Saturday, 22 November 2014 11:37

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢቦላ ስጋት በወር 8 ሚ. ዶላር እያጣ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በ 6 ወራት 8 አዳዲስ አውሮፕላኖችን አስገባለሁ ብሏል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ በፈጠረው ስጋት ምክንያት የመንገደኞች ቁጥር በመቀነሱ፣ በወር ከ8 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ እያጣ እንደሆነ ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
የአየር መንገዱን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያምን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ኢቦላ ለአየር መንገዱ ከየትኛውም አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ በበለጠ በእንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ተግዳሮት ሆኖበታል፡፡
ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የአየር መንገዱ ዋነኛ ማዕከል፣ በኢቦላ ቫይረስ ከተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የረጅም ሰዓታት በረራ የሚወስድ ርቀት ላይ ቢገኝም፣ በሽታው በአየር መንገዱ ተጓዦች ቁጥር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ አልቀረም ያሉት አቶ ተወልደ፤ ሁኔታው በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚቀየርና የመንገደኞች ቁጥርም ወደነበረበት እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡በአገራቱ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ፣ በመላ አህጉሪቱ ከሚደረጉ በረራዎች በአብዛኞቹ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩንና በሽታው ለአፍሪካ አየር መንገዶች ዋነኛው ስጋት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢቦላ ወደ አፍሪካ አገራት በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ስጋት መፍጠሩን የጠቀሰው ዘገባው፤ በተለይም በእስያውያን  መንገደኞች ዘንድ ያለውን ፍላጎት እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ በዘርፉ የሚታዩ የገበያ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ አየር መንገዱ የቀየሳቸውን የረጅም ጊዜ የዕድገት ዕቅዶች መተግበሩን እንደሚቀጥል ገልጸው፣ እስከ መጪው 2015 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት፣ 3 ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ጨምሮ 8 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ገዝቶ በስራ ላይ እንደሚያሰማራ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለት ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት የሚውል የ41.4 ሚሊዮን ዶላር ብድር አይኤንጂ ካፒታል ከተባለ አሜሪካ የፋይናንስ ተቋም ማግኘቱን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ብድሩ መገኘቱና አውሮፕላኖቹ መገዛታቸው፣ በአፍሪካ ትልቁ የጭነት አየር መንገድ ሆኖ የመዝለቅ ዕቅድ ለያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅምንና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተገልጿል፡፡

Read 3406 times