Saturday, 15 November 2014 11:21

የኦባማ ማስቲካ ቻይናውያንን ክፉኛ አስቆጣ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ሰሞኑን  በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ በተካሄደው የእስያ ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ በስብሰባ ማዕከሉ ውስጥ ማስቲካ ሲያኝኩ መታየታቸው ቻይናውያንን ክፉኛ እንዳስቆጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ኦባማ ቤጂንግ ከደረሱበት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ፣ በወጡ በገቡ ቁጥር ማስቲካ ሲያኝኩ እንደነበር የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ይፋ መደረጋቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ የኦባማ ድርጊት የቻይናን ታዋቂ ምሁራን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን እንዳስቆጣ ጠቁሟል፡፡ኦባማ በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይ ማስቲካ ማኘካቸውን ቻይናውያን በንቀት እንደተረጎሙትና ሲና ዌቦ የተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽም፣ ኦባማን በሚተቹ አስተያየቶች መጥለቅለቁን ዘገባው ገልጧል፡፡“ገና ከመኪናቸው ሲወርዱ ጀምሮ፣ እንደ ስራ ፈት ማስቲካ እያኘኩ ነበር” ብለዋል በቢጂንግ ሲንጉሃ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ይን ሆንግ፣ ድርጊቱን በማውገዝ በጻፉት ጽሁፍ፡፡
ማስቲካ ማኘክ በአንዳንድ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት፣ እንደ ነውር እንደሚቆጠር የጠቆመው ዘገባው፣ ሲንጋፖር ማስቲካ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ የሚከለክል ህግ እንዳወጣችና በጃፓንም በስራ ላይ ማስቲካ ማኘክ ክልክል እንደሆነ አመልክቷል፡፡

Read 4577 times