Saturday, 22 November 2014 11:35

“መኢአድ የበላይ ጠባቂ የለውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“እኔ ከአቶ አበባው በላይ ለመኢአድ ዋጋ ከፍያለሁ

በቅርቡ በተካሄደው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለአራት ዓመት ታግደው የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ ወደ ፓርቲው ተመልሰው በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው የተካሄደውን ድንገተኛውን ምርጫ ተከትሎም የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው… “መፈንቅለ ሥልጣን” ተካሂዶብኛል ያሉ ሲሆን ሂደቱ ከፓርቲው ደንብ ውጪ ነው ሲሉም ተቃውመውታል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ አወዛጋቢውን ምርጫ ጨምሮ ለአራት ዓመት ስለታገዱበት ሁኔታ፣ ስለ እርቁ፣ ፓርቲው ስላለበት አቋምና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ አቶ ማሙሸትን በፅ/ቤታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡


ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንፃር በቅርቡ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ ፕሬዚዳንት መመረጡ አግባብ ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ የአቶ አበባውን ስልጣን ካየን፣ በህግ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አይደሉም፡፡ ያልሆኑበት ምክንያት ሐምሌ 13 እና 14 ቀን 2005 ዓ.ም ተደረገ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ኮረም አልተሟላም፡፡ ይህንንም መላው የጉባኤው ተሳታፊዎች በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡ ከዚያም ምርጫ ቦርድ፤ “በምልአተ ጉባኤው ያልተመረጠ ፕሬዚዳንት ነው” ብሎ የአቶ አበባውን ፕሬዚዳንትነት ውድቅ አድርጓል፡፡ ህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ቦርዱ ለእነ አቶ አበባው ያለ ምልአተ ጉባኤ ምርጫ መካሄዱን በደብዳቤ አሳውቋቸዋል፡፡ እነሱ ግን “ምርጫ ቦርድ አያገባውም” ብለው በጋዜጦች ላይ ሲመላለሱበት ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ ፓርቲው በህገ ወጥ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ጠቅሶ፣ ለ6 ጊዜ ያህል ደብዳቤ ፅፎላቸዋል፡፡ ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም ደግሞ ቦርዱ ከማንም ፓርቲ ጋር ውህደትና፣ ጥምረት ማድረግም ሆነ በፓርቲው ማህተም መጠቀም እንደማይችሉ ጠቅሶ ደብዳቤ ፅፎላቸዋል፡፡ ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ከአንድነት ፓርቲ ጋር ሊደረግ የነበረው የውህደት ስምምነት የቀረው በዚያ ምክንያት ነው፡፡
የምርጫ ቦርድን ትዕዛዝ ጥሰው እንዋሃዳለን ብለውም ነበር፤ ነገር ግን ቦርዱ ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ፤ “ይሄን ብታደርጉ በህግ እንጠይቃችኋለን” ብሎ ማስጠንቀቂያ ፅፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ አቶ አበባው በቦርዱም ሆነ በፓርቲው ህገ ደንብ ስልጣን አልነበራቸውም፡፡
