Saturday, 15 November 2014 11:09

መንግሥት የመብራትን ጉዳይ “ሆድ ይፍጀው” ቢል ይሻለዋል!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(15 votes)

በቻይና የመብራት ኃይል ኃላፊው ሰክረው ለ6 ሰዓት መብራት ጠፋ
እኛ አገር ማንም ሰው ሳይሰክር በቀን መቶ ጊዜ መብራት ይጠፋል    

             ሰሞኑን በምስራቃዊ ቻይና ሄናን በተባለች ግዛት የተሰማው ወሬ ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ የመብራት ኃይል ኩባንያ ኃላፊው ድብን ብለው ሰክረው፣ ከፊል አገሪቱ ለ6 ሰዓት በጨለማ ተዋጠች ይለናል ቢቢሲ፡፡ (“አልሰሜን ግባ በሉት” አሉ!) እኛ አገር እኮ ማንም ሳይሰክር ላለፉት 6 ዓመታት መብራት ሲጠፋብን ከርሟል፡፡ (ቢቢሲን ታዘብኩት!)
እርግጥ ነው ቻይና በኢኮኖሚ አቅሟ ዓለምን በሁለተኛነት እየመራች እንደሆነ አይጠፋንም፡፡ እኛም ብንሆን ግን የዋዛ አይደለንም፡፡ ላለፉት 8 ዓመታት ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግበናል፡፡ (ያውም እኮ ያለ መብራት!) አንዳንድ ጨለምተኛና የኒዮሊበራል አቀንቃኞች እድገቱን ባይቀበሉትም አይጨንቀንም፡፡ ለምን ቢሉ---እነ አይኤምኤፍ እንደሆነ ተቀብለውታል፡፡ የምዕራብ ሚዲያዎችም ዘግበውታል፡፡ ኦባማም ተደምመዋል፡፡ (አለዚያማ “የምርጫ ተሞክሮ እንለዋወጥ” አይሉም ነበራ!)
 ቢቢሲ ግን ይሄን እውነታ አላወቅሁም ለማለት-- የእኛን የ6 ዓመት የኃይል መቆራረጥ ትንፍሽ ሳይል የቻይናን ለመዘገብ ተጣደፈ፡፡ (የሚዲያ ሽፋን በዘመድ ሆነ እንዴ?) ከምሬ ነው የምላችሁ… 6 ዓመት በኃይል መቆራረጥ ከተንገላታነው ይልቅ የሚዲያ ሽፋን ማጣታችን በጣም ያበግናል፡፡ (ወይ ከመብራት ወይ ከሚዲያ አልሆንም!)
በነገራችን ላይ በቻይና መብራቱ ከመጥፋቱ በላይ የሚያስገርመው አጠፋፉ ነው፡፡ እንደኛ አገር የህዝብ ቁጥር ስለጨመረ ወይም በሙስና ፎርጅድ ትራንስፎርመር ስለተገዛ አሊያም ፊውዝ ስለተቃጠለ አይደለም ኤሌክትሪክ የተቋረጠው፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ በሉ ስሙኝ የሆነውን ልንገራችሁ፡፡
የሄናን ግዛት የመብራት ሃይል ሰራተኞችና አለቃቸው ወደ አንድ መሸታ ቤት ጐራ ይሉና ሲጠጡ ያመሻሉ፡፡ በርካታ ሳጥን ቢራ ከጨለጡና የአልኮል መጠጦችን ከደጋገሙ በኋላ ነው ችግር የተፈጠረው፡፡ መሸታ ቤቱ አንድ ዙር በነፃ ይጋብዘን ብለው ድርቅ አሉ፡፡ መጠጥ ቤቱ ደግሞ “በምን እዳዬ?” ብሎ አሻፈረኝ ይላል፡፡ ይሄኔ ብጥብጥ ተነሳ፡፡ የመብራት ኃይል ኩባንያው ሠራተኞች እቃ ሰባበሩ፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፡፡ የኩባንያው ኃላፊ የመጠጥ ቤቱን መብራት እንደሚያስቆርጥባቸውም ዛተ፡፡ ዛቻውንም ወዲያው ተግባራዊ አደረገው፡፡(ዛቻ ብቻማ የፈሪ ነው!) እዚያው እያሉ ወደ መ/ቤቱ ይደውልና ለጥገና በሚል የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲቋረጥ ያዛል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም መሸታ ቤቱ ብቻ ሳይሆን  ከፊል አገሪቷ በጭለማ ተዋጠች፡፡ (“ለኃጥአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል” አሉ!)
