የህክምና እርዳታ ለመጠየቅ የሚችሉ ናቸው፡፡
መካከለኛ የአዕምሮ ጤና ችግር የምንለው ደግሞ የስሜት መዋዠቅ ይታይባቸዋል፡፡ አንድ ወቅት ድብርት ውስጥ ይገባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተቃራኒው ይሆናሉ፡፡ እነዚህ በሁለት አይነት የአዕምሮ ጤና ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ በአንድ አገር እስከ 20 በመቶ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ቁጥራቸው ከ25-40 በመቶ ሊደርስም ይችላል፡፡ ትንሹን እንኳን ወስደን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ብናየው፣ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ቢያንስ 18 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ በቀላልና መካከለኛ የአዕምሮ ጤና ችግር የሚጠቃ ነው፡፡ ከባዱና ሳይኮሲስ እየተባለ በሚጠራው የአዕምሮ ጤና ችግር የተጠቁ ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ሆኖ እይታቸው፣ አመለካከትና የአስተሳሰብ ባህርያቸው ሲዛባ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ለሌሎች የማይታይን ነገር ማየት፣ ሌሎች የማይሰሙትን ድምፅ መስማት … አይነት ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የባህርይ ለውጥም ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ኬጂቢ ቦንብ ጠምዶ እየተከታተለኝ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ያን ግዜም ራሳቸውን ለመከላከል በሚወስዱት እርምጃ በሌሎች ሰዎች ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና ችግር ከምንላቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ድብርት ነው፡፡ ድብርት መዳን የሚችል ህመም ሲሆን በአግባቡ ካልታከመ ህይወትን የሚያሳጣ አደገኛ ችግር ነው፡፡ በዚህ ሳይኮሲስ እያልን በምንጠራው አደገኛ የአዕምሮ የጤና ችግር የተጠቁ ሰዎች በሆስፒታል ውስጥ ተገኝተው የቅርብ ክትትልና እርዳታ ማግኘት የሚገባቸው ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገራችን 1.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በከፍተኛ የአእምሮ ጤና ችግር እየተሰቃዩ ነው፡፡ ዛሬውኑ ተኝቶ መታከም፣ ዛሬውኑ መድኀኒትና መርፌ ማግኘት፣ ዛሬውኑ የምክር ህክምና ማግኘት የሚገባቸው ናቸው፡፡
ለአዕምሮ ጤና ችግር ዋንኛ መንስኤዎች ተብለው የሚጠቀሱት ምንድናቸው?
ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ውጥረቶች፣ ተገዶ መደፈርና አደንዛዥ እፆችን መጠቀም ዋንኞቹ ብለን ልንጠራቸው እንችላለን፡፡ እነዚህ ነገሮች የአዕምሮ ጤና ችግር ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር በገጠማቸው ጊዜ ወደ ህክምና ተቋማት ሄዶ እርዳታ ማግኘት አለመፈለጋቸው በቀላሉ ሊድን የሚችለውን ችግር ውስብስብና አደገኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡
አብዛኛው የአዕምሮ በሽተኛ በየቤቱና በየፀበሉ ታስሮ ነው ያለው፡፡ ጥቂቱ ደግሞ በየመንገዱና በየጎዳናው እየዞረ ነው፡፡ እነዚህ ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው እርዳታ ማግኘት ቢችሉ ችግሩን ለማቃለል ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ህሙማኑ ወደ ህክምና ተቋማት ቢሄዱ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ይችላሉ? በአገራችን ምን ያህል ተቋማትስ አሉ?
በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች የህክምና ተቋማት አሉ፡፡ ለአዕምሮ ጤና ችግር ህክምና የሚሰጡ ማለት ነው፡፡ አስተኝቶ ለማከም ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ በአጠቃላይ የግሉንም፣ ወታደራዊ የህክምና ተቋማትን ጨምሮ ከ700 የማይበልጡ አልጋዎች ናቸው ያሉን፡፡ ይህ ደግሞ ከችግሩ አንፃር ኢምንት ነው፡፡ ስለዚህም ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ የሚገባን መከላከሉ ላይ ነው፡፡ ያለበለዚያ ውጤት የለውም፡፡ እኛ ሃኪሞች ወደ ህክምና ተቋማት የመጡልንን ጥቂት ዕድለኞች ማከም ላይ ብቻ ተወስነን መቅረት አይገባንም፡፡ ሁላችንም መከላከሉ ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል፡፡

Read 4978 times