Saturday, 15 November 2014 11:07

ናይል ኢንሹራንስ ከ64ሚ. ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ናይል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከምንጊዜም የላቀ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ የኩባንያው የዳሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ማስረሻ ወ/ሥላሴ ሰኔ 30 ቀን የተዘጋውን የ2014 ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለ አክሲዮኖች ባቀረቡበት ወቅት፣ ኩባንያው፣ ከምስረታው ጀምሮ ባለፉት 20 ዓመታት አስመዝግቦ የማያውቀውን 64,845,197 ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልጸው፤ ይህም ትርፍ የኩባንያው የተጣራ ሀብት 35 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ከጠቅላላ ኢንሹራንስ 300 ሚሊዮን 433 ሺህ 888 የአረቦን ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን፣ ለዚህም ዕድገት መገኘት ኢኮኖሚው ያሳየውን አዎንታዊ ዕድገትና ኩባንያው በተለያዩ አሰራሮች ላይ የወሰዳቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱና ከዚያ በፊት ባሉት ዓመታት ትላልቅ መጠን ያላቸው የካሳ ጥያቄዎች ቀርበው ክፍያ መፈፀሙን የጠቀሱት አቶ ማስረሻ፤ ባለፈው ዓመት ከጠለፋ ዋስትና የተገኘው ሂሳብ ተቀንሶ 152 ሚሊዮን 539 ሺህ 344 ብር ካሣ መከፈሉንና ይህም ከካቻምናው ጋር ሲነፃፀር የ10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ ከበጀት ዓመቱ የተጣራ ትርፍ 64, 845, 197 ብር ውስጥ የዓመቱ ህጋዊ መጠባበቂያ 6, 484, 520 ብር እንዲሁም ለዳይሬክተሮች ቦርድ የሚከፈለው 1,780,647 ብር ከተቀነሰ በኋላ ቀሪው 56,672,531 ብር የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል ከ100 ሚሊዮን ወደ 200 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ጠይቀው የባለ አክሲዮኖቹን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ በዓመቱ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል የነበረው በዋጋ ላይ ያተኮረ ውድድር መጨመር፣ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አፈጻጸም ላይ የታየ ችግር እንደሆነ የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አነስተኛነት ተከትሎ የአዳዲስ ኩባንያዎች መቋቋም፣ በአረቦን ዋጋ ላይ ብቻ ያተኮረውን ፉክክር የበለጠ ያንረዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡   

Read 1789 times