የአሁኑን ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ያካሄዱት በ2003 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በሙሉ ድምፅ ተመርጠው የነበሩት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ናቸው፡፡ ይህ የተደረገበት ምክንያት ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ፕሬዚዳንት እሳቸው ብቻ ስለነበሩ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም ሆነ በ2005ቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የነበሩት አባላት ተሟልተው መገኘታቸው ተረጋግጦ ነው የአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤው የተደረገው፡፡ ይሄንንም ሁለት የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡
እርስዎን ጨምሮ 14 ሰዎች ከ2003ቱ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ የታገዳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
በወቅቱ የታገድነው በስህተት ነበር፡፡ በአቶ ያዕቆብ ለኬ የተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንትነት አመራረጥ ላይ ልዩነት በመፈጠሩ ነው፡፡ በወቅቱ በምክር ቤቱ ሳይቀርብና ውሳኔ ሳይሰጥበት አቶ ኃይሉ፤ “አቶ ያዕቆብን ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት አድርጌዋለሁ” አሉ፡፡ ይህንን ህገ ወጥ አካሄድ ነው በማለታችን፣ በተፈጠረ ችግር እኛን ከሰሱንና በፍ/ቤት እንድንታገድ ተደረገ፡፡ በፍ/ቤት ከታገድን በኋላ የዲሲፒሊን እርምጃ ተወስዶባችኋል የሚል የእግድ ደብዳቤ እንደገና መጣ፡፡ ይህንን የእግድ ደብዳቤ የተመለከተው ፍ/ቤቱ፤ “አንድ ሰው ሁለት ክስ ሊቀርብበት አይችልም” በማለት፣ የዲሲፒሊን እርምጃውን ውድቅ አደረገው፤ የቀረውን “ሁከት መፍጠር” የሚል ክስ “ሁከት የለም፤ ፓርቲው በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት እንዲተዳደርና ይህንንም ምርጫ ቦርድ እንዲያስወስን” ብሎ ፍ/ቤት ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ስለዚህ እኛ በዲሲፒሊንም ሆነ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አልታገድንም፤ ይህም በፍ/ቤቱ ውሳኔ የተረጋገጠ ነው፡፡
ኢ/ር ኃይሉ “ፓርቲውን እንዳሻቸው የሚያሽከረክሩ አምባገነን ናቸው” በሚል ስትወቅሱ ነበር፡፡ አሁን እርቃችሁ በምን መሰረት ላይ የፀና ነው?
እኛ በመጀመሪያ ወደ እርቁ ስንመጣ ማዕከል ያደረግነው ድርጅታችንን ነው፡፡ ድርጅታችን አደጋ ላይ ነበር፡፡ አንደኛ ህጋዊ ሰውነት አልነበረውም፡፡ በየሁለት ዓመቱ መከናወን የነበረበት ጠቅላላ ጉባኤ ባለመካሄዱ ችግር ላይ ነበር፡፡ ሁለተኛው እርቃችን መሰረት ያደረገው መርህን ነው፡፡ መተዳደሪያ ደንባችን ምን ይላል? የሚለውን ቁጭ ብለን ነው የመረመርነው፡፡ አንድ ፕሬዚዳንት ሲመረጥ ምን ይላል? ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት፣ ምክትሉና ፀሐፊው የሚመረጡት በጠቅላላ ጉባኤው ነው ይላል፡፡ ሌሎች የስራ አስፈፃሚዎችን ደግሞ ፕሬዚዳንቱ መርጦ ለላዕላይ ም/ቤቱ ያቀርባል፡፡ ላዕላይ ም/ቤቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርብና ሹመቱ እንዲፀድቅለት ይጠይቃል ይላል፡፡ መተዳደሪያ ደንባችን ይሄን ይላል፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የአቶ ያዕቆብ ልኬ አመራረጥ ስህተት ነበር፡፡ በኋላም ኢ/ር ኃይሉ ይሄን በሚገባ ተረድተውታል፡፡ እናምየኛ አካሄድ ልክ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተን ተስማምተን፣ ከኛም ሆነ ከእሳቸው ይልቅ ድርጅታችን እንደሚበልጥ ተማምነንበት በሙሉ ድምፅ እርቅ ተፈጸመ፡፡ እርቁ ደግሞ በእሳቸውና በኛ ብቻ አይደለም የተወሰነው፡፡ ከመላ ሃገሪቱ በመጡ የጉባኤው አባላት ነው፡፡ ከእሳቸው ጋር ከታረቅን በኋላ ሁለታችንም ወደ ጠቅላላ ጉባኤው ነው የመጣነው፡፡ ጉባኤው የፓርቲው የመጨረሻ አካል እንደመሆኑ፣ እርቁ መፈጸም አለበት ብሎ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡
ኢ/ር ኃይሉ  ስህተታቸውን በሚገባ አምነው ተቀብለዋል ማለት ነው?
ያሳሳቷቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ እሳቸው በወቅቱ ታመው ውጭ ሃገር ለህክምና ይመላለሱ ነበር፡፡ ያኔ አንዳንድ ሰዎች የሚሰጧቸው መረጃ የተሳሳተ ነበር፡፡ የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ኋላ ላይ እሳቸውም አረጋግጠዋል፡፡ ለምሳሌ የፍ/ቤቱን ጉዳይ እኛ አሸንፈን እያለ፣ “ተሸንፈዋል” የሚል መረጃ ነበር የቀረበላቸው፡፡ እርቁ እስከሚፈፀም ድረስ ፍ/ቤቱ በኛ ላይ እንደወሰነ ነበረ የሚያውቁት፡፡ የፍ/ቤቱ ውሳኔ ሲነበብላቸው ግን በጣም ነው ያዘኑት፡፡ ምን ዓይነት ስህተት ውስጥ እንደከተቷቸውም ተረድተዋል፡፡ ስለዚህ እርቃችን በደምሳሳው የተካሄደ ሳይሆን ከአንድ ወር በበለጠ ሂደት ብጥር ተደርጎ የተስማማንበት ነበር፡፡
እናንተን ጨምሮ በርካቶች “መኢአድ ኢ/ር ኃይሉ በገንዘባቸው የሚያሽከረክሩት የግለሰብ አምባገነንነት የነገሰበት ፓርቲ ነው” በማለት ስትነቅፉ ነበር፡፡ አሁን የአቋም ለውጥ አድርጋችኋል ማለት ነው?
መኢአድ የህዝብ እንጂ የግለሰብ ድርጅት አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢ/ር ኃይሉ ይሄን ድርጅት በሊቀመንበርነት ብዙ ዓመት መርተዋል፤ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በገንዘባቸው ግን እንደፈለጉ አያሽከረክሩትም፡፡ እኛም እሳቸውም እኩል ድምፅ ነው ያለን፡፡  እንኳን አቶ ኃይሉ ቀርተው ማንም በገንዘብ፤ሊያሽከረክረው አይችልም፡፡ ለምን? መኢአድ ብዙዎች ዋጋ የከፈሉለት ድርጅት ነው፡፡ አቶ ኃይሉ ድርጅቱን በገንዘብ ሊረዱ ይችላሉ፤ ሌላውም ሊረዳ ይችላል፤ ያ ማለት ግን በገንዘብ ማሽከርከር አይደለም፡፡
አሁን ኢ/ር ኃይሉ አምባገነን አይደሉም ነው የምትሉት?
እሳቸው በወቅቱ ህመም ላይ ነበሩ፡፡ የሚነግሯቸውን ነው ይዘው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ ውሳኔዎች ሁሉ ትክክል አልነበሩም፡፡ አሁን ይሄን ተረድተዋል፡፡ አቶ ኃይሉ በአምባገነንነት የሚወስኑት ውሳኔ ስለሌለ እኮ ነው እኛ የተቃወምነው፡፡ ለዚህ ነበር “እርስዎም እኛም እኩል ድምፅ ነው ያለን” ያልነው፡፡ እሳቸውም በውይይት ያምናሉ፤ ግን ከፓርቲው ብዙ ጊዜ ሲርቁ የተነገራቸውን ነው ይዘው የሚሄዱት፡፡ ያኔ ያሳሳቷቸው ሰዎች አሁን በአጠገባቸው የሉም፡፡ ያ እውነት ስለነበረን ነው እንደዚያ ባለ ሂደት ውስጥ ያለፍነው፡፡
የፓርቲውን ገንዘብ አጥፍታችኋል የሚል ክስም ቀርቦባችሁ ነበር፡፡ እሱንስ በምን አግባብ ፈታችሁት?