 የሃይል መቋረጡን ተከትሎም በመንግስት ባለቤትነት የሚመራው የኤሌክትሪክ ኩባንያ ይቅርታ ጠየቀ (የቻይና ይቅርታ እጅ በእጅ ነው!) ከዚያ ወደ እርምጃ ገባ፡፡ መጀመሪያ መብራቱ እንዲቋረጥ ያዘዘውን ሥራ አስኪያጅ ከስራው አባረረው፡፡ (እኛ አገር 6 ዓመት ጠፍቶብንም የተባረረ ሃላፊ የለም!) አንድ ሠራተኛ ለሁለት ዓመት ከስራ የታገደ ሲሆን ሌሎች መሸታ ቤቱን የበጠበጡ የመብራት ኩባንያው ሰራተኞችም ከገንዘብ ቅጣት ጋር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ (የሙስና ክስም አይቀርላቸውም!)
ነገርዬው ቢያስገርምም ከእኛ አገሩ ግን አይብስም፡፡ እዚያስ አለቅዬው ሰክሮ ነው መብራት ያስጠፋው፡፡ እኛ ጋ እኮ እንኳን አልኮል ውሃ ሳይቀምሱ ነው ማጥፋት የሚጀምሩት፡፡ አንድያውን እንደ ቻይናዎቹ ጠጥተው ቢሆን እኮ ደህና ሰበብ እናገኝላቸው ነበር፡፡ (ሰበብም መላም ያጣንለት ችግር ሆነ!)
እኔ የምለው ግን የኃይል መቆራረጡ ሊሻለው ነው ስንል ብሶበት አረፈው አይደል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተከታታይ ለ4 ቀናት መብራት የጠፋባቸው ሰፈሮች ነበሩ፡፡ መንግስት ደግሞ የግድ መልስ መስጠት ስላለበት መልስ ሰጥቷል (ዝም ነበር የሚሻለው!)
እናላችሁ---የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የሃይል መቆራረጡ የተከሰተው በጣና በለስ ማሰራጫ ጣቢያ በተፈጠረ የባትሪ ችግር እንደሆነ ጠቁመው፤በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ መቀረፉን ተናግረዋል፡፡ (ማረጋገጫ ሳይሰጡን እንዴት እንመናቸው?!) አጠቃላይ የሃይል መቆራረጥ ችግርን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽም፤ ችግሩ ከማሰራጫ መስመር ጋር የተያያዘ እንደሆነና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡ (እኔ መንግስትን ብሆን፣ እንደ አርቲስቱ “ሆድ ይፍጀው” ነበር የምለው!) ሚኒስትሩ ሌላው ቢቀር እንኳን ምነው ትንሽ ጊዜውን ገፋ ቢያደርጉት?! (ሁለት ወር ከሚሉ ሁለት ዓመት!) “ልማታዊ መንግስታችን” ቃል አባይ ነው ለማለት እኮ አይደለም (ምን ቁርጥ አድርጎኝ!) የዘንድሮ ጊዜ እንደ ድሮ አይደለም ብዬ እኮ ነው፡፡ ወዲያው ነው ከች የሚለው (የድሮ ሁለት ወር ዘንድሮ ሁለት ሳምንት ማለት ነው!) አልተጠናም  እንጂ ሳስበው የጊዜ “ግሽበት” ሳይከሰት አልቀረም፡፡
እኔ የምለው… በአገራችን 18 ሚሊዮን ህዝብ በቀላልና መካከለኛ የአዕምሮ ጤና ችግር የተጠቃ መሆኑን ሰምታችኋል? ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከ1ሚ. በላይ ሰዎች በከፍተኛ የአዕምሮ ጤና ችግር እየተሰቃዩ መሆኑንስ? እንደተባለው ከሆነ እኮ፣ ከ1ሚ. በላይ ህዝብ አሁኑኑ ተኝቶ ህክምና መጀመር ያለበት ነው፡፡ ክፋቱ ግን ድሃ ነን፡፡ ለአእምሮ ህመምተኞች በአጠቃላይ ያለው አልጋ ከ700 በታች ነው ተብሏል፡፡ የሃኪሙ ቁጥር ደሞ ስንት እንደሚሆን አስቡት፡፡ (ከሃኪም ይልቅ ፖለቲከኛ፣ ከሆስፒታል አልጋዎች ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበዙባት አገር!)