ይሄ ጉዳይ በዚህኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ቀርቧል፡፡ በ2003 ዓ.ም በአይቤክስ ሆቴል ተካሂዶ በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፋይናንስ አስተዳደር የነበሩት አቶ ማህተመ በኩረ፤ ስራ አስፈፃሚ ሆነው ስላልተመረጡና ስለጠፉ፣ ለአባላቱ አበል የሚከፍል ጠፍቶ ትልቅ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለሆቴሉ የሚከፈለውንና 30ሺህ ብር መጠባበቂያ ገንዘብ እኔና ዶ/ር ታዲዎስ ቦጋለ በፊርማችን፣ አቶ ያዕቆብ ልኬና አቶ ግርማ ነጋ ገንዘቡን በማውጣት፣ ክፍያው ሲፈፀም ገንዘቡ ስላልበቃ (የተጠየቀው የገንዘብ መጠን 256 ሺህ ብር ነው፤ ያወጣነው ግን 90 ሺ ብር ብቻ ነው) ሩቅ ላሉት እየጨመርን፣ ቅርብ ላሉት ደግሞ ከአበላቸው ላይ እየቀነስን፣ ዶ/ር በዛብህ ደምሴ ባሉበት ሰጥተናል፡፡ ይሄን ጉዳይ በአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም አረጋግጠናል፡፡ ሁለተኛ፤ በኦዲት ወቅት “ብዙ ገንዘብ መበላቱን አረጋግጠናል” ብለው ያወሩት ነገር አለ፤ በወቅቱ እኛ ከቢሮ እንዳንገባ ተደርገን፣ ዶ/ር ታዲዎስም በታሰሩበት ሰዓት ከፍ/ቤት ትዕዛዝ ውጭ የታሸጉ ቢሮዎችን ሰብረው ገብተው “ኦዲት አደረግን” ያሉት ነበር፤ ያ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሌላው በመኢአድ ፅ/ቤት ውስጥ እነሱ ተበላ ያሉትን ያህል ብር ሊኖር አይችልም፡፡  በዚህኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ራሳቸው አቶ አበባው በጉባኤው ፊት ቆመው፣ “እነ አቶ ማሙሸትን በገንዘብ አምተናቸዋል፣ ስማቸውን አጥፍተናል ነገር ግን ባላደረጉት ነው የወነጀልናቸው፤ ባይሆን ኃይለኞች ናቸው” ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ምርጫ የተገባው፡፡ ከምርጫው በኋላም እሳቸው ለጠቅላላ ጉባኤው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ፅፈው የሄዱ ሲሆን ጠቅላላ ጉባኤውም ቆሞ አጨብጭቦ ነው የሸኛቸው፡፡
በፍ/ቤት የቀረበባችሁና አሸንፈናል ያላችሁት ክስ ምን ይዘት ነበረው?
የቀረቡብን ክሶች አምስት ናቸው፡፡ አንዱ ክስ ሁከት መፍጠር ነው የሚለው፤ ሁለተኛው የአቶ ኃይሉ ሻውልን መኪና መስበር፣ ሶስተኛው አሲድ መርጨት፣ አራተኛው ድብደባ ፈፅመዋል የሚል ሲሆን አምስተኛው በሃሰት ማህተም መጠቀም የሚሉ ናቸው፡፡ በሁከቱ ጉዳይም ሆነ አሲድ መርጨት በሚለው ፈፅሞ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ በተለይ አሲድ ረጩ በተባለው ጉዳይ አሲድ ተረጨበት የተባለው ግለሰብ ተመርምሮ፣ አሲድ እንዳልሆነ ተረጋገጠ፡፡ በዚህ የተከሰሱት ሰዎች ነፃ ወጡ፡፡ የአቶ ኃይሉን መኪና በተመለከተ ምስክር ጠፋ፡፡ ፍ/ቤቱም በሃሰት ነው የተከሰሱት ብሎ ክሱ ተዘጋ፡፡ ድብደባውን በተመለከተ ተደብድቧል የተባለው ዘበኛ ቀርቦ “አልተደበደብኩም፤ ክሰስ ስላሉኝ ነው የከሰስኩት” ብሎ ተናገረ፡፡ ፍ/ቤቱ በዚህ ክስም ነፃ ናችሁ አለ፡፡ ማህተም መጠቀም በሚለው ዶ/ር ታዲዎስና አቶ ግርማ ነጋ ተከሰሱ፡፡ የአራዳ ምድብ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፤ በአንድ ቀጠሮ ብቻ ዶ/ር ታዲዎስን 2 ዓመት ከ4 ወር፣ አቶ ግርማ ነጋን 1 ዓመት ከ8 ወር እንዲታሰሩ ፈረደባቸው፡፡ በይግባኝ ከፍተኛው ፍ/ቤት ከእያንዳንዳቸው እስር ላይ 6 ወር አነሳላቸው፡፡ ቀጥለንም ጉዳዩን ሰበር አደረስነው፤ ተከራካሪው እኔ ነበርኩ፤ አምስቱም ዳኞች የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ተችተው፣ ከክሱ ነፃ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ በአምስቱም ክሶች ነፃ ወጥተናል፡፡
ኢ/ር ኃይሉ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተፅዕኖ ፈጥረው፣ እናንተን ከውጪ አምጥተው አስመርጠዋል የሚሉ  ወገኖች አሉ፡፡ ኢ/ር ኃይሉ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የነበራቸው ሚና ምንድን ነው? ያንንስ ሚና በምን አግባብ አገኙ?
እኛ ከውጪ የመጣን አይደለንም፣ ለዚህ ፓርቲ ከማንም በላይ መስዋዕትነት የከፈልን ሰዎች ነን፡፡ እግድ የተባለውም በፍ/ቤት ተሽሯል፡፡ ከፍ/ቤት በላይ ማንም ሊመጣ አይችልም፤ ይሄ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራበት ዋናው ምክንያት የኛን ጉዳይ ለማየት ነው፡፡ አቶ ኃይሉ በ2003 በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እኛ ራሳችን በሙሉ ድምፅ የመረጥናቸው ፕሬዚዳንታችን ናቸው፡፡ እኛ አካሄዱን ነው እንጂ የተቃወምነው ፕሬዚዳንት መሆናቸውን አንጠራጠርም፡፡ አሁን ያንን ሚናቸውንና ኃላፊነታቸው ነው የተወጡት፡፡ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም የፓርቲው ህጋዊ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ኃይሉ ነበሩ፡፡ የ2005ቱ ጠቅላላ ጉባኤ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው ማለት ነው፡፡ በዚህ ኃላፊነታቸው ይሄኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተዋል፡፡ መድረኩን የመሩትም በፕሬዚዳንትነት ኃላፊነታቸው ነው፡፡ ምርጫው የተካሄደውም እሳቸውን የሚተካ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ነበር፡፡ ነገር ግን አቶ አበባው እንዲወዳደሩ ሲጠየቁ፣ አስቀድመው ደብዳቤ አዘጋጅተው ተራ አባል እሆናለሁ ብለው ከውድድሩ ጥለው ወጡ፡፡ ኢ/ር ኃይሉም ሆኑ እኛ አቶ አበባውን ከጉባኤው  ገፍተን አላስወጣንም፤ ውድድሩ ነፃ ነበር፡፡
አቶ አበባው መኢአድን ከአንድ ዓመት በላይ ሲመሩ ቆይተው “ፓርቲው በፕሬዚዳንትነት አያውቃቸውም” ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?
ምርጫ ቦርድ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም በፕሬዚዳንትነት የሚያውቃቸው አቶ ኃይሉ ሻወልን ነው፡፡ አቶ አበባው ኮረም ባልሞላ ጉባኤ የተመረጡ ሰው ናቸው፡፡ የጥቅምት 30 ጠቅላላ ጉባኤ አብላጫው አያውቃቸውም፡፡ ስለዚህ እሳቸው የመኢአድ ህጋዊ ፕሬዚዳንት አልነበሩም ማለት ነው፡፡ ኢ/ር ኃይሉም ቢሆኑ የጀርባ ተልዕኮ  ይዘው የመጡ አይደሉም፡፡ በወቅቱ ስልጣናቸው ስለሚፈቅድላቸው ነው መድረኩን የመሩትም ሆነ ጉባኤውንም የጠሩት፡፡ ሃቁ ይሄ ነው፡፡
ኮረም አልሞላም ሲሉ …
ኮረም አልሞላም ሲባል መገኘት የነበረባቸው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በአብላጫ ቁጥር አልተገኙም ማለት ነው፡፡ ኢ/ር ኃይሉ የ2005 ጠቅላላ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ ውድቅ መሆኑን እርቁ እስከሚፈፀምበትና የመኢአድና አንድነት ውህደት እስኪደናቀፍ ድረስ አያውቁም ነበር፡፡ የአቶ አበባው ካቢኔ ህጋዊ እንደሆነ ነበር የተነገራቸው፡፡ ሃቁን ተደብቀዋል፡፡ እኛ ያንን ነው አንጥረን ያወጣነው፡፡ አቶ ኃይሉም በዚህ መሰረት ነው ግዴታቸውን የተወጡት፡፡
ኢንጂነር ኃይሉ የፓርቲው የበላይ ጠባቂ ናቸው የሚለው ነገር እንዴት ነው?
እሱ በ2005 የተፈጠረ ነገር ነው፡፡ መኢአድ የበላይ ጠባቂ የሚባል ነገር የለውም፡፡ መተዳደሪያ ደንባችን ላይም የለም፡፡ ከየት እንደመጣም አናውቅም፡፡ አሁን ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው የፓርቲው አማካሪ ሆነዋል፡፡ የበላይ ጠባቂ የሚለውን ግን አናውቀውም፡፡ መተዳደሪ ደንባችን ላይም ፓርቲው የበላይ ጠባቂ ይኖረዋል የሚል የለም፡፡ የምንተዳደረው ግንቦት 1 ቀን 2001 በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በፀደቀው ደንባችን ነው፡፡
ወደ ጉባኤው ከፍተኛ ደጋፊ ይዛችሁ በመግባት ሁለት ዓመት በተራ አባልነት እንድትገመገሙ የተወሰነውን ውሳኔ በማፈን ነው ወደ ስልጣን የመጣችሁት የሚል ወቀሳም ቀርቦባችኋል …
ይሄ ቀልድም ይመስላል፡፡ እኛ ትልልቅ ሰዎች ነን፡፡ እርቅ ምን እንደሆነና የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ምንም ይሁን ምን የሚወሰንብንን ለመቀበል ተዘጋጅተን ነው የገባነው፡፡ በሌላ በኩል ቲፎዞ (ደጋፊ) ይዘው ገብተው ነው የሚባለው፣ አንደኛ በጉባኤው መገኘት የሚችሉት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ በውድድር ደግሞ ደጋፊ አብዝተህ እንዲመርጥህ ማድረግ አንዱ የዲሞክራሲ መርህ ነው፡፡ ግን እኛ አንድም ሰው እንዲመርጠን አልጠየቅንም፡፡ ነገር ግን እነሱ አራት ዓመት ሙሉ ሲሉ የቆዩትና እኛ ቀርበን ስናስረዳ እውነቱ ስለወጣ ነው ሚዛኑ የተለየው፡፡ እኛ ሁለቱንም ቀን ምንም ሳንናገር ቆይተን ነው በሶስተኛው ቀን እንድንናገር የተደረገው፡፡
አቶ አበባውም ያኔ ነው ስለኛ በገንዘብ አለመታማት የመሰከሩት፡፡ ህዝቡም አጨብጭቦ ነው እውነቱን የተቀበለው፡፡     
ቀጣዩ ምርጫ ሊካሄድ ስድስት ወር ብቻ በቀረበት ወቅት ፓርቲው በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት የላችሁም?