እናላችሁ … ይሄን መረጃ ከሰማሁ በኋላ ምን አልኩ መሰላችሁ? ለአገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መንስኤው የአዕምሮ ጤና ችግር ቢሆንስ? (ከሚታከመው የማይታከመው ይበልጣል!) ይታያችሁ … እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ስልጣኑን፣ ፖለቲካውን፣ ተቋማቱን፣ ወዘተ … የመቆጣጠር ዕድል ባገኙ ጊዜ ምን እንደሚፈጠር! ግልፅ ነው፡፡ ውጥንቅጥ፣ ለማመን የሚከብዱ ክስተቶች፣ ለማሰብ የሚቸግሩ ውሳኔዎች፣ ግራ የተጋቡ እርምጃዎች … በአጠቃላይ ጤንነት የጎደላቸው እንቅስቃሴዎች በአገሪቱ ላይ ይነግሳሉ፡፡ (ደግሞም ነግሰዋል እኮ!) ለምን በማስረጃ እያስደገፍን አናያቸውም፡፡ ከቅርቡ እንጀምር፡፡
ባለፈው እሁድ ይመስለኛል፡፡ በከተማዋ የሚታወቁ የታክሲ መሳፈሪያ ፌርማታዎች ድንገት ተቀያይረው ተገኙ ተባለ፡፡ ይታያችሁ---በሚዲያ አልተነገረም፡፡ የታክሲ ሹፌሮችና ተሳፋሪዎች አልሰሙም፡፡ ፌርማታዎቹን የቀያየረው ወገን አልታወቀም፡፡ (“ኃላፊነቱን እወስዳለሁ” የሚል ጠፋ!) እናም … ሳምንቱ እንዲሁ ሲታመስ---ነዋሪዎችም ሲንገላቱና ሲያማርሩ ሰነበቱ፡፡ ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሲጠየቅ ምን ቢል ጥሩ ነው? “ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመካከርን ነው” (ችግር እየፈጠሩ ምክክር መቀመጥ ተጀመረ?)
እስቲ ደግሞ  ብዙ የጤና የማይመስሉ ነገሮች ወደምንታዘብበት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጎራ ደረስ ብለን እንመለስ፡፡ (ጦቢያ የተቃዋሚዎችም እኮ ናት!) እኔ የምለው---መኢአድ ውስጥ ምንድነው የተፈጠረው? መፈንቅለ መንግስት እየቀረ ነው በሚባልበት ጊዜ፣የፓርቲው የቀድሞ ፕሬዚዳንት “መፈንቅለ ሥልጣን” ተፈጸመብኝ እያሉ እኮ ነው (ኢህአዴግ በሳቅ ነው የሚሞተው!) ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በድርጊቱ “የፓርቲው የበላይ ጠባቂ” የኢንጂነር ኃይሉ ሻውል እጅ አለበት፡፡ እኔን አውርደው ለ4 ዓመት ከፓርቲው ታግደው የቆዩትን እነ ማሙሸትን ሥልጣን አሲዘዋል ብለዋል- ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የፓርቲው ጉባኤ ከስልጣን የወረዱት አቶ አበባው መሃሪ፡፡ እኔን የገረመኝ ከሥልጣን መውረዳቸው ሳይሆን   የወረዱበት መንገድ ነው፡፡በነገራችን ላይ “የፓርቲው የበላይ ጠባቂ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ “ሹም ሹር” የሚያካሂድ ማለት ነው እንዴ? (የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አባባል ይዤ ነው!) ደግሞ እኮ ሌሎቹ ፓርቲዎቹ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ የመኢአድ ልዩ ቀለም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይሄን “የፓርቲ የበላይ ጠባቂ” ጉዳይ ወደ አገር ከፍ ስታደርጉት ምን ይሆናል መሰላችሁ? “የኢትዮጵያ  የበላይ ጠባቂ” እናም--- አሁን ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን ሲወርዱ “የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ” ተብለው ቢሾሙ ብላችሁ አስቡ፡፡ (ፈረንጅ “ዊርድ” የምትለዋን ቃል የሚጠቀመው እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመው ይመስለኛል!)
ለማንኛውም ግን ----ብዙ የጤንነት የማይመስሉ ነገሮች እያየን ነው፡፡ ለጊዜው መፍትሄው ምን መሰላችሁ? የዓለም ጤና ድርጅት የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች ድጋፍ እንዲሰጠን መማጸን ብቻ ነው፡፡

Read 3778 times