ውሳኔ የሚሰጠው ህዝብ ነው፡፡ ለምርጫም የምንቀሰቅሰው ህዝቡን እንጂ እነ አቶ አበባውን አይደለም፡፡ አሁን እነሱ እየሰጡት ያለው መግለጫ ምንም ጥርጥር የለውም ይቆማል፡፡ መኢአድ ለሁለትና ለሶስት አካል አይገዛም፡፡ ህጋዊ አካል ሊሆን የሚችለው አንድ ወገን ብቻ ነው፡፡ ቦርዱም ይሄንን የሚታገስበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
 በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ተደሳች ቦርዱ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ኢ/ር ኃይሉ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ ያሳሰበውም ቦርዱ ነው፡፡ እሳቸው ባይጠሩ ኖሮ፣ እኛ ባሰባሰብነው የ300 ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ፊርማ ጉባኤው ሊጠራ ይችል ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ቦርዱ የአሁኑን ጠቅላላ ጉባኤ ህጋዊ ሰውነት እንደሚያረጋግጥ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምርጫን በተመለከተ አሁንም በመላ ሀገሪቱ መዋቅራችን  ሰፊ ነው፡፡ ወደ ምርጫው ለመግባትም ሆነ ተወዳዳሪ ለመሆን በኛ አደረጃጀት የምንቸገርበት ነገር አይኖርም፡፡ ጊዜ ስላለንም ለዝግጅት ይበቃናል፡፡
ከአንድነት ጋር የተጀመረው ውህደት የሚቀጥል ይመስልዎታል?
እስካሁን ሰነዶች እጃችን አልገቡም፡፡ ከአንድነት በኩልም አላገኘንም፡፡ ፓርቲው በ9 ፓርቲዎች በተመሰረተ “ትብብር” ውስጥም አለበት ተብሏል፡፡ ስለሱም አናውቅም፤ ወደፊት ሰነዶች አይተን የምንወስንበት ይሆናል፡፡
መኢአድን የሚመሩት ከአንድ ብሄር የሚወከሉ፤ ባስ ሲልም እርስዎን ጨምሮ የሰሜን ሸዋ አካባቢ ሰዎች ብቻ ናቸው የሚል ቅሬታ ይሰማል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ  የመኢአድ ፕሬዚዳንትነት አመራረጥ ሂደት፣ ዘርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ዘርና ቋንቋን መሰረት ካደረግን በቀጥታ የዚህን መንግስት የፌደራሊዝም አወቃቀር ተከተልን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ስርዓት የሚለየው የመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የህዝብ አሰፋፈርና የኢኮኖሚ ፍሰትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ነው፡፡
ፕ/ር አስራት ወልደየስ የተመረጡት በችሎታቸው ነው፡፡ አቶ ኃይሉንም ከቀረቡት 23 ሰዎች ውስጥ በትምህርትና በአመራር ብቃት ተብሎ ህዝቡ በአንድ ድምፅ ነው የመረጣቸው እንጂ በሰሜን ሸዋነታቸው አይደለም፡፡ አቶ አበባው ለምሳሌ ከጎጃም የመጡ ናቸው፡፡ ጎጃሜነታቸውን መሰረት ያደረገ ምርጫ አልነበረም፡፡
አሁንም ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንቱ የአሩሲ ሰው ናቸው፣ ም/ፕሬዚዳንቱ ከሳውላ ጎት ናቸው፡፡ እኔም በፕሬዚዳንትነት ስመረጥ በሰሜን ሸዋ ተወላጅነቴ አይደለም፡፡
መንደርን መሰረት አድርጎ የሚነሳ ዘረኝነት ከቀጠለ፣ ትልቋን ሃገራችንን እንረሳታለን፡፡ ይሄ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ እኔ ከአቶ አበባው በላይ ለዚህ ድርጅት ዋጋ ከፍዬበታለሁ፡፡ በዚህ በኩል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
አንዱ የፕሬዚዳንትነት መስፈርት፣ እጩው በድርጅቱ ውስጥ የከፈለው መስዋዕትነትና ቆይታ ነው፡፡ ምርጫው የሚካሄደው በዚያ መሰረት እንጂ በተወለድንበት አካባቢ አይደለም፡፡ መኢአድ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤት ነው፡፡

Read 3081 times